Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ብልህ ከእርግብ ክንፍ ፍላጻ ይቀርጻል እንዲሉ …

0 308

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ብልህ ከእርግብ ክንፍ ፍላጻ ይቀርጻል እንዲሉ …

ወንድይራድ ኃብተየስ

አገራችን ባለፉት 26 ዓመታት በርካታ  ነገሮች (በመልካምም ይሁን በመጥፎ) ገጥመዋታል። የኢፌዴሪ  መንግስት መልካም አጋጣሚዎችን ብቻ ሳይሆን ተግዳሮቶችንም  ወደ ስኬቶች መቀየር የቻለ መንግስት ነው።  በእኔ ዕይታ መልካም አጋጣሚ  ናቸው እንዲሁም  መጥፎ ናቸው  ብዬ  ከለየኋቸው ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹን  ለማነሳት ወደድኩ። ከመልካሙ ለመጀመር ያህል አገራችን ባለፉት 26 ዓመታት መሰረታዊ ለውጦች ካሳየችበት ነገሮች መካከል የመጀመሪያው  የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን እኩልነትና ነጻነትን ያረጋገጠ ህገመንግስት ማግኘት መቻሏ ነው።

ህገመንግስቱ ለአገራችነ ህዝቦች ካስገኛቸው ጥቅሞች የመጀመሪያው ፌዴራላዊ ስርዓት እንድትከተል በማድረጉ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብትን አጎናጽፋቸዋል።   የፌዴራል ስርዓቱ ህዝቦች በመረጧቸው ተወካዮቻቸው እንዲተዳዳሩ፣ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን ማሳደግ የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸቱ ህዝቡ በማንነቱ እንዲኮራ አድርጎታል።  የኢፌዴሪ  ህገመንግስት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ  በማድረጉ ለአገሪቱ  ዘላቂ ሰላም   ዋስትና ሆኗል።  የህዝቦች አብሮነትና  አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆም ህገመንግስቱ የቃልኪዳን ሰነድ ሆኗቸዋል።

የኢፌዴሪ  ህገመንግስት ለዘመናት በህዝቦች መካከል የነበረን  የተዛባ አሰራርና አስተሳሰብ ማረም አስችሏል። አገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን መተግበር በመቻሏ በርካታ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ዴሞክራሲያዊ  ምርጫ በማካሄድ ህዝቦች ለመጀመሪያ  ጊዜ  ድምጻቸውን ይበጀኛል ላሉት ተወካዮቻቸው መስጠት ችለዋል። አገራችን እስካሁን አምስት አገራዊ ምርጫዎችን በማድረግ ህዝቦች ይበጀኛል ይወክለኛል ለሚሉት አካል ድምጻቸውን መስጠት ችለዋል። የምርጫ ስርዓቱ የራሳቸው እጥረቶች ቢኖሩባቸውም  ሄደታቸው ግን  ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ የታየባቸው በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ  የታጀቡ ነበሩ።

ህገመንግስታችን የቆየውን የአገራችንን የተዛባ  አካሄድ እንዲስተካከል በማድረጉ በአገራችን ዘላቂና ዋስትና ያለው ሰላም ማስፈን ተቻለ። ይህም በመሆኑ አገራችን ባለፉት 15 ዓመታት ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኤኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች ይህ ሌላው የአገራችን ትልቅ ስኬት ነው። አገሪችን በፍጥነት በሚባል መልኩ ከድህነት መውጣት ጀምራለች። በእርግጥ አሁንም በርካታ ዜጎች በድህነት ውስጥ የሚኖር ቢሆንም  መንግስት በተከተለው ትክክለኛ  ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በርካታ ዜጎችን ከድህነት ማላቀቅ ተችሏል። የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ26 ዓመታት በፊት ከነበረበት ከአራት እጥፍ በላይ  ማሳደግ ተችሏል። በሁሉም የአገራችን ክፍል ተመጣጣኝ እድገት እንዲኖር መንግስት ጠንክሮ በመስራቱ  ከኢኮኖሚ እድገቱ ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኗል።

ባለፉት 26 ዓመታት ማህበራዊ መገልገያዎች መስፋፋት ማለትም በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል።  ትምህርት  ከፍተኛ  ለውጥ የታየበት ዘርፍ ነው።  በትምህርት ላይ ማለትም ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ከ28 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ይገኛሉ። በፌዴራል መንግስት ብቻ በዕትዕ ሁለት እየተገነቡ ያሉትን 10 ዩኒቨርሲቲዎችን ሳይጨምር አሁን ላይ ከ35 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን  በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ።   ዛሬ ላይ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት ብቻ ሳይሆን  ተማሪዎች በመረጡት የትምህርት መስክ ትምህርታቸውን  መከታተል እንዲችሉ  ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው። በጤናው ረገድም በአገራችን በርካታ ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ የዞን ሆስፒታሎች፣ ሪፈራል ሆስፒታሎች፤ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ፍተሃዊ በሆነ መንገድ መገንባት ተችሏል።

የአገሬ ስኬት የሆነውና ትኩረቴን የሳበው ጉዳይ  በአገራችን በፍጥነት እያደገ ያለው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ነው። አገሪቱ ፈርሳ እንደገና የምትገነባ እስክትመስል ድረስ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢውች በርካታ ግንባታዎች በመካሄድ ላይ ናቸው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ አድርገን የምናነሳት አዲስ አበባ ነች። አዲስ አበባ ፈርሳ የምተገነባ ከተማ ሆናለች። የቀድሞ ደሳሳ ቤቶች እየፈረሱ በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ማህበራዊ መገልገያዎች፣ የንግድ ተቋማት ወዘተ በመገነባት ላይ የገኛሉ። በአፍሪካ በጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ረገድ እንደኢትዮጵያ መንግስት ጥረት ያደረገ አንድም መንግስት አለ በዬ አላምንም። ይሁንና በአገራችን  የግንባታው ዘርፍ ከዜሮ ሊባል የሚችል ደረጃ የተነሳ በመሆኑ  አሁንም በአገራችን የግንባታው ዘርፍ ብዙ ስራ የሚጠይቅ ነው።

በመሰረተ ልማት ግንባታ ማስፋፋት በተለይ በመንገድ  ረገድም ሌላው የአገራችን ትልቅ ሰኬት ነው።  አገሪቱን ከጎረቤት አገራት የሚያገናኙ ትላልቅ አውራ ጎዳናዎች፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች (ኤርፖርቶች) ወዘተ በመካሄድ ላይ ናቸው።  በመንገድ ደረጃ  አርሶና አርብቶ አደሩን  ጥቅም ታሳቢ ያደረጉ ቀበሌዎችን ከቀበሌዎች፣ ቀበሌዎችን ከወረዳዎች ወዘተ የሚያገናኙ ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ መንገዶችን መገንባት ተችሏል። በከተሞች መሰረታዊ ለውጦች ተካሂደዋል። የአገራችን የኤኮኖሚ ዕድገት አብዛኛው ህዝብ የሚኖርበትን ገጠሩን መዓከል ያደረገ ስለሆነ ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል በሁሉም አካባቢ እንዲኖር አስችሏል። መንግስት የሃብት ክፍፍሉ ፍተሃዊ ለማድረግ በርካታ ሃብትን የሚያፈሰው መሰረተ ልማት በማስፋፋት፣ የትምህርትና ጤና ተቋማትን በመገንባት ላይ ነው። ይህ ተጨባጭ እውነታ ነው።

በትምህርትም ሆነ በጤና አገልግሎት ላይ የጥራት ችግር ቢኖርም በለፉት 26 ዓመታት አገራችን እነዚህን ዘርፎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከማደረግ አኳያ  ስኬታማ መሆን ችላለች። የሰው ሃብት ልማት ረገድ እነዚህ ሁለት ዘርፎች ያላቸው አስተዋጽዖ ወሳኝ በመሆኑ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኙ አድርጓል። በዚህም አሁን ላይ ብቻ ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ።

በአገሪቱ የተረጋጋ ሰላም በመስፈን መንግስት አገሪቱን ከድህነት ማውጣት የሚያስችሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ለተግባራዊነታቸው ርብርብ በማደረግ ላይ ነው። ለአብነት የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች፣ የሃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ በተለይ ከታዳሽ የሃይል አቅርቦት፣ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት፣ ወዘተ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ተችሏል። ይህ ለአገራችን ሌላው ስኬት ነው።

በእኔ እይታ ባለፉት 26 ዓመታት አገራችን ገጠሟታል ከምለው ተግዳሮቶች  መካከል አንኳር የሆኑትን ላንሳቸው። የመጀመሪያውና ትልቁ በ1983 ዓ.ም አምባገነኑ ደርግ ስርዓት ውድቀትን ተከትሎ በርካታ የታጠቁ አካላት አገሪቱን ለመቀራመት የተነሱበት ወቅት ነበር። በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  እኛ እኩልነትንና ነጻነትን ፍለጋ  ትግል አደረግን እንጂ  ለመለያየትና ለመበታተን አይደለም በሚል አዲሲቷን ኢትዮጵያ በአዲስ ቃልኪዳን እውን አድርጉ። አገሪቱ ሳትበታተን፣ የህዝብ እልቂትም ሳይከሰት የአገሪቱ አንድነትን ማስጠበቅ ተችሏል። ይህ  አገራችንን  ከገጠሟት የከፉ አደጋዎች መካከል ቀዳሚው ነበር ማለት ይቻላል። ያ አስከፊ  ወቅት  አልፎ ዛሬ ላይ አገራችን በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ያለባት አገር ለመሆን በቅታለች።

እንደኔ ሌላው አስቸጋሪ ወቅት የነበረው  የኤርትራ  ወረራ ወቅት ነበር። ከኤርትራ ወረራ ቀደም ባሉ ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግስት መንገድና ትምህርት ቤት ሲያስፋፋ፣ ድህነትን ለመቅረፍ ሲጣጣር  የኤርትራ መንግስት ግን የጦር መሳሪያዎችን ሲገዛና ወታደር ሲያሰለጥን ነበር። በወቅቱ የኤርትራ መንግስት ግምት የነበረው ኢትዮጵያ ተከፋፍላለች፣ ሉዓላዊነቷን ማስከበር አትችልም  በሚል ነበር። ይሀንና  የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአምባገነኑን የኤርትራን ጦር ከመሸገበት ጠራርገው እንዲወጣ አድርገዋል። በዚህም በአጭር ጊዜ   የአገሪቱን ሉዓላዊነት በማስከበር  ወደ ልማት መመለስ ተችሏል። ያ ክፉ ወቅትም  በስኬት ተደምድሟል።

የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ማብቃት ተከትሎ በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል ሌላው ለአገራችን ፈተና እንደነበር በርካቶች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። በአንዳንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ በተፈጠረው የስልጣን መባለግ ምክንያት በፓርቲው ውስጥ የመከፋፈል አደጋ ተጋርጦ የነበረ ቢሆንም ፓርቲው ባዳበረው ጥልቅ ግምገማ የተበላሸ  አመራሩን የሚስተካከሉተን በማስተካከል ያልሆነውን ደግሞ ቆርጦ በመጣል ኢህአዴግ ራሱን አደሰ።  

ኢህአዴግ ሁኔታዎችን በሰከነ ሁኔታ በመገምገም  አዳዲስ  ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን  መንደፍ  በመቻሉ  አገሪቱ ፈጣን  የኤኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ  ጀመረች።  ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አገራችን ባለሁለት አሃዝ እድገት በማስመዝገብ የህዝቦችን የቆየ የልማት ጥያቄዎች መመለስ ጀመረች። በዚህም አገራችን ዛሬ ላይ ፈጣን እድገት ማስመዝገብ ከቻሉ ጥቂት የአለማችን አገራት መካከል አንዷ ለመሆን ችላለች። ይህ ውጤት ኢህአዴግ በተከተለው ትክክለኛ መስመር ሳቢያ መመዝገብ የቻለ ነው።

ለአገራችን ፈታኝ የሆነ የምለው ሌላው ገጠመኝ የ97ቱን ምርጫ ተከትሎ የተነሳው ሁከት ነው። በወቅቱ ቅንጅት አጠቃላይ ምርጫውን ያሸነፍኩት እኔ ነኝ በሚል ያስነሳው ሁከት የበርካቶችን ህይወት ቀጥፏል፣ ንብረት አውድሟል እንዲሁም የአገራችንን የዴሞክራሲ ሂደት ከፉኛ ጎድቶታል።  ያ ወቅት ብዙዎች ለአገራችን አስቸጋሪ ብለው ቢሉትም መንግስት በብለሃትና አርቆ በማሰብ ሁኔታዎች እንዲበርዱና መልክ እንዲይዙ አድርጓል። መንግስት በተከተለው የሰከነ አካሄድ ሁኔታዎች ተረጋግተው አገራችን የጀመረችው ፈጣን የኤኮኖሚ ዕድገት ማስቀጠል ተችሏል።

ባለፈው ዓመት  ጀምሮ በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች የተነሱ ሁከቶች ሌላው ለአገራችን መልካም ያልሆኑ ነገሮች እንደሆኑ ማንሳት ይቻላል። እነዚህ ሁከቶች  መሰረታቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቢሆኑም አካሄዳቸው ግን  ጽንፍ የረገጠ እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ነው። የመልካም አስተዳደር ችግሮች በየትኛውም አገር የሚፈጠሩ ነገም የሚኖሩ መፍትሄም የሚሰጣቸው በሂደት እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው። ከዚህም ባሻገር የመልካም አስተዳደር ችግሮች በነውጥና ሁከት ምላሽ ሊያገኙ አይችሉም።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት የመልካም አስተዳዳር ችግሮች የአንድ ወቅት ክስተቶች አይሆኑም። የዴሞክራሲ ባህላችን እየዳበረ  በሄደ ቁጥር  ጠያቂ ህብረተሰብ ይፈጠራል፤  ጠያቂ ህብረተሰብ ደግሞ  ትንሽም ቢሆን መብቱን  መስጠት አይፈልግም።  የመልካም አስተዳደር  ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በሁከትና ብጥብጥ ሳይሆን  በመቀራረብና በመነጋገር ብቻ ነው። በአገራችን የሰላማዊ ትግል ሜዳ ተመቻችቷል። ይሁንና የሰላማዊ ትግል ባህል መጎልበት ይቀረዋል።  ይህን  የሰላማዊ የትግል ባህላችንን ማጎልበት የህብረተሰቡ የቀጣይ የቤት ስራ መሆን መቻል አለበት። በየትኛውም መስፈርት ቢሆን በነውጥና በሁከት ወደ መንግስት ስልጣን መምጣት  አይቻልም። እንዲህ ያለ አካሄድን በህገመንግስታችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘግቶታል።  የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን መፍታት ወይም መፍትሄ ማፈላለግ የመንግስት ሃላፊነት  ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡም  ጭምር ነው። አሁንም  መንግስት  ከህዝቡ  የተነሱ  የመልካም አስተዳዳር ችግሮችን  እልባት  በመስጠት ለዴሞክራሲ ስርዓቱ  መጎልበት   መጠቀም ይቻላል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy