Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ብረት ያልረታው ህዝብ እንዴት በድህነት ይረታል?

0 455

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ብረት ያልረታው ህዝብ እንዴት በድህነት ይረታል?/ብ. ነጋሽ/

ኢትዮጵያውያን በ1988 ዓ/ም ሃገራቸውን በቅኝ ግዛትነት ለመያዝ የሰለጠነ፣ የዘመኑ ቴክኖሎጂ የደረሰበትን የላቀ የጦር መሳሪያ የታጠቀና የተደራጀ ባለሞያ ሰራዊት አስለፎ ቀይ ባህርን ተሻግሮ የዘለቀውን የጣሊያን ሃይል በመመከት ነጻነታቸውን ማሰጠበቅ የቻሉ ህዝቦች ናቸው፤ በአድዋ ድል። ይህ ታሪካዊ የአድዋ ድል የኢትዮጵያወያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝቦች፣ ከዚህም አልፎ በነጭ አውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ህዝቦች ድል ነበር። በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር ወድቀው የነበሩ የአፍሪካ፣ የካራቢያን፣ የኢሲያ ሃገራት ህዝቦችን ለትግል አነሳስቷል። የጸረ ቅኝ ግዛት የነጻነት ትግልን ለኩሷል፤ የአድዋ ድል።

በአድዋ ጦርነት ድል የተነሳው የጣሊያን ቅኝ ገዢ ወራሪ ሃይል፣ ከመረብ በታች ላለችው ኢትዮጵያ ነጻ መንግስትነት እውቅና ሰጠ። ከራስ ዱሜራ እስከራስ ካዛር ያለውን የቀይ ባህር ዳርቻ ጨምሮ ኤርትራ የጣሊያን ቅኝ ግዛት ሥር ወደቀች። የጣሊያን መንግስት ከኤርትራ በተጨማሪ በምስራቅ አፍሪካ ከፊል ሶማሌን እንዲሁም በሰሜን አፍሪካ ሊቢያን ይዞ ነበር።

ታዲያ በአድዋ ጣርነት ድል የተነሳው የጣያን መንግስት ልክ በ40ኛ ዓመቱ በ1928 ዓ/ም የዓለም መንግስታት ሊግ አባል የነበረችውን ነጻይቱን ኢትዮጵያ ወረረ። የጣሊያን መንግስት የመንግስታቱን ሊግ ስምምነት ጥሶ ኢትዮጵያ ላይ ወረራ እንዲፈጽም ያደረገው የአድዋውን ውርደት በመካስ በምስራቅ አፍሪካ ታላቅ የጣሊያን ግዛት ለመመስረት ነው። የጣሊያን ብሄራዊ ፋሺስት ፓርቲ መስራችና መሪ እንዲሁም እ ኤ አ ከ1922 እስከ 1943 ዓ/ም የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ቤንቶ ሞሶሎኒ በሃገር ውስጥ የገጠመውን የፖለቲካ ኪሳራ በዓለም አቀፍ ስኬት ለመካስ የፈጸመው ወረራ ነው የሚሉም አሉ። ያም ሆነ ይህ ነጻይቱ ኢትዮጵያ በብሄራዊ ፋሽስት ፓርቲ ይመራ በነበረው የጣሊያን መንግስት ወረራ ተፈፅሞባታል።

ከአድዋ ድል በኋላ በነበሩት አርባ ዓመታት በጣሊያን ሃይል አሰላለፍ ላይ የበለጠ ጥንካሬ ታይቷል። በአድዋው ጦርነት ተዋጊ አውሮፕላን ያልነበረው የጣሊያን ሃይል በ1928 ዓ/ም ወረራ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን ታጥቆ ነበር። የኢትዮጵያ ሃይል በወታደራዊ ትጥቅና ድርጅት አቅሙ በአድዋ ከነበረው ይሻላል ሊባል ቢችልም፣ የጣሊያን ሃይል ካሳየው የአቅም መጠናከር ጋር ሲነጻጸር ግን በነበረበት ነው የቆየው ማለት ይቻላል። እርግጥ ኢትዮጵያ ጥቂት የሰለጠነና የተደራጀ ባለሞያ ሰራዊት ነበራት። ይህ ሃይል ግን ከጣሊያን አቅም ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም።

ጣሊያን ዳግም የኢትዮጵያን በወረረበት በ1928 ዓ/ም የነበረችበት ፖለቲካዊ ሁኔታም በ1888 ዓ/ም ከነበረው በእጅጉ የተለየ ነበር። በ1988 ዓ/ም በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ስር በአሃዳዊ ስርአት መተዳደር የጀመሩ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በንጽጽር ሲታይ በራሳቸው ነባር ስርአትና መሪዎች የሚተዳደሩበት ሁኔታ ነበር። አንጻራዊ ነጻነት ነበራቸው ማለት ይቻላል። በዚህ ምክንያት የጣሊያን ሃይል ወረራ ሲፈጽም በራሳቸው የአካባቢ መሪ ስር ተሰልፈው ለመዝመት ከመነሳት እንዲያቅማሙ ያደረጋቸው ምክንያት አልነበረም። በዚህ ምክንያት ከመላው ኢትዮጵያ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሃይል ማሰለፍ ተችሏል።

በ1928 ዓ/ም ግን ይህ ፖለቲካዊ ሁኔታ አልነበረም። የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አሃዳዊ መንግስት የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ከ40 ዓመታት በፊተ የነበራቸውን አንጻራዊ በራሳቸው የመተዳደር ነጻነት አሳጥቷቸው ነበር። “በባእዳን” የመተዳደር ሰሜት ስላደረባቸው፣ በማዕከላዊ የንጉሰ ነገሥቱ መንግስት ክተት ለዘመቻ ሊነሱ አልቻሉም። እናም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከተት አውጀው ጣሊያንን ለመግጠም ወደ ማይጨው ሲዘምቱ አብሯቸው የተሰለፈው ሃይለ እንደአድዋው ከሁሉም የሃገሪቱ ማእዘን ‘ሆ’ በሎ የተመመ መሬት የሚያርድ አልነበረም።

ከላይ የተገለጹት የጣሊያን ወራሪ ወታደራዊ ሃይል አቅም እጅግ መበርታትና በኢትዮጵያ የነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ተዳምረው የጣሊያን ወራሪ ሃይል በቀላሉ አሸንፎ አዲስ አበባ መግባት የሚችልበትን እድል ፈጥሮለታል።

ይህ ግን የፋሺስት የጣሊያን መንግስት እንዳሰበው ኢትዮጵያንም የሚያካትት የምስራቅ አፍሪካ ታላቅ ኢምፓየር መመስረት አላስቻለውም። ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያቸው በየራሳቸው አዛዦች እየተመሩ የጣሊያንን ሃይል አላንቀሳቀስ አሉ። ጣሊያን ለስሙ ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ ግዛቴ አካል አድርጌያለሁ ብሎ ያውጅ እንጂ፣ ሃገሪቱን በወጉ ማስተዳደር ግን አልቻለም። ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያ ግዛቴ ነች የሚለው አዋጁ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትም አላገኘም ነበር። ኢትዮጵያ የጣሊያን ቅኝ ግዛት አካል መሆኗን የተቀበሉት የጀርመንና የጃፓን መንግስታት ብቻ ነበሩ። እርግጥ ሁሉም የአወሮፓ ሃገራት ኢትዮጵያ ለመንግስታቱ ሊግ ያቀረበችውን የሊጉ ስምምነት ተጥሶ ተወርሬያለሁ ለሚል አቤቱታ ጆሮ የመስጠት ፍላጎት አልነበራቸውም።

ያም ሆነ ይህ፤ ኢትዮጵያውያን በአርበኝነት ሽምቅ ውጊያ ጣሊያንን ፋታ ያሳጡት ያዙ። የአርበኝነት ትግሉን ለመግታት የወሰዳቸው የግፍ እርምጃዎችም ሆኑ የዲፕሎማሲ ሙከራዎች ትግሉን ከማባስ ያለፈ ጥቅም ሊያስገኙለት ሳይችሉ ቀሩ። በኋላ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአሜሪካ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ቻይና ህብረት እና ከዚህ በተጻራሪ የተሰለፈው የጀርመን፣ ጣሊንና ጃፓን ህብረት መሃከል የተፈጠረው ፍጥጫ በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ አዲስ እድል ፈጠረ። በዚህ ፍጥጫ የአምስቱ ሃገራት ህብረት በጣሊያን ቅኝ ግዛቶች ላይ በሙሉ ሃይላቸውን አዘመቱ። እናም የህብረቱ አባል የሆነችው እንግሊዝ ሃይሏን ወደኢትዮጵያ ጣሊያን አዘመተች። ይህ የእንግሊዝ ሃይል በሃገር ውስጥ ሲንቀሳቀስ በነበረው አርበኛ እየታገዘ ጣሊያንን በቀላሉ ከኢትዮጵያ ማስወጣት አስቻለ። አናም ኢትዮጵያውያን አርበኞች የዛሬ 76 ዓመት የፋሺስት ጣሊያን ወራሪ ሃይል ላይ ዳግም ድል በመቀዳጀት ነጻነታቸውን ዘላቂ ማድረግ ቻሉ። ሰሞኑን ያከበርነው የነጻነት ቀን ይህ ድል የተዘከረበተ ነው።

በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ በራስዋ ልጆች መስዋዕትነት ነጻነቷን ጠብቃ የዘለቀች ብቸኛ የአፍሪካ ሃገር ለመሆን በቃች። ይህ የኢትዮጵያ አውሮፓዊ ወራሪን ተዋግቶዳግም ድል የመንሳት አቅም፣ የአደዋ ድል በአወሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ህዝቦች ላይ ፈጥሮት የነበረውን የነጻነት ትግል ተነሳሽነት አደሰ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ከመሰረቱ ነጻ የዓለማችን ሃገራት መሃከል አንዷ ነበረች።

ኢትዮጵያውያን ነጻነታቸውን ጠብቀው በመቆየት አኩሪ ታሪከ መጻፍ የቻሉ ህዝቦች መሆናቸው ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ የገናና ሃገር ባለቤት ሊያደርጋቸው አልቻለም። ይህ የሆነው በውጭ ወራሪዎች ላይ በተገኘ ድል የተገኘው ነጻነት ከዘውዳዊ ፊውዳላዊ ስርአት ጭቆና ማላቀቅ አለመቻሉ ነው። ፊውዳላዊው ዘውዳዊ ስርአት በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ላይ ከጫነው ፖለቲካዊ ጭቆና በተጨማሪ፣ የሚከተለው ፊውዳላዊ የኢኮኖሚ ስልት ኢኮኖሚውን ማሳደግ አልቻለም። የሃገሪቱን መሬት በርስትና ጉልትነት የያዙት መሳፍንትና መኳንንት ባለሃገሩን ጭሰኛ አድርገው እያስገበሩ ከመኖር ውጭ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያመጣ ማድረግ የሚያስችል ሃገራዊ የካፒታል ክምችት የመፍጠርና ኢንቨስትመንትን የማስፋፋት ፍላጎት አልነበራቸውም። ዋነኛ ፍላጎታቸው የመሬት ይዞታቸውን ማረጋገጥ ብቻ ነበር። ይህ የፊውዳሊዝም ባህሪ ነው።

ይህ የዘውዳዊ ስርአት ጭቆና በህዝብ ትግል ቢገረሰስም፣ ትግሉ የተደራጀ ስላልነበረ ስልጣን በህዝብ እጅ ከመግባት ይልቅ ያንኑ ዘውዳዊ ስርአት ሲያገለግል በነበረው ወታደራዊ ሃይል እጅ ወደቀ። ወታደራዊው ሃይል በመሬት ለአራሹ አዋጅ ባለሃገሩ አርሶ አደር ባለመሬት እንዲሆን ቢያደርግም፣ አርሶ አደሩ በላቡ ያገኘው ምርት ላይ ሙሉ የባለቤትነት መብት አልነበረውም። ከዚህ በተጨማሪ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችል ምንም የልማት ስራ አላከናወነም። በዚህ ምክንያት በኢኮኖሚው ውስጥ የመዋቅር ሽግግር ማምጣት የሚያስችል የካፒታል ክምችት መፍጠር የሚያስችል ሁኔታ አልነበረም።

እናም የአውሮፓ ወራሪዎችን ድል ነስቶ ነጻነታቸውን ያረጋገጡት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረቦችና ህዝቦች ከራሳቸው አምባገነኖች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና ነፃ መውጣት ያልቻሉ ደሃ ሆኑ። ባለጸጋ ሃያላኑን ምዕራባውያን ያንበረከኩት ኢትዮጵያውያን ለድህነት ተነበረከኩ፤ ድህነት ከሰው በታች አድርጎ አዋረዳቸው፤ በምእራባውያን ፊት ተመጽዋች ሆኑ። ብረት ያላሸነፈውን ህዝብ ድህነት አሸነፈው።

እናም የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም የነጻነት ትግል ይቀረዋል። ድህነትን ተዋግቶ የማሸነፍ፣ ከድህነት ነጻ የመውጣት ትግል ይቀረዋል። አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ – ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች፣ ህዝቦችና መንግስታቸው  በድህነት ላይ ክተት አውጀው ከዘመቱ ሁለት አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል። ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ድህነትን እየረቱ ኑሯቸው መሻሻል ጀመሯል። ይህን ስኬታቸውን ዓለም መስክሮላቸዋል። በብረት ያልተረታው ህዝብ በድህነት ላለመረታት እየታገለ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይ ወጣቱ ትውልድ አዋራጁን ድህነት ረትቶ ነጻነቱን የማረጋገጥ ጉዳይ የምርጫ ሳይሆን ከነጻነቱ ጋር የሚስተካከል የህልውና እና የብሄራዊ ክብር ጉዳይ መሆኑን መረዳት አለበት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy