NEWS

አቃቢ ህግ በዶክተር መረራ መቃወሚያ ላይ ምላሽ ሰጠ

By Admin

May 04, 2017

ዶክተር መረራ ጉዲና በተከሰሱበት የሸብር ወንጀል ባቀረቡት 11 ገጽ መቃወሚያ ላይ ዛሬ አቃቢ ህግ መልስ አሰማ።

ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዶክተር መረራ ባቀረቡት ባለ 11 ገጽ መቃወሚያ፥ በዋናነት ክሳቸው ከእነ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ክስ ተነጥሎ ሊታይ ይገባል በማለት ባቀረቡት መቃወሚያ ላይ መልሱን አሰምቷል።

በዚህም አቃቢ ህግ የጋራ ግብ፣ አላማና ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ ክሱ ሊነጠል አይገባም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ከዚህ ባለፈም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መተላለፋቸውን በምላሹ ጠቅሷል።

በአጠቃላይ መቃወሚያው የወንጀል ስነ ስርዓቱንና ህጉን ያልተከተለ መቃወሚያ መሆኑን በአምስት ገጽ አያይዞ አስተያየት አቅርቧል።

አስተያየቱን የተከታተለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ የወንጀል ችሎት፥ ዶክተር መረራ ያቀረቡትን መቃወሚያ እና የአቃቢ ህግን አስተያየት መርምሮ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 25 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ዶክተር መረራ ጉዲና በተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ላይ ባለፈው የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም የክስ መቃወሚያቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል።

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ የወንጀል ችሎት ያቀረቡት መቃወሚያ፥ በዋናነት ዶክተር መረራ“ ክሴ ከእነ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እና ጃዋር መሀመድ ጋር አብሮ ሊታይ አይገባም፤ የእኔ የህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሊቀ መንበርነት ከእነሱ አላማና አፈጻጸም ጋር የማይገናኝ በመሆኑ ሊነጠል ይገባል“ ይላል።

“ቤልጂየም ብራስልስ ለህዝባዊ ስራ ነው የሄድኩት፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቁጥር 11/2009 ዓ.ም መሰረት ኮማንድ ፖስቱ ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መመሪያ አንቀጽ 2/1 ስር የተመለከተውን ተላልፏል የተባለውን እቃወማለሁ“ ሲሉም በመቃወሚያቸው ጠቅሰው ነበር።

“በ2008 እና 2009 ዓ.ም በአማራና በኦሮሚያ ክልል ለተከሰተው ሁከት እና አለመረጋጋት እኔ ልጠየቅ አይገባም“ ሲሉም ተቃውሟቸውን አቅርበዋል።

“የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ተብሎ በሚጠራው ሚዲያ ላይ ስለ ኢሬቻም ሆነ የሁከት ጥሪ በሚመለከት ቃለ ምልልስ አላደረኩም“ ሲሉም የቀረበባቸውን ክስ ተቃውመዋል።

በአጠቃላይ በክሱ የወንጀል ስነስርአት ህግ ቁጥር 111፣ 112 እና 130 አንቀጾች ዝርዝር ነገሮች ይቀሩታል በማለት በ11 ገጽ አያይዘው ነበር ያቀረቡት።