CURRENT

ተባብረን ካልሰራን ለውጥ አናመጣም›› – ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ

By Admin

May 06, 2017

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በሰላም ፣ በደህንነትና በልማት ጉዳዮች ተባብረው ካልሰሩ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደማይችሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ ለስራ ጉብኝት ትናንት አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ፕሬዚዳንቱን በብሄራዊ ቤተመንግስት ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንደገለፁት፤ አገራቱ በሰላም፣ በደህንነትና በልማት ጉዳዮች ከዚህ ቀደም ከነበረው በላቀ ደረጃ ተቀራርበው ካልሰሩ የሚፈለገውን ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ በተለይም የአገራቱ ግንኙነት በማጠናከር አብረው መስራታቸው የቀጣናውን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ ያግዛል፡፡

አክራሪነትና ሽብርተኝነትን እንዳይስፋፋ የተጠናከረ ጥረት ለማድረግ መስማማታቸውን አቶ ኃይለማርያም ጠቁመው፤ በተለይም የሶማሊያን የአገር ውስጥ መከላከያ አቅም ማጠናከር እንደሚያስፈልግም መምከራቸውን አመልክተዋል፡፡ በዋናነትም የሶማሊያን ሰላም ለማጠናከር ይቻል ዘንድ ኢትዮጵያ ድጋፏን እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ድህነትን ለመቀነስ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አቶ ኃይለማርያም ጠቁመው፤ በዚህ ረገድም አገራቱ አስተማማኝ ልማትን ለማምጣትና ድህነትን ለመቀነስ በሚያስችሉ እንደ ትምህርት፣ መሰረተ ልማት የመዘርጋት ስራዎች በጋራ መስራት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ከፕሬዚዳንቱ ጋር መወያየታቸውን አስገንዝበዋል፡፡

በኢኮኖሚ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጎልበትም ከአንዱ አገር ወደ ሌላው የሚደረገውን ጉዞ ቀላል ማድረግ የአየርና የየብስ ጉዞን ቀልጣፋና ምቹነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ጠቁመዋል። ይህም ትልቅ የኢኮኖሚና የንግድ ትስስርን እንደሚፈጥርና የኢትዮጵያ ባለሀብቶች በሶማሊያ የሶማሊያም በኢትዮጵያ ለመሰማራት እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ሶማሊያ የግብርና፣ የውሃ እና የቀንድ ከብት ሀብቷ አልተሰራበትም፡፡ ይህን በመጠቀም የሶማሊያን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በጋራ መስራት ያስፈልጋል። ሶማሊያ በተማረ የሰው ሀይል አቅሟን እንድታጠናክርም ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን እንደምትልክ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የምታደርገውን ጥረት በማድነቅ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀዋል። በተለይ በሁለቱ አገራት ላይ እየተከሰተ ያለው ረሀብ አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል። እንዲሁም ሁለቱ አገራት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ መወያየታቸውንና በማንኛውም ጉዳይ ላይ በቅርብ ለመነጋገር እንደተስማሙም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም አገሮቹ ድህነትን በመዋጋት የህዝቦችን የኑሮ ደረጃን ከፍ ለማድረግ እንደሚሰሩም ገልፀዋል። ለዚህም እንዲያግዝ በአገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ በማሳደግ የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል በማንኛውም ዘርፍ አብረው እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

ሰላማዊት ንጉሴ