Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከንቱ ወሬ

0 484

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከንቱ ወሬ

ኢብሳ ነመራ

የአውሮፓ ፓርላማ በቅርቡ ኢትዮጵያ ላይ አሳለፍኩት ያለውን አንድ ውሳኔ ይፋ አድርጓል። የአውሮፓ ፓርላማ ኢትዮጵያ ላይ ውሳኔ ሲያሳልፍ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ ቀደምም ውሳኔ አሳልፎ ያውቃል። ለውሳኔው መነሻ የሚሆነው ሃሳብ በፓርላማው ተጠንቶ የተገኘ ጭብጥ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአመዛኙ የኢፌዴሪን ህገመንግስታዊ ስርአት በሃይል ለመናድ ከሚንቀሳቀሱ የሌላ ሃገራት ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚቀበለው ነው፣ መርምሮ ሳያረጋግጥ የሚቀበለው ወሬ። እነዚህ ኢትዮጵያዊነታቸውን በፍቃዳቸው የተዉ የሌሎች ሃገራት ዜጎች፣ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን ለማተራመስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ከተጣለበት የኤርትራ መንግስት ጋር በመተባባር የሚሰሩ ናቸው። ተቃዋሚ ነን ባዮቹን ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኤርትራ መንግስትን ወይም መሪውን ኢሳያስ አፈወርቂ ያወዳጃቸው ኢትዮጵያ ላይ ያላቸው ተመሳሳይ ፍላጎት ነው። ይህም ኢትዮጵያ የምትባለውን ሃገር በዓለም ፊት የማዋረድ፣ በእርስ በርስ ግጭት የሰቆቃ ምድር የማድረግ፣ ዜጎቿ በድህነት (በምግብ እጥረት፣ በበሽታ፣ በመሃይምነት . . .) የሚማቀቁባት አስከፊ ምድር የማድረግ፣ ከተቻለም ከነአካቴው ሃገር መሆን የማትችልበትን ሁኔታ መፍጠር ነው።

ኢትዮጵያን ለማጥፋት እንቅልፍ አጥተው ከሚባዝኑት ትውልደ ኢትዮጵያውያን መሃከል የተወሰኑት የአውሮፓ ፓርላማ ውስጥ ወዳጆች አላቸው። የአውሮፓ ፓርላማ ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያሳልፈው ውሳኔ መነሻ ሃሳብ የሚገኘው ከእነዚህ ፓርላማ ውስጥ ወዳጆች ካላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ነው። የአውሮፓ ፓርላማ በተዘዋዋሪ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ስር በሚገኘው የኤርትራ መንግስት እየተመራ መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል።

የአውሮፓ ፓርላማ ኢትዮጵያ ላይ ለሚያሳልፈው ውሰኔ፣ ሞሽን ወይም የወሳኔ ሃሳብ የሚቀርበው በአንድ ቢበዛ በሁለት የፓርላማው አባላት ነው። የውሳኔ ሃሳቡም የሚተላላፈውም ከ700 በላይ ከሆኑት የምክር ቤቱ አባላት ቢበዛ መቶዎቹ በተገኙበት ስብሰባ ነው። ከእነዚህ በመቶዎች ከሚቆጠሩት የውሳኔ ሃሳቡን የማይደግፉትም ቁጥር ቀላል አይደለም። በመሆኑም የፓርላማው ውሳኔ ብዙም ዋጋ የሚሰጠው አይደለም። ይሁን እንጂ “ነገሩ ነው እንጂ ጩቤ ሰው አይጎዳም” እንዲሉ፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ወዳጆቻቸው ላይ ተለጥፈው በመሰረተ ቢስ ወሬ ኢትዮጵያን ለመጉዳት የሚያደርጉት መፍጨርጨር ይቆጫል። በመሆኑም የአውሮፓ ፓርላማ ውሳኔ የተባለውን ሰነድ ይዘት መሰረተ ቢስነት ለማሳየት ያህል የተወሰኑ ጉዳዮችን ላነሳ ወድጃለሁ።

የህብረቱ ፓርላማ ባለፈው ዓመት አሳለፍኩት ካለውና መደርደሪያ ከማሳመር ያለፈ የትም ያልደረሰውን ውሳኔ ከመመልከት ልጀምር። ይህ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ የተላለፈ ውሰኔ የትም አልደረሰም። በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ተወካይ እንዲሁም የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሚስ ፌድሪካ ሞገሆሪኒ በኢትዮጵያ ባደረጉት የስራ ቆይታ ከኢፌዴሪ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት የደረሱባቸው የትብብር ስምምነቶች ለዚህ ማሳያነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ያም ሆነ ይህ፣ የአውሮፓ ፓርላማ ባለፈው ዓመት ጥር ላይ አሳልፎት ለነበረው ውሳኔ መነሻ ሆኑኝ ብሎ በምክንያትነት ከዘረዘራቸው መሃከል የተወሰኑትን በመጥቀስ ልጀምር። ኢትዮጵያ የብሄርና የሃይማኖት ብዝሃነት ያላት ሃገር ብትሆንም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላቸው በተለይ የኦሮሞና የሶማሌ (ኦጋዴን) ብሄሮች የአማራና የትግራይ ብሄሮችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል እየተገፉ ነው፤ የሚለው ይገኝበታል። አንድ ልጨምርላቸሁ እንግሊዛዊው የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ቡድን መሪ አንዳርጋቸው ጽጌ የሞት ቅጣት ተወስኖበት የውሳኔውን መፈጸም እየተጠባበቀ ነው፤ ይላል። ከውሳኔዎቹ መሃከል ደግሞ እንግሊዛዊው የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚ አንዳርጋቸው ጽጌ በአስቸካይ እንዲፈታ የሚለው ይገኝበታል።

በቅድሚያ ኢትዮጵያ የብሄሮቿን፣ ብሄረሰቦቿን መብት በህገመንግስት ያረጋገጠች ሃገር መሆኗ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን (ራሳቸውን በመረጧቸው ተወካዮቻቸው አማካኝነት የማስተዳደር፣ በቋንቋቸው የመስራት፣ ቋንቋቸውን ለትምህርት መስጫነት የመጠቀም፣ ታሪካቸውን የመንከባከብ፣ ባህላቸውን የማሳደግ . . .) እስከመገንጠል ያላቸው መብት በህገመንግስት ተረጋግጧል። ይህ ተግባራዊ ከተደረገ ሁለት አስርት ዓመታት አልፈዋል። የአውሮፓ ፓርላማ ባለፈው ዓመት የአማራና ትግሬ ብሄረሰቦችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል መብታቸው ተገፋ ያላቸው የኦሮሞና የሶማሌ ብሄሮች፣ ህዝባቸው የሚኖርበት ወሰን ላይ የራሳቸውን ክልላዊ መንግስት መስርተው ራሳቸውን እያስተዳደሩ ይገኛሉ። በኦሮሚያም ሆነ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስት ውስጥ የአማራ ወይም የትግራይ ክልል ምንም ስልጣን የላቸውም። እንግዲህ ለአማሮችና ለትግራዮች ሲባል ኦሮሞዎችና ሶማሌዎች የተገፉት በምን አኳኋን ይሆን?

ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚያሳልፈው የአውሮፓ ፓርላማ አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ እውነት ምንም እንደማያውቅ ያረጋግጣል። ፓርላማው ምንም በማያውቀው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ መድፈሩ ግን ይቅር የማያስብል ትልቅ ስህተት ነው። የፓርላማው አባላት እዚህ ስህተት ላይ የሚወደቁት ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለማፍረስ በአንድ ሰው ከሚመራው የኤርትራ መንግስት ጋር ከሚባዝኑት ቡድኖች የሚነገራቸውን ወሬ እንደወረደ ስለሚቀበሉ ነው። ለምሳሌ ከላይ የተጠቀሰውን ወሬ ያገኙት ራሳቸውን የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) እና የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ብለው ከሚጠሩ ቡድኖች ውስጥ ካሉ የፓርላማው አባላት ወዳጆች መሆኑን መገመት ምንም አያዳግትም።

