Artcles

አገራችን መብቶችን የምታከብረው ሌሎች አካላትን ለማስደሰት አይደለም!

By Admin

May 02, 2017

አገራችን መብቶችን የምታከብረው ሌሎች አካላትን ለማስደሰት አይደለም! /ዳዊት ምትኩ/

     በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለስልጣን ሰሞኑን ወደ ሀገራችን እንደሚመጡ መዘገቡን ተከትሎ የተለያዮ መላ ምትች እየተሰነዘሩ ነው። እነዚህ መላ ምቶች የኢፌዴሪ መንግስት የዜጎቹን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያከብረው የውጭ ሃይሎችን ለማስደሰት አሊያም ዓለም አቀፍ ተቋማትን ከመፍራት የመነጨ አስመስሎ የሚቀርቡ ናቸው። መላምቶቹ የኢፌዴሪ መንግስትን ትክክለኛ ባህሪያት የሚያንፀባርቁ አይደሉም።

እንደሚታወቀው መንግስት አገራችን ውስጥ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እውን እንዲሆኑ ታግሏል፤ አታግሏል። እርግጥም በሀገራችን ውስጥ የተካሄደው ረጅም ጦርነት መነሻው የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመኖር በመሆኑና ይህ የሀገራችን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ በአሁኑ ወቅት በቂ ምላሽ በማግኘቱ ነው። ይህም መንግስት ገና ከጅምሩ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

ባለፉት 26 ዓመታት የተከናወኑት ተግባራት ለዚህ አባባል አስረጅ ናቸው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር ተደርጓል። ሰው በመሆናቸውም በሁሉም መስኮች በእኩልነት እንዲስተናገዱ ተደርጓል። ከሰብዓዊ መብቶች ውስጥ አንዱ መገለጫ የሆነው ልማት በሀገራችን ውስጥ ሲካሄድ እያንዳንዱ ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ የዕድገቱ ተሳታፊ ሆኗል። ይህም ሀገራችን ሰብዓዊ መብቶችን የምታከብረው የውጭ ተቋማትንና ሃይሎችን በመፍራትና እነርሱን ለማስደሰት ሳይሆን፤ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በሀገራችን ውሰጥ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ነው።

የኢትዮጵያ መንገስት የዜጎቹን ሰብዓዊ መብቶች ካላከበረ ሀገራዊ ሰላምን እውን ማድረግ እንደማይችል ይገነዘባል። ሰላም ካለተረጋገጠም የሀገራችን የህልውና ጉዳይ የሆነው ልማትን ማስፈን አይቻልም። እናም እነዚህን ሁኔታዎች ታሳቢ በማድረግ መንግስት ሰብዓዊ መብት ማክበርን የሞት ሽረት ጉዳይ አድርጎ ወስዶታል። ተግባራዊነቱንም በህግ በማስደገፍ እያረጋገጠ ይገኛል።ይህ የመንግስት ጥረት ዛሬም ይሁን ነገ የሚቀጥል ነው።

የዴሞክሳሲያዊ መብቶች ትግበራም ከዚህ የተለየ አይደለም። መንግስት እንደ ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያከብረው እንዲሁ የህልውና ጉዳይ ስለሆነበት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ የሚከበረው የትኛውንም ወገን ለማስደሰት አይደለም—አገራችን የምትከተለው ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ስለሆነ ነው። እርግጥ አንዳንድ ፅንፈኞች ‘እገሌ የሚባል ፖለቲከኛ ስለታሰረ ኢትዮጰያ ውስጥ ዴሞክራሲ የለም’ በማለት ዘገራችን ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ትክክለኛ የዴሞክራሲ መንገድ ለመካድ ይሞክራሉ።

ሆኖምየፖለቲካ እስረኞች ተበራክተዋል የሚለው ክርክርም በእኔ እምነት ነባራዊውን ሃቅ የሚያንፀባርቅ አይመስለኝም፡፡ እርግጥ ፖለቲከኛ ሆኖ በሌላ የወንጀል ጉዳይ የታሰረ የለም ለማለት አይዳዳኝም። ሊኖር ይችላል፤ ይኖራልም። እኔ እሰከሚገባኝ ድረስ በህግ ጥላና ከለላ ስር ያሉት ግለሰቦችም ቢሆኑ የሀገሪቱን ህግና ስርዓት ተላልፈው የተገኙ ወንጀለኞች እንጂ ፖለቲከኛ ስለሆኑ የታሰሩ አይመስለኝም።

አንድ ግለሰብ ፖለቲከኛ ስለሆነ ብቻ የሚታሰር ከሆነ፤ በህገ-መንግስቱ ላይ የሰፈሩት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አስፈላጊ ባልሆኑ ነበር። ሆኖም በሰለማዊ ፖለቲከኝነት ሽፋን አንድ ፖለቲከኛ ወንጀል ከፈፀመና የሀገሪቱን ሰላም ለማወክ ከተንቀሳቀሰ አሊያም በሀገሪቱ ውስጥ በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶችን ተልዕኮ ለማስፈፀም ከተንቀሳቀሰ እንደ ማንኛውም ግለሰብ በህግ አግባብ መጠየቁ የሚቀር አይመስለኝም። በየትኛውም ሀገር ውስጥ ማንም ሰው ቢሆን ከህግ የበላይ ሊሆን አይችልምና።

እርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲከኝነቱ ብቻ የታሰረ ግለሰብ ለመኖሩ ማስረጃ ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም። ግና ክርክሩ ‘አንድ ሰው ፖለቲከኛ ስለሆነ ወንጀል ቢፈፅምም መታሰር የለበትም’ የሚል ከሆነ እሳቤው የትኛውንም ወገን የሚያስማማ አይመስለኝም። ምክንያቱም በየትኛውም ሀገር ውስጥ በዴሞክራሲያዊ አግባብ የተመረጠ መንግስት ከህዝብ በተሰጠው አደራ መሰረት የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ ሰላለበት ነው።

እናም በተቃዋሚነት የተሰለፈም ይሁን ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን በወንጀል እስከተጠረጠረ ድረስ በህግ ጥላ ስር ውሎ ጉዳዩ መጣራቱ የሚቀር አይመስለኝም። በዚህ ዙሪያ መንግስት ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ በቅርቡ በተለያዩ ክልሎችና ከተማዎች የህዝብን አደራ ወደ ጎን በማለት በኪራይ ሰብሳቢነት በተዘፈቁ አመራሮችና በየደረጃው በሚገኙ አስፈፃሚዎች ላይ የወሰደውን አስተማሪ እርምጃ መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል።

ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ በምቶች በዋነኛነት የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለፅ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት እንዲሁም አቤቱታን ማቅረብን የሚያጠቃልሉ መሆናቸው ይታወቃል። እነዚህ መብቶች ሀገራችን ውስጥ ጥበቃ እየተካሄደላቸው ያሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ በተጨባጭ ገቢራዊ እየሆኑ የመጡም ጭምር ናቸው። መንግስት ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ ይመስለኛል። በተለያዩ ወቅቶች የተካሄዱ ማናቸውም የቡድንና የግለሰብ ፖለቲካዊ መብቶች ያለ አንዳች ጣልቃ ገብነት እየተከናወኑ ነው። ከበሬታ እየተቸራቸውና  ጥበቃ እየተደረገላቸውም ጭምር ነው።

ሌላኛው ከዴሞክራሲ መብት ጋር ተያየዞ የሚነሳው የሃይማኖት መብትና የእምነት ነፃነት ነው። ሆኖም የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የመንግስትና የሃይማኖት መለያየትን በግልፅ መደንገግ ብቻ ሳይሆን ድንጋጌውም ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በላይ ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ በመሆኑ ነው።

እስካሁን ድረስ ባለው ሁኔታ መንግስት ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማስከበር ቁርጠኝነቱን ወደ ጎን ብሎ ከህገ መንግስታዊ ድንጋጌው ውጭ በማንኛውም ሃይማኖት ጣልቃ ገብቶ ‘ይህን አድርግ ያንኛውን ደግሞ ተው’ ያለበትን ሁኔታ የለም። የሃይማኖት መሪዎችን ሲሾምና ሲሽርም ተመልክቻለሁ የሚልን ሰው በእማኝነት ማቅረብ አይቻልም—የሌለ ነገር ነውና። ሆኖም በሃይማኖት ሽፋን የሚካሄዱ የፅንፈኝነት ተግባራትን የማውገዝ፣ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅና ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ የመንግስት ግዴታ መሆኑ ሊካድ አይገባም። ይሁን እንጂ እነዚህ ተግባራት ከሃይማኖት አክራሪነት እንጂ፤ ከሃይማኖት ነፃነት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም።

እርግጥ ሀገራችን ውስጥ ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዩች አኳያ ሙሉ ለሙሉ ምንም ዓይነት ችግሮች የሉም የሚል እምነት የለኝም። በሂደት የሚፈቱ ተግዳሮቶች መኖራቸው እሙን ነው። ያም ሆኖ ግን በደፈናው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እዚህ ሀገር ውስጥ የሉም የሚያስብል ነባራዊ ሁኔታ የለም። ከ26 ዓመታት በፊት ምንም ካልነበረ ነገር ተነስቶ፣ ዛሬ ሊፈቱ ተግዳሮቶች ቢኖም የዜጎችን ሁለንተናዊ መብት ማክበርና ማስከበር ትልቅ እመርታ መጓዝ ተችሏል። እርግጥ ዛሬ እዚህ ሀገር ውስጥ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበረው የሌሎችን ፍላጎትን ለማሟላት ወይም የውጭ መንግስታትን ለማስደሰት አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ ሀገራችን ውስጥ በውጭ ሃይሎች አማካኝነት የሚዘወሩ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊኖሩ አይችሉም፤ አይገባምም። ምክንያቱም መብቶቹ የሚከበሩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዘመናት ትግል ውጤት እንዲሁም የአገራችን የህልውና ጉዳይ ስለሆኑ ብቻ ነው። ቸር እንሰንብት።

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ልማትና የዴሞክራሲ መብቶች መከበር የህልውና ጉዳይ መሆናቸውን፣ መንግስት የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲ መብቶች የሚያከብረውና የሚያስከብረው ሌላ አካልን ለማስደሰት ወይም ዓለም ዓቀፍ ተቋማትን በመፍራት ሳይሆን የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማከበር ለስርዓቱ ለህልውናው ሲል መሆኑ ማስረዳት፤