CURRENT

“በፍጥነት ያልተሰጠ ፍትህ እንደ ቀረ ይቆጠራል!”

By Admin

May 03, 2017

አያድርስብዎትና አንድ በጉልበቱ አዳሪ አሳቻ ሰዓት ጠብቆ እርስዎ ላይ አሊያም ደግሞ ንብረትዎ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ቢመጣብዎት ምን ያደርጋሉ? ሞቴን ሞት ያድርገው ብለው ራስዎንና ንብረትዎን ለመታደግ ይሞክሩ ይሆን? መልሱን ለእናንተው ትቼዋለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ሰዎች ጉልበት ሲያጥራቸውም ሆነ በቅርብ ሊደርስላቸው የሚችል አጋር ሲቸግራቸው ፊት ለፊታቸው አደጋ የደቀነባቸውን አካል “ኧረ በህግ?“ብለው ሊያስቆሙትም ሊያስፈራሩትም ይሞክራሉ፡፡

ጉዳት አድራሹ አካል ‘በህግ’ ስለተባለ ብቻ ሊፈጽመው የተዘጋጀበትን ወንጀል ከመፈጸም ይቆጠባል ወይ? የሚለው ጥያቄ ምላሹ ግልጽ ቢሆንም ተጠቂዎቹ በአካባቢያቸው ሊጠሩትና አቤት ሊላቸው የሚችል አካል በሌለበት ጊዜና ቦታ ሁሉ ህግን ጠርተው ከተደቀነባቸው አደጋ ራሳቸውን ለማዳን መሻታቸው ግን ህግ ጉልበት ላጣው፣ አቅም ላነሰው፣ የቅርብ አጋር ለሌለው ሁሉ ጥላ ከለላ መሆኑን ያመላክታል፡፡

በእርግጥም ህግ ሰው ባለበትም ይሁን በሌለበት ጊዜና ቦታ ሁሉ ጉልበት ላጠራቸው መከታ፣ አቅም ላነሳቸው ምርኩዝ ነው፡፡ ለአንድ ሀገር ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና ሁሉ ህግ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ያገለግላል፡፡

ዓለማችንን ያለ ህግ አስባችኋት ታውቃላችሁ? ስርቆቱ፣ ግድያው፣ ስርዓት አልበኝነቱ፣… ዓለማችንን ከመኖር ወደ አለመኖር ሊቀይራት ይችል እንደነበር ለመገመት አያዳግትም፡፡ ለዚህም ነው አንድ ሀገር እንደ ሀገር ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ቅድሚያ ሰጥቶ የጸጥታና ፍትህ ተቋማትን ለማጠናከር የሚሯሯጠው፡፡

ሀገራት ውስጣዊ ሰላምና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ ከሚያቋቁሟቸው የፍትህና የጸጥታ ተቋማት በተጨማሪ ዓለም ዓቀፍ ወንጀልንና ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር የሚያስችሏቸውን የሰላም፣ የፍትህና ጸጥታ ተቋማትንም አቋቁመዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም በዓለማችን ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ወንጀሎችን እንዳይፈጸሙ ማድረግ ግን አልተቻለም፡፡

ዓለማዊው ህግ አጥፊዎችን በመቅጣት ራሳቸውን ያርማል፤ ሌላውም መሰል ጥፋቶችን እንዳይፈጽም ያስጠነቅቃል(ያስተምራል)፡፡ አጥፊዎቹ እንደ ጥፋታቸው ክብደትና ቅለት ከቀላል እስከ እድሜ ልክ እስራትና ከዚያም ሲያልፍ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ሊተላለፍባቸው ይችላል፡፡

መንፈሳዊው ህግም ቢሆን ከሞት በኋላ ይኖራል ተብሎ የሚታሰበውን ቅጣት ጠቅሶ ያስተምራል፤ ይመክራል፡፡ ሁለቱም ህግጋት እንድንተገብራቸው የተፈቀዱና እንዳናደርጋቸው የተከለከሉ ትዕዛዛት አሏቸው፡፡ አድርጉ የተባለውን አለማድረግና አታድርጉ የተባለውን ደግሞ ሲያደርጉ መገኘት ሁለቱም ለህግ ተጠያቂነት ይዳርጋሉ፡፡

ይህ ማለት ግን ህግጋቱ በስውርም በአደባባይም አይጣሱም ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የሰው ልጅ እያወቀ በድፍረት ሳያውቅ በስህተት ህግን ይተላለፋል፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ህግን መጣስ ግን ከተጠያቂነት እንደማያድን ዓለማዊውም ሆነ መንፈሳዊው ህግ በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡ ለዚህም ነው ዓለማዊውንም ሆነ መንፈሳዊውን የህግ ስርዓት በህብረተሰቡ ዘንድ ለማስረጽ የሚመለከታቸው ተቋማት ጊዜ ወስደው ለማስተማርና ለማሳወቅ ሲወጡ ሲወርዱ የሚስተዋሉት፡፡

ሀገራችን ህግና ስርዓትን በመላ ሀገሪቱ ለማስፈን እንዲሁም  የዜጎችን ህጋዊ ዋስትና ለማረጋገጥ የጸጥታና ፍትህ ተቋማትን የማጠናከርና ከማንኛውም ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው ስራቸውን በነጻነት የሚያከናውኑበትን ሥርዓት ዘርግታለች፡፡ ይሁን እንጂ ዘርፉ የመልካም አስተዳደር ችግርን መሻገር ባለመቻሉ በህዝብ ዘንድ ቅሬታን አስነስቷል፤ የህዝብ አመኔታውም የሚገባውን ያህል አላደገም፡፡

ተገልጋዮች ፍትህን ፍለጋ  ወደ ተቋማቱ  ጎራ ባሉበት ጊዜ በፍጥነትና በተገቢው መንገድ ሳይስተናገዱ ሲቀሩ ያማረራሉ፣ ይሰላቻሉ ግፋ ሲልም በተቋማቱ ላይ የነበራቸው እምነት ይሸረሸራል፡፡ ከዚህ አልፎም የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ በህዝብ ዘንድ ቅሬታ ይፈጥራል፡፡ ቅሬታው እየዋለ እያደረ ሲሄድ ደግሞ ለስርዓት አልበኝነት መንስኤ ወደ መሆን ሊሸጋገር ይችላል፡፡

የፍትህ ስርዓቱን ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ለማላቀቅ የተለያዩ ጥረቶች መተግበራቸውን ተከትሎ መጠነኛ መሻሻሎች መታየታቸውን ያነጋገርናቸው የህግ ባለሙያዎች አረጋግጠውልናል፡፡ ይህ ማለት ግን ዘርፉ ከችግሩ ሙሉ ለሙሉ ተላቋል ማለት እንዳልሆነም ነው ባለሙያዎቹ የሚናገሩት፡፡

ተመስገን ላጲሶ በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዓቃቤ ህግ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ምንም እንኳን የዛሬው የፍትህ ስርዓት ያለምንም የፍርድ ሂደት የሰው ልጅ በብጣሽ ወረቀት ላይ በሰፈረ ቃለ ጉባዔ ብቻ ይረሸን ከነበረበት ጊዜ ጋር ለንጽጽር የማይቀርብ ቢሆንም ዛሬም ቢሆን ከህዝብ ቅሬታ ሙሉ ለሙሉ ነጻ ነው ለማት አያስደፍርም፡፡

“ጠንካራ የፍትህ ስርዓት በለሌለበት ስለ ልማት፣ ሰላምና እድገት ማሰብ የዋህነት ነው” የሚሉት አቶ ተመስገን ሰዎች ጥረው ግረው ያፈሩት ሀብት ንብረት ዋስትና የማይኖረው ከሆነ እንዲሁም በሰላም ወጥተው ለመመለስ የማይተማመኑበት ሁኔታ ከተፈጠረ የሀገር ውስጥ ዜጋው ሰርቶ የመለወጥ ፍላጎት ይኮሰምናል፤ የውጭ ባለሀብቱም ቢሆን አስተማማኝ ህግና ስርዓት በሌለበት ሀገር ገንዘቡን፣ እውቀቱንና ጉልበቱን ሊያፈስ እንደማይችል አብራርተዋል፡፡