ሌላኛውን እንመልከት፤ እንግሊዛዊው የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ቡድን መሪ አንዳርጋቸው ጽጌ የሞት ቅጣት ተወስኖበት የውሳኔውን መፈጸም እየተጠባበቀ ነው፤ ይልና እንግሊዛዊው የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚ አንዳርጋቸው ጽጌ በአስቸኳይ እንዲፈታ ሲል ይጠይቃል።

ይህ አቋም የታላቋ አወሮፓ ፓርላማ ጥቂት አባላት፣ አንድ እንግሊዛዊ ዜጋ የኤርትራ በረሃ ወርዶ የኢትዮጵያን መንግስት በሃይል ለመለወጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደተገቢ እርምጃ መቁጠራቸውን ያመለክታል። የፓርላማ አባላቱ አዙረው ቢመለከቱ ኖሮ በቅድሚያ እንግሊዛዊው አንዳርጋቸው ጽጌ ጠመንጃ ይዞ ኢትዮጵያውያን በውክልና ያቋቋሙትን መንግስት ለመናድ የኤርትራ ጫካ መግባት ለምን አስፈለገው? ብለው ይጠይቁ ነበር። የፓርላማው አባላት ይህን ወሬ የተቀበሉት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ካለው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ለኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ አገልጋይነት ካደረው ግንቦት 7 የተሰኘ ቡድን አመራሮች ነው፤ ከእነብርሃኑ ነጋ።

እንኳን እንግሊዛዊ፣ ኢትዮጵያዊም ቢሆን ከሃገሪቱ ስትራቴጂካዊ ጠላት ጋር አብሮ ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ ቢሞክር ድርጊቱ በወንጀል ያስጠይቀዋል። ህገመንግስታዊ ርአቱን የማስከበር ሃላፊነት ያለበት የኢፌዴሪ መንግስት በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ ግለሰቦችን በህግ እንዲጠየቁ ያደርጋል። እንግዲህ እንግሊዛዊው በፍርድ ቤት ቅጣት የተወሰነባቸው ከኤርትራ መንግስት ጋር ኢትዮጵያን ለማፈረስ በመሞከራቸው ነው። እንግሊዛዊው ሚስተር አንዳርጋቸው ይህን ሲያደርጉ የነበረው በድብቅ ሳይሆን፣ በይፋ በመገናኛ ብዙሃን መግለጫ እየሰጡ ነበር። የአውሮፓ ፓርላማ ጥቂት አባላት ይህን ይፋ ጉዳይ ችላ ብለው፣ ኢትዮጵያ የሚሰነዘርባትን ጥቃት በዝምታ እንድትመለከት የሚጠብቁ መሆናቸው እጅግ አስገራሚ ነው። ከዚህም አለፈው በይፋ የፍርድ ሂደት በቀረበ ማስረጃ ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጦ ህግ በሚያዘው መሰረት ቅጣት የተወሰነባቸው አንዳርጋቸው እንዲፈቱ ትእዛዝ ለማሳለፍ ሞክረዋል። እነዚህ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ምናልባት 20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ያበቃለት የአባቶቻቸውና የአያቶቻቸው ርካሽ የቅኝ ግዛት አመለካከት አልለቃቸው ብሎ ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ለአባቶቻቸውና አያቶቻቻው ያልተንበረከከች ሃገር መሆኗን ቢያስታወሱ ግን መልካም ነበር።

በጽሁፌ መግቢያ ላይ እንደጠቀስኩት አዙረው የማይመለከቱ ወይም የአያቶቻቻው ርካሽ የቅኝ ገዢነት አመለካካት ውርዴ የሆኑ፣ ከአጠቃላይ የአውሮፓ ፓርላማ መቀመጫ አንድ አምስትኛ ያህል የያዙ ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው አባላት ባለፈው ሳምንት ግንቦት 10፣ 2009 ዓ/ም ኢትዮጵያ ላይ ውሳኔ አሳልፈናል ብለዋል። የሰሞኑ የአወሮፓ ፓርላማ ውሳኔ ላይ ከሰፈሩት ጉዳዮች መሃከል የተወሰኑትን እንመልከት።

የአውሮፓ ፓርላማ ሰነድ ለውሳኔ መነሻ በሚል ከዘረዘራቸው ጉዳዮች መሃከል በ2006 እና 2008 ዓ/ም በኦሮሚያ ተቀስቅሶ የነበረው ሁከት ቀዳሚው ነው። ሚያዚያ 2006 ዓ/ም ላይ መንግስት የአዲስ አበባ ከተማን ወሰን በሃገሪቱ ትልቁ ብሄራዊ ክልል ወደ ሆነው ኦሮሚያ የሚያሰፋውን የተቀናጀ ማሰተር ፕላን ተግባራዊነት ይፋ ሲያደርግ ሁኔታዎች ተባባሱ ይላል። በማያያዝ 2008 ዓ/ም የአዲስ አበባ ወሰን፣ በመሬት ወረራ የ2 ሚሊየን ሰዎች መኖሪያ ወደሆነው የኦሮሚያ አካባቢ ሲስፋፋ በኦሮሚያ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ ይላል። የዶ/ር መረራ ጉዲናን እና ሌላ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የተባሉ ግለሰብን መታሰርም በመነሻነት ይጠቅሳል።

የአውሮፓ ፓርላማ፣ ኢትዮጵያ ላይ ውሳኔ ለማሳለፈ አነሳሳኝ በሚል የጠቀሳቸው እነዚህ ጉዳዮች ጠለቅ ብለን ስንመረምር መሰረተ ቢስ ሆነው እናገኛቸዋለን። በ2006 ዓ/ም በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ሁከት የተቀሰቀሰው፣ የአዲስ አበባንና የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተግባራዊነት ይፋ ስለተደረገ አልነበረም። ማስተር ፕላኑ እንኳን ተግባራዊነቱ ይፋ ሊደረግ፣ በመንግስት በኩል በረቂቅ ደረጃ መዘጋጀቱም አልተገለጸም ነበር። ሰነዱ ገና በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ያለ የህዝብ ውይይትን የሚጠብቅ ግርድፍ ረቂቅ ነበር። የረቂቅ ማሰተር ፕላኑ ይዘት በአዲስ አበባ አስተዳደርም ይሁን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ይፋ አልተደረገም። በይፋ ያለተገለጸውን ረቂቅ ማስተር ፕላን፣ የኦሮሚያ ህዝብ ህገመንግስታዊ መብቴ ተጥሷል የሚል ስጋት እንዲያድርበትና እንዲቆጣ በሚያደርግ አኳኋን ለህዝብ የገለጹት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ነበሩ። በወቅቱ ኦሮሚያ ውስጥ ሁከቱ የተነሳው በዚሀ አኳኋን ሃገር ውስጥና ውጭ ሃገር በሚገኙ ተቃዋሚዎች ተዛብቶ በቀረበው የማስተር ፕላን ይዘት ነበር። እናም የአውሮፓ ፓርላማ ይህን ገሃድ እውነት ክዶ ነው የተቀናጀ ማስተር ፕላኑ ተግባራዊነት በመንግስት ይፋ ሲደረግ በሚል የገለጸው። ይህ ውሸት ነው።

የዶ/ር መረራ ጉዲናና ፍቅሩ ማሩ መታሰርን በተመለከተ የሁለቱም ግለሰቦች ጉዳይ ገና በፍርድ ሂደት ላይ ያለ ነው። ዶ/ር መረራ የተከሰሱት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጁ ቡድኖች ጋር በመገናኘት ሲሆን ዶ/ር ፍቅሬ ማሩ ደግሞ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ነው።

የአውሮፓ ፓርላማ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች በተመሳሳይ ሁኔታ መሰረተ ቢስ የሆኑ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ ባሳለፈው ውሳኔ፤ ዶ/ር መረራ ጉዲና አና ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ በዋስ ተለቅቀው ክሳቸው ውድቅ እንዲደረግ። በሌሉበት የተከሰሱት ብርሃኑ ነጋና ጃዋር መሃመድ ጉዳያቸው ውድቅ እንዲደረግ ሲል ጠይቋል።

ልብ በሉ፤ ዶ/ር መረራ ጉዲና በይፋ የተቃውሞ ፖለቲካውን ጎራ ተቀላቅለው በህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሪነት በተንቀሳቀሱባቸው ያለፉ ሁለት አስርት ዓመታት ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አልተደረጉም። ተቃዋሚ ፓርቲን በመወከል በፌደራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ለአምስት አመታት መቆየታቸውም ይታወቃል። ዶ/ር መረራ የተቃውሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ በቆዩባቸው በእነዚህ አመታት በቧልት ጭምር ስርአቱን በይፋ በመቃወም የሚስተካከላቸው አይገኝም። ዶ/ር መረራ በሃገር ውስጥ ጋዜጦች ላይ ሳይታዩ ለአንድ ወር ያህል ከቆዩ በሃገር ውስጥ እንደሌሉ እስክንገምት ድረስ የፈቀዱትን ያለከልካይ ሲናገሩ ነው የቆዩት።  የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራምም የዶ/ር መረራን የቧልት ተቃውሞ ካላሰማ የሰራ አይመስለውም። ዶ/ር መረራ የተቃውሞ ፖለቲካ ቆይታቸው በፓርቲያችው ስር ከከፈተኛ አመራርነት ዝቅ ብሎ አያውቅም፤ ሁሌ ሊቀመንበር ናቸው፤ ሊቀመነበር ካልሆኑ ምክትል ሊቀመነበር ናቸው፤ ትንሽ ቆይተው ደግሞ እንደገና ሊቀመነበር ይሆናሉ።

ታዲያ በዚህ የፖለቲካ ቆይታቸው አንዴም ተከሰው አያውቁም። አንዳንድ ጊዜ በህግ ሊያስጠይቅ የሚችል ድርጊት ሲፈጽሙ መቆየታቸው ባይካድም ይህ ሁሉ በሆደ ሰፊነት እየታለፈ በተቃውሞ እንቅስቃሴያቸው የቆዩት አቋማቸውን የማራመድ በህገመንግስት የተረጋገጠ መብትና ነጻነት ስላላቸው ነው። ዶ/ር መረራ ያልታሰሩተ ስለተፈሩ አይደለም። ወይም ውጭ ሃገር ሆነው የሚጮሁላቸው አጋሮች ስላላቸው አይደለም። ኢትዮጵያ ሰዎች በአመለካከት የሚታሰሩባት ሃገር ብትሆን ኖሮ፣ ቀድመው ይታሰሩ የነበሩት ዶ/ር መረራ ነበሩ።

አሁን ግን በወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸዋል፤ የአስቸካይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተደነገገውን በአሸባሪነት ከተፈረጁ ቡድኖች ጋር የመገናኘት ክልከላን ጥሰው ስለተገኙ። ዶ/ር መረራ ለአውሮፓ ህብረት አባላት ስለኢትዮጵያ ስለተናገሩ አይደለም የተጠየቁት። ከአትሌት ሌሊሳ ፈይሳ ጎን ተቀምጠው ስለታዩም አይደለም። ሌሊሳን የፈረጀውም ወደሃገር እንዳይመጣ የከለከለውም የለም። ዶ/ር መረራ ከኤርትራ መንግስት ጋር በመተባባር የኢፌዴሪን ህገመንግስታዊ ስርአት ለማፍረስ በይፋ የሚንቀሳቀሰውና በዚህ ድርጊቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ግንቦት 7 የተባለ ቡድን መስራችና መሪ ከሆኑት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይል ትግሉን እመራለሁ በሚል አስመራ ከከተቱት ብርሃኑ ነጋ ጋር ተገናኘተው ስለመከሩ ነው። እስካሁንም በስራ ላይ ባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይህ ድርጊት በህግ ያስጠይቃል። ተጠርጣሪውን በዋስ የመልቀቅ፣ ክሳቸውን ውድቅ የማድረግ ስልጣን የፍርድ ቤት ብቻ ነው። እርግጥ አቃቤ ህግ ለጠረጠረበት ወንጀል በቂ ማስረጃ የለኝም ብሎ ካመነ ክሱን ሊያቋርጥ ይችል ይሆናል።

የአውሮፓ ፓርላማ ይፈቱ ሲል ትእዛዝ ያስተላለፈላቸው ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ደገሞ በሙስና ወንጀል ነው የተከሰሱት። ዶ/ር ፍቅሩ ነጋዴ እንጂ ፖለቲከኛም አይደሉም። ብርሃኑ ነጋና ጃዋር መሃመድ ህገመንግስታዊ ስርአቱን ሽብርተኝነትን ጨምሮ በማንኛውም መንገድ ለመናድ በይፋ አውጀው እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል። በ2008 ዓ/ም በኦሮሚያና በጥቂት የአማራ ክልል አካባቢዎች ህዝቡ ያነሳውን ተገቢ ተቃውሞ በመጥለፍ ወደአውዳሚ ሁከትነት መቀየራቸውንና አውዳሚ ሁከቱን በተለያየ መንገድ መምራታቸውን የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች አሉ።

እንግዲህ የአወሮፓ ህብረት በተጨባጭ ህግን በመተላለፍ ሊያስከስስ የሚችል ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጡ ግለሰቦችን (በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩን ጭምር) ፍቱ የሚል ቀጭን ትእዛዝ ነው ያስተላለፈው። ይህ የአወሮፓ ፓርላማ አካሄድ የህግ የበላይነት መርህን የሚጻረር፣ የአንድ ሃገር የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ፍጹም ተገቢ ባልሆነ አኳኋን ጣልቃ እንደመግባት የሚቆጠር ድርጊት ነው። ይህ የአውሮፓ ፓርላማ ድርጊት ጸያፍም ነው። የአውሮፓ ፓርላማ የተወሰኑ አባላት፣ የዚህ አይነት ግዙፍ ስህተት የፈጸሙትና የሃገሪቱን የህግ የበላይነት የተዳፈሩት ተቃዋሚ ነን በሚሉ የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች ወሬ ተሞልተው ነው። የሚያገናዝበ አእምሮ እያላቸው እንደቴፕሪከርደር የነገሯቸውን በሙሉ ተቀብለው መሞላታቸው ግን አሳፋሪ ነው።

የአውሮፓ ፓርላማ የራሱን አቋም የሚጻረር ውሳኔም አሳልፏል። በአንድ ወገን፣ ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተቀስቅሶ በነበረው ሁከት የደረሰው ጉዳት በገለልተኛ አካል ይጣራ እያለ እየጠየቀ፤ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በገለልተኝነት ጉዳዩን መርምሮ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ አጥፊዎችን በተመለከተ የሰጠው አስተያያት ተግባራዊ ይደረግ ሲል አሳስቧል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስተያያት ተግባራዊ መደረግ ያለበት ከሆነ፣ ሪፖርቱ ተቀባይነት አለው ማለት ነው። ሪፖርቱ ተቀባይነት ካለው ደግሞ፣ ተጨማሪ የማጣራት ስራ ማከናወን ምንም ጥቅም የለውም። ጉዳዩ በትክክል ተመርምሮ ችግሮች ተለይተው ይፋ ተደርገው ባለበትና በህግ የሚጠየቁ አካላት ተጠያቂ ይሆናሉ ተብሎ በሚጠበቅበተ ሁኔታ፣ ሌላ ምርመራ ማካሄድ ዓላማው እውነትን ፍለጋ ሳይሆን ነገር ፍለጋ ነው። ምርመራ አድርጌያለሁ በሚል ሰበብ እንደተለመደው አስቀድሞ ውጭ ሃገር የተጻፈ ሪፖርት በማቅረብ ተገቢ ያልሆነ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘ ከማሰብ የተለየ ዓላማ የለውም። የአውሮፓ ፓርላማ ያሳለፈው በውሸት ወሬ የታጨቀ መሰረተ ቢስ ውሳኔ፣ የውሸት የሰብአዊ መብት ምርመራ ሪፖርትም በተመሳሳይ ሁኔታ ሊቀርብ እንደሚችል በአሰረጂነት ሊጠቀስ ይችላል።

በመጨረሻ የአወሮፓ ፓርላማ የኢትዮጵያ ብሄሮችን እኩልነት አሰመልክቶ የያዘውን አቋም እንመለከት። ፓርላማው፤ የተለያዩ ብሄሮች እኩል የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል መብቶች እንዲኖራቸው ይደረግ ብሏል። እንግዲህ የኢትዮጵያ ብሄሮች እኩልነት ከውጭ በመጣ ትእዛዝ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦችን አባላት ከፈተኛ የህይወት መስዋዕትነት በጠየቀ ትግል ከተረጋገጠ እነሆ ሃያ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል። አዲሲቱ ኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በምርጫቸው፣ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነት ለመኖር ተስማምተው የመሰረቷት ሃገር ነች። አዲሲቱ ኢትዮጵያ ሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች በየአካባቢያቸው ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ፣ በቋንቋቸው እየሰሩ፣ ባህላቸውን እያጎለበቱ፣ ታሪካቸውን እየተንከባከቡ፣ ህዝባቸውን የተፈጥሮ ሃብቱ ተጠቃሚ እያደረጉ . . . የሚኖሩባት ሃገር ነች። በአዲሲቱ ኢትዮጵያ አንዱ የሌላውን መብት እንዲጥስ ማደረግ የሚያስችል ሁኔታ የለም። አንዱ የሌላውን መብት የማይጥስ መሆኑን ለማረጋገጥ በህገመንግስት የተቀመጠ  ዋስትናም አለ። ይህም የተገፋ ወይም የተጨቆነ ብሄር፣ ጥያቄው የህዝብ መሆኑን በሚያረጋግጥ አኳኋን የመገንጠል ህገመንግስታዊ መብት ያለው መሆኑ ነው።

እናም የአውሮፓ ፓርላማ የኢትዮጵያ ብሄሮች የማንንም እርዳታ ሳይጠይቁ የመሰረቱትን የእኩልነት ስርአት የሌለ በማሰመሰል፣ በአውቅላቹሃለሁ ስሜት እኩልነት አስፍኑ! በሚል ያስተላለፈው ትእዛዝ ትዝብት ላይ ይጥለዋል፤ አዛኝ ቂቤ አንጓች። ከሁሉም የሚያስገርመው የአውሮፓ ፓርላማ ኢትዮጵያ ላይ ውሳኔውን እንዲያሳልፍ በወሬ የሚሞሉት ቡድኖች፣ የብሄሮች እኩልነት የተረጋገጠበትን ፌደራላዊ ስርአት የሚቃወሙና የአንድ ብሄርና ሃይማኖት የበላይነት የሰፈነበትን አሃዳዊ ስርአት የመመሰረት ህልም ይዘው የሚባዝኑ መሆናቸው ነው። የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዘንድ ተአማኒ እንዲሆን ከፈለገ በመጀመሪያ እነዚህን ትምክህተኞች መስማት ያቁም።

በአጠቃላይ፤ የአውሮፓ ፓርላማ ኢትዮጵያ ውስጥ የመረጠው ህዝብ ያለ የመስል በየዓመቱ ኢትዮጵያ ላይ ለማሳለፍ የሚሞክረው ውሳኔ፣ በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ምንም እንደማያውቅ ያመለክታል። በተጨባጭ ያለውን ሁኔታ ከመመረመር ይልቅ ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ውሳኔ የሚያሳልፍ መሆኑንም ያመለክታል። ምናልባት ይህ ሁኔታ የተወሰኑ አባላቱ አሁንም ካልለቃቸው የአባቶቻቸውና አያቶቻው የቅኝ ገዢነት ርካሽ አመለካከት የመነጨም ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ምናልባት የፓርላማው አባላት ራሳቸው ወሳኔው ምንም ተጽእኖ እንደሌለው ስለሚያውቁ፣ አውሮፓና አሜሪካ የሚኖሩ የሌላ ሃገር ዜግነት ያላቸውን የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ጓደኞቻቸውን ለማስደሰት ያህል ብቻ ያደረጉት ሊሆንም ይችላል። ዋናው ነገር ግን የፓርላማው ውሳኔ መሰረት የሌለው፣ ተጽእኖ የማሳደርም አቅም የሌለው ከንቱ የከንቱ ከንቱ ወሬ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy