NEWS

ኢትዮጵያ በጣሊያን በሚካሄደው የቡድን 7 ሀገራት ጉባዔ ላይ ተጋበዘች

By Admin

May 25, 2017

ኢትዮጵያ በጣሊያን በሚካሄደው የቡድን 7 ሀገራት የመሪዎች ጉባዔ ላይ በተሳታፊነት መጋበዟ ተነግሯል።

በጣሊያን ቶርሚና በሚካሄደው 43ኛው የቡድን 7 ሀገራት ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት የአፍሪካ ሀገራት ተጋብዘዋል።

ከፊታችን ዓርብ ግንቦት 18 እስከ 19 በሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ላይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደሚገኙ ይጠበቃል።

እንዲሁም የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪ እና የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ቤጂ ካይድ ኢሴቢ ከአፍሪካ በጉባዔው ላይ እንዲሳተፊ የተጋበዙ መሪዎች ናቸው።

የቡድን 7 አባል ሀገራት የሆኑት አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ ጃፓን እና ፈረንሳይ በጉባዔው ላይ የሚሳተፉ ሲሆን፥ የአውሮፓ ህብረትም በጉባዔው ላይ ይገኛል ተብሏል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንግላ ሜርከል፣ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትረዱ፣ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ፣ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ፣ የጣሊያኑ ፓውሎ ጄንትሎኒ እና አዲሱ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ማኑዌል ማክሮን የቡድን 7 ሀገራትን በመወከል በጉባዔው ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል።

እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ድርጅት፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የዓለም ባንክም በጉባዔው ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል።

ጉባዔው በሁለት ቀናት ቆይታው ሽብርተኝነትን መዋጋት፣ የስደተኞች ችግር ዙሪያ በስፋት ይመክራል ተብሏል።

የቡድን 7 ሀገራት የአለማችን 46 በመቶ ጠቅላላ ምርትና 30 በመቶ የመግዛት አቅምን ይሸፍናሉ፡፡