CURRENT

በዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ አህጉራዊ ጉባዔ በመጪው ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

By Admin

May 13, 2017

በዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ አህጉራዊ ጉባዔ በመጪው ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ጉባዔው “ሁሉን አሳታፊ ዘላቂ ልማትና ብልጽግና ለሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ ከግንቦት 9 እስከ 11 2009 ዓ.ም በአፍሪካ ኅብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ይካሄዳል።

የአፍሪካ ሃገራት ልምድና ተሞክሮ በመለዋወጥ የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችና የ2063 አጀንዳ ተፈጻሚነት ላይ መወያየት የጉባዔው ዋነኛ አጀንዳ ይሆናል ተብሏል።

በ2017 ለማሳካት የታቀዱና የ2063 አጀንዳ የመጀመሪያ 10 ዓመት ግቦች ማሳካትን አስመልክቶም ውይይት ይካሄዳል።

ድህነትን በማስወገድ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የሚካሄድ ምክክርም ሌላው የውይይቱ አጀንዳ ነው።

ተሳታፊዎች “ሁለቱን የልማት ግቦች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ያሉ ዕድሎችና ፈተናዎች ምንድን ናቸው?” በሚል ርዕስ እንደሚመክሩም ይጠበቃል።

ከጉባዔው ጎን ለጎን ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር አባላት በዘላቂ ልማት ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን፣ የመንግስታቱ ድርጅት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ተቋማት፣ የልማት አጋሮችና ባለድርሻ አካላት በጉባዔው እንደሚሳተፉ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ድረ-ገጽን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።