ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የከተሞች አከታተም ካላቸው ሀገራት ተርታ መሰለፏን የከተማና ቤቶች ሚኒስቴር ባስጠናው ጥናት ይፋ አደረገ።
የከተሞቹ አከታተም ዝቅተኛ ለመሆኑ በፕላንና እቅድ አለመመራትና ከተሞች ያላቸውን ሀብትና የሰው ሀይል በአግባቡ አለመጠቀም በምክንያትነት ተነስቷል።
በጎንደር ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ሰባተኛው የከተሞች ፎረም በከተሞች ልማትና እድገት ዙሪያ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን የፓናል ውይይቶችም ተካሂደዋል።
የቀረቡት ጥናቶች በሀገሪቱ ለሚገኙ ከተሞች የወደፊት እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብሏል።
በኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል “የከተሞች የጎንዮሽ መስፋፋት ምክንያቶች ተጽእኖዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች” በሚል ርዕስ በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ፥የከተሞች መስፋፋት የመጨረሻ ግብ ለከተማ እና ለኢንዱስትሪ ልማት የሚሆን መሬት የማግኘት ብቻ ሳይሆን በአካባቢው የሚገኙ ዜጎችን ህይወት በዘላቂነት መቀየርንም በተሟላ መንገድ የሚተገብር መሆን እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡
ከከተሞች ልማት ጋር በተያያዘ ከይዞታቸው ለሚነሱ ዜጎች የሚሰጠው ካሳ በዘላቂነት እንዲያቋቁማቸው በህግ ድጋፍ መታገዝ እንዳለበትም ነው ያመላከተው።
ጥናቱን ያቀረቡት ዶክተር ዘመንፈስ ገብረእግዚአብሄር፥ የልማት ተነሺዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በፓኬጅ የተዘጋጀና የከተሞችን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የህግ ማእቀፍ ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡
“ፓኬጁ የተነሺዎችን የእድሜ ሁኔታ፣ የትምህርት ዝግጅት፣ የስራ ዝንባሌና ፍላጎት፣ የካፒታል አቅም መሰረት በማድረግ በሰልጠና፣ በብድር፣ በምክር አግልግሎት፣ በገበያ ትስስር፣ በማምረቻና መሸጫ ቦታ አቅርቦት መደገፍ አለበት” ብለዋል፡፡
አረጋውያንንና አካል ጉዳተኞችን ደግሞ በማህበራዊ ዋስትና እንዲታቀፉ የሚያደርግ ሊሆን እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የካሳ አዋጁ መመሪያና የደንቦች ማጠንጠኛ የተፈናቃይ ዜጎችን የቀጣይ የኑሮ ዘይቤ መሰረት ያደረገና ዘላቂ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው በማድረግ በኩል በግልጽ መደንገግ እንዳለበት ጥናቱ አመልክቷል።
ተነሺዎች የመሬት ይዞታቸውን ሲለቁ የሚሰጣቸው የመፈናቀያ ክፍያ ቀድሞ የነበራቸው የመጠቀም መብት በመቋረጡ ሌላ የገቢ ምንጭ እስኪያገኙ ድረስ የሚቀጥል ድጋፍ መሆኑ በግልጽ በህግ መደንገግ እንደሚኖርበት ጥናቱ አመላክቷል፡፡
“ከተሞች አቅም በፈቀደ መጠን የልማት ተነሺዎችን የማቋቋም ድጋፍ ያደርጋሉ” የሚለው አስገዳጅነት የሌለው የህግ አንቀጽ አስገዳጅ ሆኖ መደንገግ እንዳለበትም ጥናቱ አመላክቷል፡፡
የፓናል ውይይቱን የመሩት በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ አቶ በረከት ስምኦን፥ በፍጥነት እያደጉና እየተስፋፉ የመጡ ከተሞች ዘላቂ እድገታቸውን ከማስቀጠል አኳያ የሚገጥሟቸውን ችግሮች በጥናትና ምርምር መለየት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
በኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማእከል ለከተሞች ፎረም ተብሎ ያዘጋጀው የመነሻ ጥናትም ከተሞች በችግሮቻቸው ዙሪያ ጥናቱን መነሻ በማድረግ እንዲወያዩ፣ እንዲመክሩና ጠቃሚ ግብአቶችን ማሰባሰብ እንዲችሉ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ በፎረሙ ተሳታፊ ከሆኑ 231 ከተሞች የተጋበዙ የከተማ ማዘጋጃ ቤት ሃላፊዎች ከንቲባዎችና ባለሙያዎችን ጨምሮ የፌደራል ከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሮችና የክልል ቢሮ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።