Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያ ጥራት ላላቸው የቻይና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ ትሰጣለች

0 474

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያ ለልማት ለምታደርገው እንቅስቃሴ የላቀ ጥራት ላላቸው የቻይና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ እንደምትሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

የኢትዮ – ፉጃን የኢንቨስትመንት ትብብር መድረክ ዛሬ በቻይና ፉጃን ግዛት ተካሂዷል።

“የኢትዮጵያ ወቅታዊ የትኩረት አቅጣጫ ወደ ኢንዱስትሪው ሽግግር ማድረግና ተወዳዳሪ የሆነ የአምራች ኢንዱስትሪ መገንባት ሲሆን፤ ለዚህም ቻይና የሰው ኃይል በከፍተኛ ሁኔታ በሚጠይቁ ቁልፍ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ዋንኛ ምንጭ ናት” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በመድረኩ ላይ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የጉልበት ዋጋ፣ የኤሌትሪክ ኃይል አቅረቦትና መሬት ያላት መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አሁንም ሆነ ወደፊት ለቻይና ባለሀብቶች ተመራጭ አገር መሆኗን ትቀጥላለች” ብለዋል።

የፉጃን ግዛት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በተለይም በጨርቃ ጨርቅ፣ ጥጥና ቆዳ ምርት እንዲሁም በልማቷና በኢንዱስትሪ ፓርኮች አስተዳደር ያላት ተሞክሮ የመንግስታቸውን ትኩረት እንደሳበ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም የፉጃን ግዛት መንግስትና በግዛቷ የሚገኙ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እንዲያቋቁሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የጠየቁ ሲሆን፤ ለዚህም ኢትዮጵያ “አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግዛቱ በነበራቸው ቆይታ ከትላልቅ ኩባንያ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሸጋገር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች ሲሆን፤ በተለይም በአምራቹ ዘርፍ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነች ነው።

የቻይና  መንግስት የአገሩን ኩባንያዎች በማደግ ላይ ባሉ አገሮች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ሲያበረታታ ዋንኛ ምርጫው ኢትዮጵያ ናት።

የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ዛዲግ አብርሃ እንደተናገሩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፉጃን ያደረጉት ጉብኝት የግዛቲቱ ታላላቅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስመንት እድል አውቀው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ያለመ ነው።

በዚህም ረገድ ከሻንዶንግና ፉጃን ግዛቶች ኃላፊዎችና በግዛቱ ከሚገኙ ኩባንያዎች ጋር የተደረገው የሁለትዮሽ ውይይት ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

በግዛቶቹ የሚገኙ ኩባንያዎች የአዋጪነት ጥናት በማድረግ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን አውጥተው በልማት ለመሳተፍ እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን አቶ ዛዲግ አክለዋል።

በፉጃን ግዛት ውስጥ ከሚገኙ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ፋሽን ፍላዪንግ ግሩፕ ፕሬዝዳንት ሚስተር ቼን ጌንግ  እንደገለጹት ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ ፍላጎት አለው።

በጨርቃ ጨርቅ፣ ፋይበር፣ ህትመት፣ ዲዛይንና ማሽነሪ ዘርፎች “የምርት ሰንሰለት በመገንባት ያለውን ተሳትፎ ያሳድጋል” ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2014 ጀምሮ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ እየሰራ መሆኑን ያስታወሱት ሚስትር ጌንግ፤ በቀጣይም በፓርኩ በተለያዩ ምዕራፎች ለሚሰሩ ስራዎች 20 ሚለዮን ዶላር መመደቡን አስታውቀዋል።

“ኢትዮጵያ በጣም ጥሩ አገር ናት። የቻይና ዜጎች በዚያው ይኖራሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም በአገሪቷ ሰላም እንዲሰፍን በበቂ ሁኔታ እየሰራ ነው። ይህ በመሆኑም ኩባንያችን ያለ ምንም ስጋት በሰላም እየሰራ ነው” ብለዋል።

በፉጃን የሚገኙ ስምንት ኩባንያዎች በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው እየሰሩ መሆናቸውንና በአጠቃላይ የዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሳቸውን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።

የፉጃን ግዛት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2016 ባስመዘገበችው የ423 ነጥብ 9 ሚለዮን ዶላር ዓመታዊ የምርት መጠን በቻይና ከሚገኙ ግዛቶች አስረኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy