NEWS

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መሳካት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ቀጥለዋል

By Admin

May 03, 2017

በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መሳካት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ቀጥለዋል።

በሲዊዲን፣ በኖርዌይ፣ በፊንላንድ፣ በአውስትራሊያና በፈረንሳይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት ስድስተኛ ዓመት ክብረ በዓል “ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የአገራችን ህብረ ዜማ የህዳሴያችን ማማ” በሚል መሪ ሀሳብ  አክብረዋል።

በዓሉን ባከበሩበት ወቅት በኖርዌይ ኦስሎና ፊንላንድ ሄልሲንክ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተከናወነ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የሚውል ከሰላሳ ስድስት ሺ ዶላር  በላይ መገኘቱ ነው የተገለጸው።

በተመሳሳይ በአውስትራሊያ በሜልበርንና በካራቤራ ከተማ በተካሄዱ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች ደግሞ አስራ አምስት ሺ ዶላር የቦንድ ሽያጭ ተከናውኗል።

በኖርዲክ አገሮች ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ፤ “የህዳሴ ግድቡ ታላቅ አገራዊ ተስፋን ያነገበና መጪው ትውልድም የሚኮራበትና የሚመካበት ነው” ብለዋል።

“የአገሪቷ ልማትና ዕድገት እውን የሚሆንበትና አገሪቷ የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ በተግባር የሚረጋገጥበት ፕሮጀክት ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በአውስትራሊያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ትርፉ ኪዳነማርያም እንደገለጹት፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ በአገሪቷ እየተሰሩ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች የሃይል ፍላጎት ከማማላቱም ባሻገር የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው።

ለዚህ ታላቅ ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቦንድ በመግዛት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ በፓሪስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተከናወነው ስነ ስረዓት ላይም ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል።

በፈረንሳይ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ነጋ ጸጋዬ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በፈረንሳይና በስፔን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቦንድ በመግዛትና ስጦታ በማበርከት ተረባርበዋል።

በዚሁም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በእለቱ ከቦንድ ሽያጭና ከስጦታ 10 ሺ ዩሮ ለማሰባሰብ ተችሏል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙ ተሳታፊዎችም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት በላከልን የፕሬስ መግለጫ አስታውቋል።