ዛሬ በመላ ሀገሪቱ እየተተገበረ ያለው የፍትህ ስርዓት ህገ መንግሥታዊ ዋስትና አለው፡፡ ፍርድ ቤቶች ያለምንም ተጽዕኖ በነጻነት ህግን የመተርጎም ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ ዓቃቤ ህግ፣ ፖሊስና የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ደግሞ ህጉን የማስፈጸም ግልጽ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ይላሉ አቶ ተመስገን ላጲሶ “… ይህ ማለት ግን የፍትህ ስርዓቱ ከሚፈለገው ደረጃ  ደርሷል ማለት ሳይሆን በትክክለኛው መስመር ላይ እየተጓዘ መሆኑን ይጠቁማል፡፡”

አቶ ተመስገን እንዳብራሩት በተለይ በተቋማቸው የለውጥ መሳሪያዎች መተግበር ከጀመሩ ወዲህ ተገማችና ቀልጣፋ የፍትህ አሰጣጥ ስርዓቱ ፈር እየያዘ መጥቷል፡፡ ቀላል፣መካከለኛና ከባድ ተብለው የተፈረጁ የወንጀል አይነቶች በምን ያህል ጊዜ መከናወን እንዳለባቸው በማያሻማ መልኩ ተቀምጧል፡፡ ይህም ለፖሊስ ከሚደርሰው ጥቆማ እስከ አቃቤ ህግ ምርመራና ውሳኔ ድረስ በተቀመጠው ጊዜ እየተከናወነ በመሆኑ የሚወዘፉ መዛግብት ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱንም ነው አቃቤ ህጉ ያብራሩልን፡፡

ሌላው የፌደራል ዓቃቤ ህግ አቶ ዋለልኝ ምትኩ ከተወሰኑ ጊዜያት በፊት ምርመራ የሚያደርጉት ከፖሊስ አባላት ጋር ሆነው እንደነበር ጠቅሰው አሁን በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ስር መካተታቸው ስራቸውን እንዳቀላጠፈላቸው ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳን አሁንም ቢሆን ቦታው ድረስ ሄዶ ምርመራ ለማድረግ ግድ የሚልበት ሁኔታ ቢኖርም አብዛኛውን ጊዜ ግን መዝገቦች ተጠናቅረው ስለሚቀርቡላቸው በአፋጣኝ ያስከስሳል አያስከስስም የሚሉ ውሳኔዎችን ለመስጠት አግዟቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ያለውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ ችግሮቹ ተለይተው አስቸኳይ የመፍትሄ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም  ነው የዓቃቤ ህጉ እምነት፡፡

አቶ ዋለልኝ  ለፍትህ ስርዓቱ መጓተት በምክንያትነት ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የምስክሮች ተሟልቶ አለመቅረብ ነው፡፡ ምስክር በሌለበት ፍርድ መስጠት የማይቻል በመሆኑም ምስክሮችን አሟልቶ ለመስማት ሲባል የፍርድ ሂደቱ ይጓተታል፡፡ “በፍጥነት ያልተሰጠ ፍትህ እንደ ቀረ ይቆጠራል” የሚል አባባል ጠቅሰውም የህብረተሰቡ ቅሬታ ተገቢ መሆኑን አስረድተውናል የፌደራል ዓቃቤ ህጉ አቶ ዋለልኝ ምትኩ፡፡

በውጫዊ ምክንያቶች የተነሳ የፍርድ መጓተቱ በሰፊው ይሰተዋል እንጂ የአገልግሎት ሰጪው ድክመቶችም ለቅሬታ መንስዔ የሚሆኑበት አጋጣሚ መኖሩን አቃቤ ህጉ አልደበቁም፡፡

ለዚህም አልፎ አልፎም ቢሆን የተከሳሹ አለመገኘት፣ ማስረጃ በቅጡ ሳይሰበሰብ ቀርቶ ክስ ሊሆን የሚገባው ጉዳይ በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ህጉ አንቀጽ 42 መሰረት ሊዘጋ የሚችልበት አጋጣሚ እንዲሁም የሰው ሃይልና የግብዓት አቅርቦት እጥረቱና መሰል ሁኔታዎች ለተገልጋዮቹ አለመርካት ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በነዚህና መሰል ምክንያቶች የፍርድ መጓተቱ በህዝብ ዘንድ ቅሬታ ያስነሳ እንጂ ቀድሞ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ግን መሻሻል መኖሩን አቶ ዋለልኝ አጫውተውናል- ለዓመታት ሲንከባለል የነበረ መዝገብ በአሁኑ ጊዜ ከ3-5 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ እልባት የሚያገኝበት የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን በአስረጂነት በመጥቀስ፡፡

በሰው ሃይልና አስፈላጊ በሆኑ ግብአቶች የተደራጁ የፍትህ ተቋማትን ከአሁኑ በተሻለ ማስፋፋት የሚቻልበት አግባብ ቢፈጠር ደግሞ የህብረተሰቡ ቅሬታ ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀረፍ ያምናሉ፡፡

የፌደራል ዓቃቤ ህጉ ተመስገን ላፒሶ ደግሞ ህብረተሰቡ በፍትህ ስርዓቱ እንዳይረካ አድርገዋል ያሏቸውን ምክንያቶች በሁለት ይከፍሏቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ከፍትህ ተቋማት የሚመነጨው ችግር ነው፡፡ይኼውም ተቋማቱ የሚሰጡት አገልግሎት ህዝቡ በሚፈልገው ልክ ካለማደጉ ጋር ይያያዛል፡፡ ከስነምግባር ጉድለት ጋር የሚታዩ የፍትህ መዛባቶችም ሙሉ ለሙሉ ተወግደዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡

የህብረተሰቡ የህግ ንቃተ ህሊና አለመጎልበትም  ሌላኛው የፍትህ ስርዓቱ ማነቆ ሆኗል፡፡ አንድ የወንጀል ድርጊት በሚፈጸም ጊዜ ጉዳዩ አቃቤ ህግ ዘንድ ከመድረሱ በፊት ከመገናኛ ብዙሃን እጅ ይገባል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ደግሞ ስለ ወንጀሉ ምንነትና ስለ አስከፊነቱ እንጂ ስለ ህጉና ስለ ቅጣቱ የሚሰጡት መረጃ ስለማይኖር በኋላ በጥፋተኛው ላይ የቅጣት ውሳኔው በሚተላለፍበት ጊዜ ህብረተሰቡ በውሳኔው አይረካም፤ ህጉ ላይም እምነት እያጣ ይመጣል፡፡

መገናኛ ብዙኃን የህክምና ማስረጃ በሌለበት፣የህግ ባለሙያዎች አስተያየት ባልታከለበት ሁኔታ  የወንጀሉን እከፊነት ከህብረተሰቡ አእምሮ ካሰረጹት በኋላ ፍርድ ቤቱ በሚያሳልፈው ውሳኔ  ህብረተሰቡ ሊረካ እንደማይችልም ነው ዓቃቤ ህጉ ያስረዱት–መገናኛ ብዙኃን ለወንጀል ዘገባዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በመጠቆም፡፡

የህብረተሰቡን የህግ ንቃተ ህሊና ከማጎልበት ጋር በተያያዘ የሚጠበቀውን ያህል ተሰርቷል የሚል እምነት እንደሌላቸውም አቶ ተመስገን ላጲሶ ተናግረዋል፡፡

ዛሬ የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በራሳቸው ቋንቋ የሚዳኙበት ስርዓት እውን ሆኗል፡፡ በየአካባቢያቸውም የፍትህ ተቋማት ተቋቁመውላቸዋል፡፡ እናም ተቋማቱ አገልግሎታቸውን ህገ መንግሥቱን መሰረት አድርገው መስጠት ከቻሉ የህዝቡ ቅሬታ የሚፈታበት ጊዜ ያን ያህል ሩቅ እንደማይሆንም ነው የህግ ባለሙያው የተናገሩት፡፡

አቶ ወንድማገኝ ብርሃኑ  በፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪና ሀገራዊ ጉዳት የሚያስከትሉ የወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ከሰባት ዓመታት በፊት የፍትህ ተቋማትና ህብረተሰቡ የሚነጋገሩበትና የሚመካከሩበት የጋራ መድረክ አለመኖሩ የተቋማቱንና ተገልጋዮቻቸውን ግንኙነት መሳ ለመሳ አድርጎት ቆይቷል፡፡

ተቋማቱ የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ እንዲሁም ህገ መንግሥቱንና ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ተቋማቱ በተዋረድ ከሚያቀርቡት ሪፖርት በዘለለ ወደ ህብረተሰቡ አውርደው የሚያስገመግሙበትና ከህብረተሰቡም ግብዓት የሚሰበስቡበት መድረክ እንዳልነበረ ያስታውሳሉ፡፡

በየዓመቱ የፍትህ ሳምንት መከበር ከጀመረ ወዲህ ግን ህብረተሰቡና የፍትህ ተቋማት በአንድ መድረክ ተገናኝተው የሚመካከሩበት እድል ሰፍቷል፡፡ ይህም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን ለህዝብ በማስገምገምና ለመልካም አስተዳደር እጦት መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን ከተገልጋዮቻቸው ጋር በመምከር አገልግሎታቸውን ለማሻሻል  አግዟቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፍትህ ሳምንቱ  የህብረተሰቡን የህግ ንቃተ ህሊና በማጎልበት ረገድም የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው አቶ ወንድምአገኝ ያብራሩት፡፡

በፍትሕ ስርዓቱ የህዝብ ቅሬታ የሚያስነሱ ክፍተቶችን ለመድፈን  የፌደራል ዓቃቤ ህግ የራሱን ጥረት እያደረገ መሆኑን ያብራሩት አቶ ወንድማገኝ፣ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ቅርንጫፎችን የማቋቋም፣ የሰው ሃይል እጥረቱን የማሟላትና አስፈላጊ ግብዓቶችንም የማቅረብ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ መጀመሩን በአስረጂነት አንስተዋል፡፡

የተበደለ ሊካስ፣ በዳይም ፍትሃዊና ተመጣጣኝ ቅጣት ሊተላለፍበት ግድ ይላል፡፡ ለዚህም ነው ጠንካራ የፍትህ ተቋማት የሚያስፈልጉት፡፡ ይሁን እንጂ ከአመለካከት፣ ከግንዛቤ እጥረትና መሰል ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የፍትህ ሂደቱ ሲጓተትና ባለጉዳዮችም ምልልስ ሲበዛባቸው ህጉ ላይ የነበራቸው ዓመኔታ ሊሸረሸርና በውሳኔውም ላይረኩ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ችግሩን ከስር መሰረቱ ለመቅረፍ ተነቅሰው የወጡ የመልካም አስተዳደር እጦት መንስኤዎችን ለማጥበብ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል፡፡

የፍትሕ ተቋማት ከህብረተሰቡ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከርና በስኬቶቻቸውና በክፍተቶቻቸው ዙሪያ  ክህብረተሰቡ ጋር ለመመካከር ዘንድሮም “የሕግ የበላይነት ለዘላቂ ሰላምና ለህዝቦች አንድነት” በሚል መሪ ቃል ሰባተኛውን የፍትህ ሳምንት ከሚያዝያ 30-ግንቦት 6/2009 ዓ.ም ባሉት ቀናት ያከብራሉ፡፡

ከዚያ ቀደም ብሎም የፌደራል የፍትህ ተቋማት የክፍለ ከተማ የንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀት ከህብረተሰቡ ጋር ምክክር በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ በየመድረኮቹም ህብረተሰቡ የተማረረባቸውንና ይስተካከሉ የሚላቸውን ጉዳዮች ነቅሶ በማውጣት ከፍትህ ተቋማት ተወካዮች ጋር በመመካከር ላይ ነው፡፡

ይህ መሰሉ ግልጽና አሳታፊ ውይይት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ነቅሶ ለማውጣት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ቀልጣፋ፣ፈጣንና ተገማች ውሳኔዎችን በመወሰን ህብረተሰቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት እዲያሳድርና ለስርዓቱ መጎልበትም የድርሻውን የሚወጣበትን ተነሳሽነት ለመፍጠር በር ይከፍታል፡፡ የፍትህ ሳምንቱ “በፍጥነት ያልተሰጠ ፍትህ እንደ ቀረ ይቆጠራል” የሚለውን ባህል ለመስበርም የጎላ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

ከእንግዳ መላኩ