Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከሳዑዲ ዓረቢያ አለመውጣት አማራጭ አይሆንም!!

0 351

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከሳዑዲ ዓረቢያ አለመውጣት አማራጭ አይሆንም!!

ዮናስ

ሳዑዲ ዓረቢያ በሕጋዊ መንገድ ያልገቡ ዜጎች ለቀው እንዲወጡ የሃገሪቱ መንግስት የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ ማስቀመጡ ይታወሳል።  የአዋጁ ጊዜ ገደቡ ከግማሽ በላይ እየተጠናቀቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት  ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የአገሪቱን መንግሥት የምሕረት አዋጅ በተገቢው ሁኔታ እየተጠቀሙ አለመሆናቸው ከኢትዮጵያ መንግስት እየወጡ የሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ሰነድ አልባ ስደተኞች ያለ ምንም ቅጣት ከሃገሪቱ እንዲወጡ ያስቀመጠው የሦስት ወራት ገደብ ሊጠናቀቅ ከ45 ቀናት ያነሰ ጊዜ የቀሩት ቢሆንም፣ እስካሁን  የኢትዮጵያውያን ተመላሽ ተመዝጋቢዎች ቁጥር ከ20 ሺሕ እንደማይበልጥ በመረጃዎቹ ተመልክቷል፡፡

ዓርብ ግንቦት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በውጭ  ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው የተመላሾች አስተባባሪ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ሚኒስትር ዴኤታው አክሊሉ ኃይለ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ከሚኒስትሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ጋር በጋራ በመሆን ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት  መንግሥት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ የማንቀሳቅስና የማስተባበር ሥራ እያከናወነ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ ኢትዮጵያውያን በአጥጋቢ ቁጥር የምሕረት አዋጁን እየተጠቀሙ አለመሆናቸው የሚያሳሰብ ነው ብለዋል፡፡

ስደተኞቹ በፍጥነት ያልመጡትና የምሕረት አዋጁን ያልተጠቀሙባቸው በርካታ ምክንያቶች መካከል ብዙዎቹ አዋጁ ተግባራዊ ሊሆን ስለማይችል ሌሎች ከወጡ በኋላ የተሻለ ገንዘብ ይገኛል የሚለውና የቤተሰብ ጫናና መዘናጋት ዋነኞቹ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ በአካባቢው የሚገኙ ሕገወጥ ደላሎች እንደዚህ ዓይነት ወሬዎችን በማስወራት፣ ዜጎች በሰላም ወደ አገራቸው እንዳይመጡ እያደረጉ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ባቋቋማቸው ሰባት የምዝገባ ጣቢያዎች እስካሁን የተመዘገቡት 20 ሺሕ ተመላሾች ብቻ ናቸው፡፡ በውይይቱ ላይ ከዚህ በፊት በ2005 ዓ.ም. በተመሳሳይ ከሳዑዲ ዓረቢያ ያጋጠመው ዓይነት ከፍተኛ የሆነ የሞት፣ የአካል መጉደልና እሱ ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ እንደገና የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ሰነድ አልባ ስደተኞች ለመመለስ ፈቃደኛ የማይሆኑት ቀደም ሲል የሳዑዲ ተመላሾችን ለማስተባበር የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ  ለስደት ተመላሾች የተገባላቸውን ቃል አለመፈጸሙ ፤ተስፋ አድርገው የመጡ ተመላሾች ተበትነው ስለመቅረታቸው ወደ ሃገር ቤት እንዳይመለሱና ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓል የሚሉ አስተያየቶችም እየተሰጡ ነው፡፡ በተጨማሪም ከአስተያየት ሰጪዎቹ ክልሎች ቃል እንደሚገቡት በተግባር እንደማይሠሩ፣ ከዚህ በፊት በስንት ችግር ከመጡ ስደተኞች መካከል ብዙዎቹ ተመልሰው መሄዳቸውንና መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ አለማበጀቱ በምክንያትነት እየተጠቀሰ ነው፡፡

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን መፍትሄውን ወደፊት ማሰብ እንጂ ሞት እንደአማራጭ መውሰድ  የለበትም። የኢትዮጵያ መንግስት በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች የመውጫ ቪዛ የሚያገኙባቸው ተንቀሳቃሽ ጽሕፈት ቤቶችን ከፍቶ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እያደረገ ቢሆንም በተለይ ማህበራዊ ሃላፊነት ያለባቸው መገናኛ ብዙኃን  አደጋውን በመከላከል ላይ ከማተኮር ይልቅ ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች ላይ ሰጣ ገባ መግጠማቸው ነው። መገናኛ ብዙሃን ምክንያታዊ የሚሆኑት ዜጎችን በመታደግና መፍትሄ በማምጣት መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት ለማሳካት አጀንዳቸው አድርገው ሲሰሩ ነው።

አሁን ሊታሰብ የሚገባው አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በህገ-ወጥ መንገድ ባህር አቋርጠው የሄዱ በመሆናቸው ምን ያህል ኢትዮጵያውያን በስፍራው እንደሚገኙ ለማወቅ እንኳ ያልተቻለበት መሆኑ ነው። በእርግጥ በጅዳ እና ሪያድ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንጽላ ፅህፈት ቤቶች ይህንን የሚያጣራ ሥራ እየሠሩ የሚገኙ ሲሆን በሳዑዲ ገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በመኖራቸው አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የምዝገባ ጣቢያዎች ተቋቁመው እየተሠራ ቢሆንም ቢያንስ ሊኖሩ ይችላሉ ተብሎ ከሚገመተው ሲሶውም አለመመዝገቡ ያሳስባል።

በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ከአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እና  መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሚሲዮኖች ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑን የሚያመለክተው መንግስት፤በጉዳዩ ላይ ለኅብረተሰቡ መረጃ እንዲደርስ ከመገናኛ ብዙሃን ጋራ ሰፊ ሥራ የተሠራ ቢሆንም በቂ ባለመሆኑ ከዜና በዘለለ ፕሮግራም እና ሌሎች ዘገባዎችን በተከታታይ በመስራት መገናኛ ብዙሃን በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ አጀንዳቸው አድርገው መሥራት አለባቸው በማለት ማሳሰቡ የስጋቱን ደረጃ የሚያመላክት ነው።

የኢፌዴሪ መንግሥት ሳይውል ሳያድር ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ ልዩ ልዩ ተግባራትን በማካሄድ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ኮሚቴ  ለተመላሾች ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ ወደአገር እስኪመለሱና ከተመለሱ በኋላ አቅም በፈቀደው መልኩ በዘለቄታ እስከሚቋቋሙበት ድረስ ከክልል መንግሥታት ጋር በመሆን ዝርዝር ጉዳዮችን በማጥናትና ሥርዓት በማበጀት ሌት ተቀን እየሰራ መሆኑንም አመልክቷል፡፡በመሆኑም መንግሥት የገባውን ቃል ተግባራዊ እንዲያደርግ  ግፊት ማድረግ እንጂ ቃሉን ላይፈጽም ይችላል በሚል ግምትና የደላላ ወሬ መታወር ተገቢ አይሆንም፡፡ 

የመንግስት ፍላጎት ከሳዑዲ ተመላሽ  ዜጎቻችን አንዳችም ዓይነት ጉዳት እና እንግልት ሳይደርስባቸው በተሰጣቸው የእፎይታ ጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ አገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ማስቻል ነው፡፡ በመሆኑም በእስካሁኑ ሂደት የተወሰኑ ዜጎቻችን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፤ በየዕለቱ በመመለስ ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ የተመላሾቹ ቁጥር ከሚጠበቀው አንጻር ሲታይ አነስተኛ መሆኑም ተረጋግጧል፡፡ ይህ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ዜጎቻችን የሳዑዲ መንግስት ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ  ወደ አገራቸው ካልተመለሱ  አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ የዜጎቻችን ሰብዓዊ መብቶቻቸው ይጣሳሉ፣ ንብረቶቻቸው ይወረሳሉ፣ ለእስራትና ለእንግልት ይዳረጋሉ። አዋጁ እንደተገለጸው ከ15 እስከ 50 ሺህ የሳዑዲ ሪያል የገንዘብ መቀጫ እንደሚጣልባቸው ነው ። በመሆኑም  በሳዑዲ የሚገኙት ዜጎቻችን ይህንኑ ከወዲሁ ተገንዝበው በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ በቀሪዎቹ ቀናት  ፈጥነው ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡

የጊዜ ገደቡ ሳይጠናቀቅ  ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ  በማድረግ በኩል በተለይ ወላጆች ለልጆቻቸው ደህንነት ሲሉ ከፍተኛ ግፊት ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን መንግሥት፣ ሚዲያዎች፣ ማህበራት፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እና መላው ህዝብ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ዜጎቻችንን ቶሎ እንዲመለሱ በማድረግ በኩል የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።

ይህ እንዳለ ሆኖ  በተለይ ‹‹እዚህም ሞት  እዚያም ሞት›› የሚል ከፍተኛ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በስደተኞቹ ዘንድ እንዳለ እየተሰጠ ያለው አስተያየት እውነትም ይሁን ውሸት መንግስት ወደፊትም ከሚኖረው ተጽእኖ አኳያ አይቶ ስደተኞቹ ሲመለሱ ለማስተናገድ ያዘጋጀውን የተለየ ፓኬጅ በግልጽ እና በተደጋጋሚ ሊያብራራ ይገባል፡፡ ቃሉንም በተግባር ሊፈጽም ይገባል።

ከሁሉም በላይ ግን ቀደም ሲል የተጀመረውና በርካታ ዓመታት ያስቆጠረው  ዜጎች መብታቸው ተከብሮላቸው በሕጋዊ መንገድ ተጉዘው እንዲሠሩ ያስችላል የተባለውን አዋጅ በፍጥነት  በሥራ ላይ ማዋል ይገባዋል።ምክንያቱም በተለይ የሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሾች የምሕረት አዋጁን ተጠቅመው  ሃገር ቤት ቢመጡ አሻራ ሳይሰጡ ስለሆነና ተመልሰው በሕጋዊ መንገድ እንዲሄዱ የሚፈቅድ በመሆኑ፣ አዋጁ ተግባራዊ ቢደረግ ስደተኞቹን ወደ ሃገር ቤት በቶሎ ለማምጣት ያስችላል፡፡በሳዑዲ ዓረቢያ በመቶ ሺሕ የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ ስደት ላይ የሚገኙ ሲሆን ብዙዎቹ አሰቃቂ የሆነውን የባህርና የበረሃ ጉዞ ሲያደርጉ ከሞት የተረፉ እንደመሆናቸው ዛሬም ሞትን እንደአማራጭ መውሰድ ተገቢ አይሆንም፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy