Artcles

ነጻነትን የሚንከባከባት መገፋትን የሚያውቅ ነው!

By Admin

May 15, 2017

ነጻነትን የሚንከባከባት መገፋትን የሚያውቅ ነው!

አባ መላኩ

ግንቦት 20  ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የነጻነትና የእኩልነት አምድ ናት። ግንቦት 20 ብዝሃነትን ያከበረ አዲስ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በአገራችን እንዲገነባ መሰረት የሆነች ዕለት ናት። ይህች ዕለት በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲገነባ፤ የዜጎች መብት ህገመንግስታዊ ዋስትና እንዲያገኝ ያስገኘች እለት ናት።  አገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማግኘት በመቻሏ  ህዝብና መንግስት ትኩረታቸውን ወደልማት ማድረግ  በመቻላቸው ባለፉት 26 ዓመታት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው  ኢኮኖሚያዊ  ስኬቶች  ማስመዝገብ ችለዋል።  

ኢትዮጵያ የብዙ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር ናት።  አንድነት ተብሎ ስለተጮኸ አንድነት ሰፍኗል ተብሎ ስለተዘመረ ብቻ እውነተኛ አንድነት ስፍኖ ነበር ብሎ ማለት አይቻልም።  አዎ! የሃይል አንድነት፣ የሌላውን ስብዕና ያላከበረ አንድነት፣ ህዝቦች መብታቸውን ያጡበት አንድነት ትንቡሽት ላይ እንደተገነባ ቤት ዘለቂታ  ሊኖረው አይችልም።   የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የባህል ብዝሃነት ባላት ሀገር ውስጥ ይህን የማይቀበል የፖለቲካ ስርዓት  እነዚህን ታሳቢ ካላደረገ አንድነት ዘለቄታዊነት እንደማይኖረው  ያለፉት የኢትዮጵያ ስርዓቶች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። ሰው በግድ ይህ ነህ ወይም እንዲያ ነህ ስለተባለ የታሰበው  ወይም የተፈለገው ነገር መጥቷል ማለት አይቻልም።

በሃይል አንድ ናችሁ ወይም በሃይል አንድ ነን በሉ የተባሉት ህዝቦች   በየአካባቢያቸው እየተደራጁ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው መከበር ወደ ትጥቅ ትግል እንዲገቡ ተገደው ነበር። የእርስ በርስ ጦርነቱ ኢኮኖሚውን ክፉኛ ስለጎዳውም  ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የማትመች፣ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ደግሞ እንደምድረ ሲዖል ትቆጠር ነበር። ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ይህን ችግር ስርነቀል በሆነ መልኩ ለመፍታት  መሰረት የተጣለባት ቀን ናት። ግንቦት 20 የህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የአገሪቱ አንድነት መሰረት የተጣለበትና ህዝቦች በእኩልነት ላይ ለተመሰረተ አንድነት ማቀንቀን የጀመሩበት ዕለት ናት።

ረሃብን የሚያውቃት የተራበ  ብቻ ነው እንደሚባለው ሁሉ ጭቆናን የሚያውት የተጨቆነና የተገፋ ብቻ ነው። ነጻነትንና እኩልነትን ለማጣጣም ቀድሞ  የነበረውን ሁኔታ  ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል።  ባለፉት ስርዓቶች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጭቆና ውስጥ ሲማቅቁ ነበር፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንበት ሁኔታ አብቅቷል።  ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች ስለነጻነትና እኩልነት  መስካሪዎች  ለመሆን በቅተዋል።

በደርግ ውድቀት አካባቢ ከ17 በላይ የታጠቁ በብሔር የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ይንቃቀሱ ነበር። ደርግም በእነኚህ ኃይሎች ተወጥሮ የሀገሪቷን አንድነት በኃይልም ሆነ በሌላ አማራጭ የሚያስጠብቅበት ዕድል ተሟጦበት ስለነበር መሪው አገርንና ህዝብን ጥሎ ከመሸሽ ውጭ አማራጭ አልነበረውም።  በዚያን ወቅት በርካቶች ኢትዮጵያ አበቃላት ልትበታተን ነው፤  በሚሉበት ሰዓት  የኢትዮጵያ ህዝቦች በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነትን አሳይተዋል። ህዝቦቿ ብዝሃነትን የምታስተናግድ  አዲሲቷን ኢትዮጵያ እውን አደረጉ።

የግንቦት 20 ለኢትዮጵያ አንድነት ዋስትና የሰጠች ዕለት ናት።  ሁሉንም ህዝቦች በእኩልነት የሚመለከት አዲስ የፖለቲካ ስርዓት በመገንባት የሀገሪቱን ህልውና ያስቀጠለች ዕለት ናት። ግንቦት 20 በከፋ ጭቆና ውስጥ ይማቅቁ የነበሩ ህዝቦች ማንነታቸው  እንዲከበር ባደረጉት ጥረት ከሌላው ጋር  ዕኩል መሆናቸው በአደባባይ ያረጋገጡበት  ዕለት ናት። ግንቦት ሃያ  የኢትዮጵያ ህዝቦች  ዕርስ በርስ ተከብሮ በጋራ የሚኖሩበት ስርዓት መፍጠር እንደሚቻል  ያሳዩበት ዕለት ናት።

ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብቶቻቸው  የህገመንግስታዊ  ዋስትና ያገኙባት  ዕለት ናት። ህገመንግስቱ በእነኚህ ህዝቦች ሙሉ ፈቃድ የፀደቀ የአንድነታቸውና የአብሮነታቸው ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ  ህዝቦች ፍላጎታቸውንና እምነታቸውን የገለፁበት፣ በአዲስ መንፈስ የጋራ ግንባር ፈጥረው፣ ተከባብረውና ተጋግዘው አብረው ለመኖር ቃል የገቡበት የአብሮነትና የአንድነት  የቃልኪዳን ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ አንድ የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር ቃል የተገባበት፣ ጭቆና ዳግም ሊመጣ እንዳይችል ተደርጎ የታሰረበት ውል የጸደቀበት ነው። ህዝቦች በማንኛውም ጉዳይ የመወሰን ሙሉ መብት ያገኙበት ማረጋገጫ ነው።

የህገመንግስቱ ዋና መርሆ የህዝቦች የስልጣን ባለቤትነትን  ማረጋገጥ ነው። የግንቦት 20 ድል የተዛቡ ታሪካዊ ገፅታዎች እንዲስተካከሉም ያስቻለ ነው። ትላንትን፣ ዛሬንና ነገን የሚያገናኝ የህግና የፖለቲካ ሰነድ በሆነው ህገመንግስት ይህ ትውልድ ካለፈው የተረከባቸው ችግሮችን መፍታት ችሏል። መብቶች ሁሉ ለሁሉም ህዝቦችና ቡድኖች በእኩልነት እንዲከበሩ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። ለዚህ እንዲረዳም በታሪክ የተከሰቱ ችግሮችን ለትምህርት እንዲሆኑ በግልፅ ተቀምጧል። ህገመንግስቱ በመግቢያው ላይ “መጪው የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ነው” ያለው ይህን ለማመላከት ነው።

የግንቦት 20 ድል መንግስት የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎች እንዲከተል የሚያስገድድ ስርዓት የፈጠረ ነው። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ መንግስት በመንግስትነቱ ሊቀጥል የሚችለው የህብረተሰቡን ፍላጎት ማሳካት እስከቻለ ድረስ ብቻ ነው።  ዜጎች ከራሳቸው በሚመነጭ ስልጣን መሪዎቻቸውን ለመሾም አሊያው ለማውረድ የሚችሉበት ስርዓት እውን አድርገዋል።  የግንቦት 20  ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለማረጋገጥ መሰረትና ዋስትና መሆን የቻለች ዕለት በመሆኗ በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ አላት።

በግንቦት ሃያ  ዜጎች ኢኮኖሚያዊ  ጠቀሜታ  ማግኘት ችለዋል።  ባለፉት 15 ዓመታት የአገሪቱ  ኢኮኖሚ በየዓመቱ ባለሁለት አሃዝ  ዕድገት ማስመዝገብ  ችሏል። ይህ ዕድገት በተመሳሳይ  ደረጃ ላይ ከሚገኙ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር እጥፍ ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት በሪፖርታቸው አረጋግጠዋል። የአገራችን  ዕድገት በህዝባችን ላይ ተጨባጭ የህይወት ለውጥን አምጥቷል። በከተማም ሆነ በገጠር ህዝቦች በየደረጃው ከዕድገቱ ፍተሃዊ ተጠቃሚነታቸውን አረጋግጠዋል። የአገራችን አጠቃላይ የአገር ውስጥ ገቢ (ጂዲፒ) ከ72 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ መገንባት ችላለች። ድህነትን ከግማሽ በላይ መቀነስ ተችሏል።

የሀገራችን ዓመታዊ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ አሁን ላይ ወደ 800 የአሜሪካ ዶላር ደርሷል። ይህ በዚሁ ከቀጠለ በ2017 ዓ.ም ሀገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ የተቀመጠውን ግብ ማሳካት የሚያስችል ነው። ይህ ዕድገት በዋናነት ከግብርና ዘርፍ የመነጨ በመሆኑ ከዕድገቱ አብዛኛው ህዝብ ተጠቃሚ መሆኑን ያሳያል። በዚህም የድህነት ምጣኔው በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ወደ 23.4 ከመቶ ዝቅ እንዳለ ጥናቶች አመላክተዋል። ይህም ድህነትን በግማሽ መቀነስ የሚለውን የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ማሳካት ያስቻለን አፈፃፀም ነው።  በኢትዮጵያ የሃብት ክፍፍሉ ፍተሃዊነትን ለማረጋገጥ መንግስት  ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው። የመንገድ ግንባታ፣ የትምህርት ተቋም ማስፋፋት፣ የጤና አገልግሎት አቅርቦት፣ የኤሌክትሪክ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በማሳደግ ረገድ የኢፌዴሪ መንግስት ትልቅ ስኬት አስመዝግቧል። ይህ ሁሉ የግንቦት ሃያ ድል ውጤት ነው። ግንቦት ሃያ ለተጨቆኑ የኢትዮጵያ ህዝቦች መድህን ናት። በመሆኑም ግንቦት ሃያ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዋስትና በመሆኗ  በብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዘንድ  ልዩ ስፍራ ያላት ዕለት ናት።