NEWS

ቻይና ለአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ 260 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሰጠች

By Admin

May 19, 2017

ቻይና ለአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ 260 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሰጠች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የተመራ የልዑካን ቡድን ከግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በቻይና የተለያዩ ግዛቶችን በመጎብኘት ላይ ነው።

ከቻይና ኤግዚም ባንክ በብድር የተገኘው ገንዘብ በአዳማ ከተማ ለሚገነባው ኢትዮ – ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚውል ነው።

ብደሩ የተገኘው በሁለቱ ሀገራት መሪዎች በተፈረመ የሁለትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ መሰረት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በብድር ስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ፓርኩ የከባድ ማሽኖች፣ የኃይል ቁሳቁሶችን የሚያመርትና ለአገሪቷ ልዩ ሊሆን የሚችል ነው።

በተለይም ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችላት ልዩ ፓርክ እንደሚሆን ነው የገለጹት።

“የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት፣ የሃይል ማመንጨትና ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ፣ በማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ልማትና የቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግርን ከመፍጠር አኳያ አስደናቂ ስራ እያከናወኑ ነው” ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከሁናን ግዛት በዘመናዊ ግብርና፣ የኢንዱስትሪ ሽግግር እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ልምድ እንደምተቀስም ነው የተናገሩት።

የቻይናዋ ሁናን ግዛት በቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሺዬቲቭ አማካኝነት በአለም አቀፍ ቀላልና ዘመናዊ የትራንስፖርት ስርዓት ዘጠኝ ፓርኮችንና 11 ቢሮዎችን ትከፍታለች።

የሁናን ግዛት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የተለያዩ ማበረታቻዎች የቀረቡላቸው ሲሆን፤ እኤአ 2016 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች የ180 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ማካሄዳቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።