CURRENT

ከስደት ተመላሾቹ በሀገራቸው ሰርተው ለመለወጥ ይፈልጋሉ

By Admin

May 02, 2017

የጂማ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ፎዚያ አሊ አደም በሳኡዲ አረቢያ ለአመታት ኖረዋል፡፡ የሀገሪቱ መንግስት ሀጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ያስቀመጠውን የ90 ቀናት የእፎይታ ጊዜ ተከትሎ ሰሞኑን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

ወይዘሮ ፎዚያ የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ያስተላለፈውን መልእክት በመስማት ምንም ጊዜ ሳይወስዱ በአፋጣኝ መመለሳቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹የእፎይታ ጊዜው ሳይጠናቀቅ ወደ አገሬ በመግባቴ ደስተኛ ነኝ›› ብለዋል፡፡

በሪያድ የሚገኝው የኢትዮጵያ አምባሲ የጉዞ ሰነድ በአጭር ጊዜ አዘጋጅቶ እንዳቀረበላቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ፎዚያ፣ እስከ ሀገሪቱ አየር ማረፊያ ድረስ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ ሲሰራም መመልከታቸውን ጠቅሰው፣ለኤምባሲው ሰራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ወይዘሮ ፎዚያ የራሳቸውን ሶስት ልጆች ጨምሮ አምስት ቤተሰብ ያስተዳድራሉ፡፡ አሁን ይዘው በመጡት ጥቂት ገንዘብ ላይ ከመንግስት ተጨማሪ ገንዘብ በመበደር የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ በመክፈት አገራቸውን እና ራሳቸውን ለመለወጥ ማሰባቸውን ይገልጻሉ፡፡

የራያ ቆቦ ነዋሪው አቶ ሻምበል አድነው ሌላኛው ተመላሽ ናቸው፡፡ ከሳኡዲ ሲመለሱ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው፡፡ በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዙር በተመሳሳይ በሳኡዲ መንግስት ተባረው ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን፣ ተስፋ ባለመቁረጥ ለሶስተኛ ጊዜ የዛሬ ሁለት አመት ወደ ሳውዲ ማቅናታቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሻምበል በሳውዲ ስራቸው ግመል እና ፍየል መጠበቅ ነበር፡፡ በሶስት ዙር የሳውዲ ጉዞ ያተረፉት ምንም ጥሪት ሀብት እንደሌላቸው ጠቅሰው፣ ይልቁኑ በአሁኑ ዙር ከባድ የእግር ህመም አጋጥሟቸው ለአራት ወራት በሆስፒታል ተኝተው እንደነበርም ይናገራሉ፡፡

‹‹የሰው ሀገር ኑሮ አሁን ሰልችቶኛል›› ሲሉ በምሬት የሚናገሩት አቶ ሻምበል ከአሁን በኋላ ከአገራቸው ላለመውጣት መወሰናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ያላቸውን ውስን መሬት በማልማት ራሳቸውን እና አገራቸውን ለመለወጥ ማቀዳቸውን ይጠቁማሉ፡፡

ወይዘሪት ማሪቱ ጋሻው በሳኡዲ አረቢያ ላለፉት አራት ዓመታት በቤት ሰራተኝነት ሰርታለች፡፡ አንድ ተጨማሪ ዓመት በሳኡዲ የመቆየት እቅድ ነበራት፡፡ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት የሰጠው የምህረት ጊዜ ሳይጠናቀቅ ሀገሯ መግባት ግድ ስለሆነባት መመለሷን ትገልጻለች፡፡

ማሪቱ ምንም ባለሰበችበት ወቅት ነው አገሪቱን ለቃችሁ ውጡ የሚል አዋጅ የሰማችው ፡፡ ይህን ስትሰማ ነገሮች ከብደዋት ነበር፡፡ የእፎይታ ጊዜው ከተጠናቀቀ በኋላ የሚፈጠሩ ነገሮች ከባድ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጻ፣ ወደ አገሯ በመመለሷ ተደስታለች፡፡

‹‹ምንም እንኳን ብዙ ገንዘብ ይዤ ባልመጣም በሰላም ወደ አገሬ በመግባቴ ደስተኛ ነኝ›› ያለችው ማሪቱ ፣ባላት ገንዘብ ትንሽ ስራ በመስራት ራሷን እና አገሯን ለመጠቀም ወስናለች ፡፡ ከመንግስትም ተጨማሪ ገንዘብ ለመበደር ማሰቧን ተናግራለች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ፣ ከሳኡዲ አረቢያ ወደ አገራቸው ለመመለስ 11 ሺ 500 ገደማ ዜጎች የጉዞ ሰነድ የወሰዱ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ አራት ሺ የሚሆኑት አገር ቤት ገብተዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ዖመር በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ እስከ አለፈው እሁድ ድረስ በሪያድ እና አካባቢው 5 ሺ333፣ በጂዳ እና አካባቢው 6 ሺ 160 ዜጎች የጉዞ ሰነድ ወስደዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አራት ሺ ገደማ የሚሆኑት ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡

መላኩ ኤሮሴ

– See more at: http://ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/news/national-news/item/12433-2017-05-02-17-45-54#sthash.Tbt1I6ef.dpuf