Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እኛና ሶማሊያ !!

0 747

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እኛና ሶማሊያ !!

                                  ይነበብ ይግለጡ

የሶማሊያ ጉዳይ የቅርብ ጎረቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን መላውን አለም ያስጨነቀ ለመፍትሔ ፍለጋም የተለያዩ የቅርብና የሩቅ ሀገር መሪዎችን ታዋቂ ግለሰቦችን አለም አቀፍ ተቋማትንም ለምክክርና ለውይይት በጋራ በጠረጴዛ ዙሪያ ያስቀመጠ ነው፡፡ ሶማሊያ ቀድሞ የነበራት የጀነራል ዚያድ ባሬ ማእከላዊ መንግስት ከፈረሰ በኃላ የአለም አቀፍ አሸባሪዎች መናሀሪያ ከመሆንም በላይ የራስዋ የጎጥና የጎሳ አለቆች በጦር አበጋዝነት ተሰልፈው እርስ በእርስ የተጫረሱባት የጦርነት አውድማ ሆና ኖራለች፡፡የመከራው ገፈት እልቂትና ስደት የእርስ በእርስ ጦርነትና ደም መፋሰሱ የጎዳው የሶማሊያን ሕዝብ ነው፡፡

ሕዝቡ በአገኘው ቀዳዳ ተጠቅሞ ከጦርነትና እልቂት በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ ኬንያ ጅቡቲ የመን ኡጋንዳ ወደተለያዩ የአፍሪካና አውሮፓ ሀገራት በገፍ ተሰዶአል፡፡የስደቱ ዋና ምክንያት በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት መጥፋቱ፤ሀገሪቱ የአለምአቀፍ አሸባሪዎች መፈንጫ መሆንዋ፤በፊት የእስላማዊ ምክርቤት ይባል የነበረው  በኃላ ስሙን ለውጦ አክራሪና አሸባሪ የሆነው እስላማዊ ኃይል የአልቃይዳ አጋርና አባል የሆነው አልሻባብ በሰፊው በሶማሊያ በመንሰራፋቱ ነው፡፡

አልሻባብ በሶማሊያ ሰፊ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር በቅቶ ስለነበር ወጣቶችን በስፋት በመመልመል ለጦርነትና ለሽብር ስራ ዳርጎአቸዋል፡፡በአፍሪካ ቀንድ የሚካሄዱትን አለም አቀፍ የሽብር ስራዎች በበላይነት የመራውና የሚያስተባብረው አልሻባብ ነው፡፡በኬንያ ገበያ ማእከል በታንዛኒያ በኡጋንዳ በተለያየ ግዜያት አጥፍቶ ጠፊዎችን በማሰማራት ፈንጂዎችን በመቅበር ፍንዳታዎች አድርሰው ንጹሀን ሰዎችን ገድለዋል፡፡

አልሻባብ በኢትዮጵያ ተደጋጋሚ አደጋ ለማድረስ በማቀድ የጅሀድ ጦርነትም እስከ ማወጅ ደርሶ ነበር፡፡በብዙ አጋጣሚዎች አልተሳካለትም፡፡ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድናችን በአዲስ አበባ ስቴዲየም የጨዋታ ውድድር በሚያደርግበት ወቅት የአልሻባብ አባላት በቦሌ ቤት ተከራይተው ፍንዳታ ለማድረስ አቅደው እያለ ቦምቡ በራሳቸው ላይ በመፈንዳቱ ሁኔታው መጋለጡን በወቅቱ ከተሰጠው መግለጫ ለመረዳት ተችሎአል፡፡

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጉዳይ የተለየ ትኩረት የምትሰጠው የቅርብ ጎረቤትና ሰፊ ድንበር የምትጋራ ሀገር በመሆንዋ ነው፡፡ማንኛውም በሶማሊያ ውስጥ የሚፈጠር ችግር በቀጥታ ኢትዮጵያን የሚነካ በመሆኑ አስቀድሞ መከላከልና በሩቁ መመከት አስፈላጊ መሆኑን ትገነዘባለች፡፡ዛሬ ላይ እንደምንመለከተው የተለያዩ ሀገራት በሶማሊያ ጉዳይ ተዋናይ የሆኑበትን ሁኔታ እያየን ነው፡፡በሶማሊያ ጉዳይ ሰላማዊ መፍትሔ ለማስገኘት አለም አቀፉ ሕብረተሰብ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ይገኛል፡፡

ትልቁ ግብ ሀገሪቱ የአለም አቀፍ አሸባሪዎች መፈንጪያ እንዳትሆን ስር የሰደደውንና ተዋጊ ኃይል አደራጅቶ የሽብር ተግባር የሚፈጽመውን የአልሻባብና የአልቃይዳን ጥምር ንቅናቄ ከግዛትዋ ጠራርጎ ለመደምሰስ በሁሉም መስክ ድጋፍ እንደሚያደርግ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ መግለጹ ተጠቃሽ ነው፡፡አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል በአልሻባብ ቁጥጥር ስር ነበር፡፡አሚሶም ከመግባቱም በፊት በአልሻባብ ይዞታ ስር የነበሩትን በርካታ ቦታዎች እየተዋጋ ያስለቀቀው  የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደነበር ይታወቃል፡፡

በሶማሊያ ረሀብና ድርቅ ብቻውን ከ250 ሺህ ሕዝብ በላይ እንዲያልቅ ምክንያት ሆኖአል፡፡ማእከላዊ መንግስት አልባ በሆነችበት ሁኔታ የሶማሊያን ሕዝብ ለከፋ ችግር የዳረጉት ሀገሩን ለቆ እንዲሰደድ ምክንያት የሆኑት በርካታ ችግሮች ተከስተዋል፡፡አሁንም ችግሩን ለማቃለል ተስፋና ጥረት መኖሩ እንዳለ ሁኖ በብስለትና በጥንካሬ ካልተያዘ የሰላም ጥረቱን መነሻ ሊያፈርሱ የሚችሉ በርካታ ሁኔታዎችም አሉ፡፡

በሶማሊያ ጠንካራና ቋሚ መንግስት መፍጠር፤የሶማሊያን ብሔራዊ ሠራዊት ሁሉንም ጎሳዎች በአማከለ መልኩ መገንባት፤ኢኮኖሚውን የመታደግና የማሳደግ እንቅስቃሴ ማድረግ፤ሕገመንግስቱን ሁሉም ወገኖች በጋራ መክረው የሚያሻሽሉትን አሻሽለው ለሁሉም የተመቸችና ሁሉም በጋራ ሀገሬ የሚላትን ሶማሊያ በውይይት በምክክር በሰላማዊ ድርድር እንዲፈጠር ለማድረግ አለም አቀፉ ሕብረተሰብ እየሰራ ይገኛል፡፡ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ አስቀድማም ተወጥታለች፡፡አሁንም በመወጣት ላይ ትገኛለች፡፡ኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈለች ሀገር ነች፡፡

በሶማሊያ የባሕር ላይ ሽፍትነት እየገነነ በመሄዱ የአንድ ወቅት የአለም መነጋገሪያ ርእስ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡አለምአቀፉን ንግድ  በአንድ አመት ብቻ 7 ቢሊዮን ዶላር እንዲያጣ አስገድዶታል፡፡ይህን አሳሳቢ ሁኔታ ለመግታት እንግሊዝ አለም አቀፉን ማሕበረሰብ በማሰባሰብ በ2011 የለንደኑን የሶማሊያ ኮንፈረንስ ካዘጋጀች ወዲህ በመጠኑም ቢሆን  ሶማሊያ ነፍስ መዝራት ችላ ነበር፡፡

የፌደራል መንግስት በ2012 ቢቋቋምም ፈርጀ ብዙ ፈተናዎችን መጋፈጥ ድንገተኛ የአሸባሪ ጥቃቶችን መመከት ግድ ሆኖበት ቆይቶአል፡፡የኢኮኖሚ ድቀቱ፤የስራ አጡ ቁጥር፤ የወደሙ መንግስታዊ ተቋማትን መልሶ የማደራጀት ስራን ለመካሄድ ያለው አቅም ደካማ ስለሆነ ብቻውን ሊወጣው አልቻለም፡፡የአለም አቀፉ ሕብረተሰብ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያትም ይሀው ነው፡፡እጅግ ብዙ ብዙ ርቀት ሄዶ መስራት ይቀረዋል፡፡ ለዚህም ነው በሶማሊያ አንጻራዊ ሠላምና ደሕንነትን ዘላቂ ለማድረግ አገሪቱ ከቀጠናውና ከአለም አቀፉ ማሕበረሰብ የተጠናከረ ድጋፍ የምትሻ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያስታወቁት፡፡

የአፍሪካ ሕብረት ተልእኮ በሶማሊያ(አሚሶም) በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል መረጋጋትን ፈጥሮ ቁልፍ ከሆኑ ቦታዎች አልሻባብን ማስወጣት የቻለ ሲሆን በተለይም የኢትዮጵያ ሠራዊት በዚህ ግዳጅ የተጫወተው ሚና በእጅጉ የላቀና የጎላ ነው፡፡የምስራቅ አፍሪካ  የልማት በይነ-መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) መሪዎችና የሚመለከታቻው አጋር አካላት በሶማሊያ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላምና ደህንነት ዘላቂ ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በእንግሊዝ እየመከሩ በነበሩበት ጉባዔ ላይ የወቅቱ የኢጋድ ሊቀ-መንበር የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚደረገው ድጋፍ ጎልብቶ ሊቀጥል እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ኃይል እንሁን፤አንድ ድምጽ ይኑረን፤ትኩረትም እንስጠው፣ቀጣናዊና ዓለምአቀፋዊ ትብብርና እርምጃ ለመውሰድ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይኑረን፤ይሄ ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ ይሰማኛል ብለዋል፡፡ ይህ ካልሆነ በእርግጠኝነት በዚህ ጉዳይ ለውጡ ውጤታማ ሊሆን አይችልም ሲሉ የተናገሩት ለትብብሩና እገዛው በጋራ ከመቆም ውጭ ያለው መንገድ ብዙም ተስፋ ሊሰጥ የማይችል ስለመሆኑ ስጋታቸውን መግለጻቸው ነው፡፡ይህ የአካባቢውን ፈጣን ተለዋዋጭ ሁኔታ የአሸባሪዎቹን አውዳሚ እንቅስቃሴ በቅርበት ከመረዳትና የአደጋውን ግዝፈት ከግምት ውስጥ በማስገባት የመነጨ ትክክለኛ ሀሳብ ነው፡፡

የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ድጋፍ በሶማሊያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት፣ለድርቅ ቅነሳና የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል፣ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ማገገሚያ፤ ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን እንዲውልም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጠይቀዋል፡፡ 

አልሻባብ አሁንም በዋና ከተማዋና በሌሎችም አካባቢዎች ከባድ የሽብር ጥቃት ለማድረስ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገልጸው ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ከአልሻባብ ጀርባ እነአልቃይዳ እነቦኮሀራም እነአይሲስ ሌሎችም በቅንጅትና በትብብር ቀጠናውን በሽብር ለማመስ እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል፡፡በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ጦርን በማጠናከር በተለይ በአልሸባብ ላይ የሚደረገውን ዘመቻ መደገፍ ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል፡፡  

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እኛ እንደ ቀጣናው አገር መሥዋእትነት መክፈሉን እንቀጥላለን፤በሶማሊያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነን፤ ከዚህ በላይ ድጋፍ የለም፤ይህ ለጋራ ጥቅም የሚደረግ ነው ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን አሸባሪነት እንዲወገድ የከፈለችውን ከፍተኛ መስዋእትነት በማስታወስ ዛሬም በአካባቢው የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን ያላትን ቁርጠኝነት የገለጹበት ጠንካራ አባባል ነው፡፡

በቀጠናው በአሁኑ ወቅት ድርቅ ተከስቷል፤የተከሰተው ድርቅና ስደት የፖለቲካና ደሕንነት ጉዳይ ሆኖ እየታየ በመሆኑ በአፋጣኝ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ  በሶማሊያ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሺኝ አፋጣኝ መፍትሔና ድጋፍ የሚሻ መሆኑን፤ የሶማሊያ ኢኮኖሚ እንዲያገግም የተሻለ መተዳደሪያ የሥራ እድል፤የአገር ውስጥ ገቢ ማስገኛ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘላቂነት ያለው ልማት ለማምጣት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የገለጹ ቢሆንም ሌሎቹ ለጉዳዩ ምን ያህል ትኩረት ሰጥተውት  በአፋጣኝ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይገባሉ የሚለው ትኩረት የሚስብ ጥያቄ ነው፡፡ልናይ ገና እንዲሉ፡፡

በሶማሊያ የተለያዩ ሀገራት ወደውስጥ ዘልቀው መግባታቸው ከብሔራዊ ጥቅሞቻቸው አንጻር ራሱን ችሎ በስፋት ሊፈተሽ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ቱርክ በሶማሊያ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ገንብታለች፡፡ ከአሜሪካና ከእንግሊዝ ጋር በመሆን አዲሱን የሶማሊያ ሠራዊት ለማደራጀት ማሰልጠኑን ተያይዘውታል፡፡ እነሱ ከመምጣታቸው በፊት ስልጠናውን ስትሰጥ የነበረችው በሶማሊያ ተከማችቶና በብዙ ቦታዎች ተንሰራፍቶ የነበረውን አለም አቀፍ አክራሪና አሸባሪ ኃይል አልሻባብን በግንባር ገጥማ የተዋጋችው አሚሶም ከመግባቱም በፊት ከገባም በኃላ ታላቅ መስዋእትነት የከፈለችው ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡

በቅርቡ ዘ- ሂል የሚል የእንግሊዝኛ ድረገጽ አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ከአሸባሪነት ጋር በምታደርገው ትግል ከእንግዲህ የኢትዮጵያን አጋርነት አትፈልግም ሲል አስነብቦ ነበር፡፡ እንዲህ አይነቱ የጽንፈኛና አክራሪ ፖለቲከኞች እጅ ያለበት አገላለጽ የአሜሪካንን መንግስት አቋም ባይገልጽም ኢትዮጵያ ሁልግዜም ተፈላጊና ወሳኝ ሀገር መሆንዋ የሚዘነጋ አይደለም፡፡በሶማሊያ የተረጋጋ ሰላም እንዲፈጠር ችግሩ ወደራስዋ ግዛት እንዳይዛመት  አልሻባብን በመዋጋት ረገድ የከፈለችው መስዋእትነት ግዙፍ ነው፡፡ይሄንን ማንም ሊክደው አይችልም፡፡

ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ካላት ቅርብ ጉርብትና በመልክ አምድርዊ ስትራቴጂክ አቀማመጥ እያደገ ከመጣው አቅሟም አንጻር በቀጠናው ተጽእኖ አሳዳሪ ሀገር ለመሆን የበቃች በመሆኑ የኢትዮጵያ አስፈላጊነት እያደር እየጨመረ የሚሄድ እንጂ የሚቀንስ አይደለም፡፡ ለሶማሊያም ሆነ ለቀጠናው ሰላም በወሳኝነት አስፈላጊ ሀገር ነች፡፡

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ለዴሞክራሲ ግንባታ ትኩረት ለመስጠት፣ አሸባሪነትና ሙስናን ለመዋጋት፤በሀገሪቱ ዘላቂነት ያለው ልማት ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ በጉባዔው ፊት በመግለጽ ሶማሊያ በሁሉም መስክ  የተሻለ እድገት ላይ እንድትደርስ የዴሞክራሲ ተቋሞችን ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ በሶስቱ  የሶማሊያ ዋና ጠላቶች በሽብርተኝነት፣በሙስና፤በድሕነት ላይ እንዘምታለን ማለታቸው ተስፋ ሰጪና በጎ ጅምር ነው፡፡

ፕሬዚደንቱ በሶማሊያ ተፈጥሮአዊ ኃብት ላይ ፍትሐዊ ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ ጅምር ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመው መንግሥታቸው በዘርፉ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ዘላቂነት ያለው ሥራ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

አዲሱ ብሔራዊ የፀጥታ መዋቅር የሶማሊያን ብሔራዊ ጦር ለማጠናከርና በአገሪቱ ለውጥ ለማምጣት ጥሩ አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ጦርን በማገዝ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአልሸባብ ላይ ድል እንደምትቀዳጅ ፕሬዚዳንቱ ያላቸውን እምነትና ተስፋ በመግለጽ ለስኬቱ የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy