NEWS

ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች በቂ ዝግጅት በማድረግ በራስ መተማመናቸውን ሊያዳብሩ ይገባል

By Admin

May 21, 2017

ሕይወት ገረመው በአዲስ አበባ እንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ለመፈተን በዝግጅት ላይ ነች፤ ጥሩ ውጤት ለማምጣት በትጋት እያጠናች መሆኗን ትናገራለች።

ስለ ዝግጅቷ ለኢዜአ አስተያየት የሰጠችው ተማሪዋ ከሦስት ነጥብ በላይ በማምጣት ለማለፍ እየተዘጋጀች መሆኗንና የወላጆቿና መምህሮቿ እገዛ እንዳልተለያት ገልፃለች።

”ወላጆቼ ፈተናውን ሳልጨናነቅ እንድሰራና በራስ መተማመኔ እንዲዳብር በምክር እየደገፉኝ ነው” ያለችው ህይወት ሌሎች ተማሪዎችም ጊዜያቸውን ለጥናት በማዋል ለፈተና መዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግራለች።

ተማሪ መቅደስ ነገሰና ተማሪ በረከት አዘዘም በህይወት ሃሳብ ይስማማሉ ተማሪ የጥገኝነት ስሜትን በማስወገድ በራሱ የሚተማመንና የሚሰጠውን ፈተናም በራሱ የሚሰራ መሆን እንዳለበትም አስተያየት ሰጥተዋል።

የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ የሆነው ተማሪ አብድልቃድር ዳምጤም “ኩረጃ ይቅር” በሚል መሪ ሀሳብ በትምህርት ቤቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ መደረጉን ተናግሯል።

ሁሉም ተማሪ ፈተናውን በራሱ ጥረት ለማለፍ መስራት እንደሚኖርበትም አስተያየቱን ሰጥቷል።

የኮከበ ፅባህ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሺመላሽ ዘውዴ ትምህርት ቤቱ 1 ሺህ 143 የ12ኛ እና የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን እንደሚያስፈትን ነው የተናገሩት።

በፈተና ወቅት የሚታየውን ኩረጃ ለመከላከልና ለማስቀረት የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

የእንጦጦ አምባ ሁለተኛ ደረጃ ትህምርት ቤት የመምህራን ልማት ምክትል ርዕሰ መምህርት ወይዘሪት ሰናይት ኃይሉ በበኩሏ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን ለብሄራዊ ፈተና ማዘጋጀት የጀመረው ከመስከረም ጀምሮ መሆኑን ገልፃለች።

በትምህርት ቤቱ ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎች ብሄራዊ ፈተና እንደሚወስዱና ኩረጃን እንዲፀየፉና በራሳቸው ውጤት እንዲኮሩ ለማድረግ በሚኒ ሚዲያና ክበባትን በመጠቀም ገለፃ መደረጉን ተናግራለች።

የራዲካል አካዳሚ ትምህርት ቤቶች አስተባባሪ ዳይሬክተር አቶ ሀጎስ ኃይሉም ትምህርት ቤቱ 384 ተማሪዎችን ለ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ማዘጋጀቱን ገልፀዋል።

የዘንድሮው የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከግንቦት 23 እስከ 25 እንዲሁም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ከግንቦት 28 እስከ ሰኔ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ይሰጣል።

በአገሪቷ 288 ሺህ 626 የ12ኛ እንዲሁም 1 ሚሊዮን 206 ሺህ 839 የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተናውን ይወስዳሉ።