CURRENT

ኢትዮጵያ ለጂቡቲና ለሱዳን ከሸጠችው የኤሌክትሪክ ሃይል ከ49 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች

By Admin

May 18, 2017

ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ወራት ከኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ በአጠቃላይ ከ3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቷን የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገለፀ።

በ2009 በጀት ዓመት ባለፉት 10 ወራት ከኤሌክትሪክ ሃይል ለመሰብሰብ የታቀደው ከ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ እንደነበርም ነው ሚኒስቴሩ የገለፀው።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደገለጹት፥ በ10 ወራት ውስጥ ከተሰበሰበው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ ከ49 ሚሊየን 400 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢው የተገኘው ለሱዳን እና ለጂቡቲ ከተሸጠ የኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ ነው።

ኢትዮጵያ እየገነባቻቸው ያለቻቸው የሀይል ማመንጫዎች ሲጠናቀቁ የሀገር ውስጥ የሀይል ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ለተለያዩ አገራት የኤሌክትሪክ ሀይል የማቅረብ ፍላጎት እንዳለት ይታወቃል።

ሀገሪቱ ለታንዛኒያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ማድረጓም ይታወሳል።

ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ገዝተው መጠቀም የጀመሩት ሱዳን እና ጅቡቲም ተጨማሪ ኃይል ጠይቀዋል።

ኬንያም 200 ሜጋ ዋት ለመግዛት የጠየቀች ሲሆን፥ ሃይሉን ለማቅረብ የመስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክት ተፈርሞ ወደ ሥራ ተገብቷል።

በቀጣይ የጠየቁትን የኃይል ፍላጎት ለማቅረብ ተጨማሪ መስመሮችና የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ለመሥራት ጥናት እየተደረገ ነው ተብሏል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት እያቀረበች ያለችው የኤሌክትሪክ ኃይል የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በማጠናከርና የልማት ትስስሩን በማፋጠን ላይ ይገኛል።