Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከአዲስ አበባ እስከ ግብፅ-ካይሮ

0 375

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከአዲስ አበባ እስከ ግብፅ-ካይሮ

ሰለሞን ሽፈራው

ከላይ በፅሁፌ ርዕስ የተመለከተውን የቦታ ርቀት ተከትሎ የተሰመረ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሳነሳ ምን ለማለት እንደፈለግኩ የማይገባው አንባቢ ይኖራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ግብፅ ካይሮ የሚለው የመጣጥፌ ርዕስ፤ በተለይም የዓባይ ተፋሰስ ዋነኞቹ ባለድርሻ ሀገራት ተደርገው የሚቆጠሩት ኢትዮጵያ፤ ሱዳንና ግብፅ በጥብቅ ተፈጥሯዊ ቁርኝት የተሳሰሩበትን የውሃ ጂኦፖለቲካ ያመለክታልና ነው፡፡

ስለሆነም ከተጠቃሾቹ ሶስት የዓባይ ተፋሰስ ዋነኛ ባለድርሻ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በጉባ ሸለቆ የምትገነባውን ግዙፍ የህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በተመለከተ፤ የለየለት አቋም መያዝ ያቃታት መስላ ስለምትታየው ግብፅና የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ስለሚከተለው መርህ ጥቂት ነጥቦችን አነሳ ዘንድ መልካም መስሎ ቢሰማኝ ነው እንዲህ መንደርደሬ፡፡ እንግዲያውስ አሁን በቀጥታ የማልፈውም፤ በተለይ የኢትዮ-ግብፅ መንግስታት ሀገራችን በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባቸው ስላለው ታላቁ የህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ጉዳይና እንዲሁም ደግሞ ስለአጠቃላይ ግንኙነታቸው የያዙትን አቋም በወፍበረር ለመቃኘት ወደምሞክርበት ነጥብ ይሆናል፡፡

ስለዚህም፤ ከአዲስ አበባ እስከ ግብፅ ካይሮ ድረስ ያለውን የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የውሃ ጂኦፖለቲካዊ ትስስርና ዛሬ ላይ የሚገኝበትን ተጨባጭ ገፅታ፤ ከሞላ ጎደል ለመዳሰስ ያህል በቅደም ተከተል መመልከት ያለብንን አንኳር – አንኳር ነጥቦች ማንሳት ተገቢ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ እናም ከዚህ አኳያ ሲታይ በቅድሚያ መነሳት የሚኖርበት ቁልፍ ጥያቄ፤ ለመሆኑ ዋነኞቹን የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የጎሪጥ እንዲተያዩ አድርገዋቸው የቆዩት የዘመነ ቅኝ ግዛት ኢ-ፍትሐዊ ውሎች በሚያሻማ መልኩ መቀልበሳቸውን አምኖ መቀበል ይቻላል ወይ? የሚለው ይመስለኛል፡፡ ይህን ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ ሆኖ የታየኝም ደግሞ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይልቅስ ከዋነኞቹ የናይል ተፋሰስ ባለድርሻ ሀገራት መካከል፤ ኢትዮጵያና ሱዳን፤ የእውነታውን መለወጥ አምነው ስለመቀበላቸው የመረጋገጡን ያህል፤ ሌላኛዋ ባለድርሻ ሀገር ግብፅ ግን ለፍርድ የሚያስቸግር አቋም እንደያዘች ለመቀጠል የወሰነች ትመስላለችና ነው እኔም ጉዳዩን ማንሳቴ፡፡

ምንም እንኳን የምስራቅ ናይል ሀገራት በመባል የሚታወቁት ኢትዮጵያ፤ ሱዳንና ግብፅ፤ በዓባይ ወንዝ ላይ ሀገራችን እየገነባች ያለችውን የህዳሴ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ለጋራ ጥቅም በሚውል መልኩ ዳር ስለማድረስ ጉዳይ ምክረ ሃሳብ የሚለዋወጡበትን የሶስትዮሽ መድረክ ውሳኔዎች፤ የፕሬዚዳንት አልሲሲ መንግስትም ጭምር እንደሚቀበላቸው ተደርጎ የሚነገርበት ዲፕሎማሲያዊ አግባብ ቢኖርም ቅሉ፤ አንዳንድ የካይሮ ፖለቲከኞች የሚያሳዩት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ግን፤ አሁንም ከዘመነ ቅኝ አገዛዙ አስተሳሰብ መላቀቅ እንዳቃታቸው ያመለክታል፡፡ በዚህ ረገድ የሚታወቁ ግብፃውያን የፖለቲካ ልሂቃን ከህዳሴው ግድብ የግንባታ ሂደት በስተጀርባ የጥፋት ሴራ የሚዶልቱበትን የተቃውሞ እንቅስቃሴ በተመለከተ የካይሮው መንግስት “ፈፅሞ እጄ የለበትም” እያለ ሲያስተባብል መደመጡ ባይካድም፤ ይህን ምላሽ አምኖ መቀበል እንደሚያዳግት የሚናገሩ ታዛቢዎች ጥቂት አይደሉም ማለት ይቻላል፡፡

የግብፅ መንግስት፤ እንደ ኦ.ነ.ግ እና ግንቦት ሰባት ዓይነቶቹን ሽብር ፈጣሪ የፖለቲካ ቡድኖች በማስተባር ኢትዮጵያን የማተራመስ ጥረት አያደርግም ብሎ ማመን እንደሚያስቸግር የሚናገሩት የቀጠናው ፖለቲካ ታዛቢዎች፤ አስተያየታቸውን በምክንያታዊ መከራከሪያ አስደግፈው የሚያቀርቡበት አግባብም “የካይሮውን ፖለቲካ በበላይነት እንዲቆጣጠሩ ዕድል የሚገጥማቸውን መሪዎች ሁሉ የሚያመሳስላቸው አንድ መሰረታዊ ባህሪ ቢኖር የዓባይ ተፋሰሱን ጉዳይ የሚያዩበት መነፅር ነው” የሚለውን ነጥብ ከነታሪካዊ ዳራው በማውሳት ነው፡፡ እናም እንደነርሱ እምነት ከሆነ፤ አሁን በግብፅ አረብ ሪፐብሊክ ስልጣን ላይ ያለው የፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ዓልሲሲ መንግስትም፤ ከቀደሙት የካይሮ ፖለቲካ መሪ ተዋኒያን የተለየ ፖሊሲ (በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ) ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

በእርግጥም ደግሞ የቀድሞው የጦር ጀነራል ወታደራዊ ዩኒፎርማቸውን አውልቀው በመጣል የፕሬዚዳንትነቱን መንበረ ስልጣን ከተቆጣጠሩ ጀምሮ እያሳዩን ያሉትን ያለየለትን አቋም ልብ ብሎ ለሚታዘብ ሰው ፤ ከላይ የተመለከተውን አስተያየት የሚሰነዝሩት ወገኖች እንዳልተሳሳቱ ነው መረዳት የሚቻለው፡፡ ምክንያቱም የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ፤ በአንድ በኩል ኢትዮጵያና ሱዳን የተስማሙበትን በፍትሐዊ የውሃ ሀብት ክፍፍል ላይ የተመሰረተ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚቀበሉ ለማስመሰል እየሞከሩ በሌላ በኩል ግን፤ የተለመደውን የካይሮ መንግስታት ፀረ ኢትዮጵያ አቋም የሚያንፀባርቅ ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ ደባ የመፈፀም አዝማሚያ ያለውን አፍራሽ እንቅስቃሴ ከማድረግ ተቆጥበው አያውቁም ማለት ይቻላልና ነው፡፡

ለአብነት ያህልም፤ ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር የሚጋሩትን የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች ወደ ካይሮው ቤተመንግታቸው እየጋበዙ በአዲስ አበባ ላይ ለሚያውጠነጥኑት እቺን ሀገር የማተራመስ ፖለቲካዊ ሴራቸው ተባባሪ ሆነው እንዲገኙ ለማድረግ ያለመ ዲፕሎማሲያዊ የማግባባት ስራ መስራትን ይሆነኝ ብለው ከተያያዙት ሰነባብተዋል፡፡ ስለሆነም፤ ከኬኒያና ከሰሜኑ ሱዳን መንግስታት በስተቀር፤ የሁሉም የኢትዮጵያ ተጎራባች ሀገራት ፕሬዚዳንቶች በሙሉ፣ ተቀራራቢ ሊባል በሚችል ጊዜ ውስጥ ካይሮን እንዲጎበኙ ከአልሲሲ መንግስት የቀረበላቸውን ግብዣ እየተቀበሉ ወደግብፅ የሔዱበት ሁኔታ መኖሩን ነው ከታመኑ ምንጮች የተገኘ መረጃ የሚያመለክተው፡፡ ደግነቱ ግን፤ በዚህ በያዝነው 2009 ዓ.ም ካይሮ ደርሰው ከተመለሱ የጎረቤት ሀገራት ፕሬዚዳንቶች መካከል አንዳቸውም የግብፅን ፀረ ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ማስፈፀሚያ የሚሆን ትብብር ለማድረግ እንዳልፈቀዱ ታውቋል፡፡

ስለዚህም፤ የፕሬዚዳንት አልሲሲ መንግስት ቀሪ ተስፋ አሁንም ከሻዕቢያ መራሹ የኤርትራ ግፈኛ አገዛዝ ጋር ያለውን ወዳጅነት ማደልደልና አቶ ኢሳያስን ለፀረ ኢትዮጵያው የትርምስ ስትራቴጂያቸው ማስፈፀሚያ አድርገው መጠቀም ብቻ ሊሆን እደሚችል ይጠበቅ ነበር፡፡ ይሄው ግምት ተግባራዊ ይሆን ዘንድም፤ እነሆ ከሰሞኑ የወጡ የዜና ማሰራጫ ምንጮች ግብፅ እስከ 30 ሺህ የሚደርስ ጦር ሰራዊቷን ኤርትራ ውስጥ ልታሰፍር ስለመሆኗ ዘግበዋል፡፡

ለምሳሌ ያህልም፤ ቅዳሜ ሚያዝያ 14 ቀን 2009 ዓ.ም ታትሞ የወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ “ግብፅ 30 ሺህ ጦር በኤርትራ ልታሰፍር ነው ተባለ” በሚል ርዕስ የፊት ለፊት ገፁነ ላይ የፃፈውን ዜና ማስታወስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ሳምንታዊው አዲስ አድማስ ጋዜጣ “ሱዳን ትሪቡን” የተሰኘውን የዜና ማሰራጫ አውታር በምንጭነት ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ በቅርቡ ወደ ኤርትራ የተጓዘ አንድ የግብፅ መንግስት የልዑካን ቡድን፤ ከ20 ሺህ እስከ 30 ሺህ የሚደርስ ቁጥር ያለውን ሰራዊት በኤርትራ ዳህላክ ደሴት አካባቢ ለማስፈር የሚያስችል ይሁንታን አግኝቶ ተመልሷል ነው የተባለው፡፡ የፕሬዚዳንት አልሲሲ ግብፅ ቀደም ሲል ይሄንኑ ጦር ሰፈር የማግኘት ጥያቄዋን ለሶማሊያ፤ እንዲሁም ደግሞ ለሱማሌ ላንድና ለጅቡቲ መንግስታት አቅርባ ሳይሳካላት መቅረቱንም ጭምር ዘገባው አመልክቷል፡፡

እንግዲህ ግብፅ ይህን ያህል ዙሪያ ጥምጥም መሔድን የፈለገችበት ምክንያት የኢትዮጵያን የህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ የግንባታ ስራ በውጥኑ የማስቀረት ዓላማ ስላላት ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች የመኖራቸውን ያህል፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የኢፌዴሪ መንግስት ግን ሁኔታው እንብዛም ያሳሰበው አይመስልም፡፡ ለዚህ ደግሞ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስታራችን አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ሚያዚያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት ወቅታዊ መግለጫ ላይ ይሔው የግብፅ በአካባቢው ሀገራት የማንዣበብ ጉዳይ ተነስቶላቸው “በኛ እምነት የግብፅ መንግስትም ሆነ ሌሎች የባህረ ሰላጤ ሀገራት ኤርትራ ውስጥ ጦራቸውን ስላሰፈሩ ብቻ ኢትዮጵያን ለመተናኮል ነው ብሎ መውሰድ ተገቢ አይመስለንም” ሲሉ መደመጣቸውን ማስታወስ ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በሰሞነኛው መግለጫቸው፤ የኢትዮ-ግብፅን መንግስታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተመለከተ የሰጡት ወቅታዊ ማብራሪያ፤ ሀገራችን ከዋነኞቹ የዓባይ ተፋሰስ ባለድርሻ ሀገራት አኳያ የምትከተለውን በፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመሰረተ መርህ እንደማትቀይር ያስገነዘበ ሆኖ ነው እኔ በበኩሌ ያገኘሁት፡፡ ይህ የመንግስታችን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ስታርቴጂ መሰል ጉዳዮችን ሰከን ባለ የሰጥቶ መቀበል መርህ የመያዝ አግባብ የሚነቀፍ እንዳልሆነ ብረዳም ቅሉ፤ ግን ደግሞ እንብዛም ሆድ ማስፋትን ሁሌም የሚያዋጣ ነው ብሎ ማመን አደጋ ሊያስከትልብን እንዳይችል እሰጋለሁ፡፡

በተረፈ ግን፤ እኔ እንደ አንድ የዓባይ ተፋሰስን ባለድርሻ ሀገራት የውሃ ነክ ጂኦ ፖለቲካዊ ትስስር የሚመለከቱ የመንግስት ለመንግስት ውይይቶችን ሂደት ከመከታተል ቦዝኖ እንደማያውቅ ኢትዮጵያዊ ዜጋ፤ ሳላደንቅ ማለፍ የማይኖርብኝ ጉዳይ አለ፡፡ እርሱም ደግሞ የኢፌዴሪ መንግስት ሀገራችን ከዓባይ ወንዝ አንጡራ የውሃ ሀብቷ ላይ ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን እንድትቋደስ ለማድረግ ሲል፤ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ መገንባት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፤ ፕሮጀክቱ የመላው ኢትዮጵያውያን ህዝቦች ፀረ ድህነት ትግል ዓይነተኛ መገለጫ ተደርጎ ይወሰድ ዘንድ የመሪነት ሚናውን በመጫወት ረገድ ያሳየው ጥረት አድናቆት ሊቸረው የሚገባ ሆኖ አግኝቸዋለሁና ነው፡፡

እንደኔ እምነት ከሆነ መቸስ፤ ይህ መንግስታችን ጉዳዩን በተለየ ጥንቃቄ የያዘበት የኃላፊነት ስሜት ባይታከልበት ኖሮ ፤ የግድቡን የግንባታ ሒደት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የማስቆም ፍላጎት ያላቸው ግብፃውያን ፖለቲከኞች፤ ከመጋረጃው በስተጀርባ የሚዶልቱብን የጥፋት ሴራ ይሳካቸው ነበር ባይ ነኝ፡፡ ይህን የምልበት ዋነኛ ምክንያትም፤ ኦ.ነ.ግ.ን የመሳሰሉት በለየለት የሀገር ክህደት ተግባር ላይ መሰማራትን እንደ የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ መገለጫ አድርገው የሚቆጥሩ ፅንፈኛ ቡድኖች፤ ለየትኛውም ፀረ-ኢትዮጵያ የውጭ ሃይል በጉዳይ አስፈፃሚነት ከመላላክና እቺን ሀገር ሰላም ለመንሳት ከመሞከር እንደማይቆጠቡ ይታወቃልና ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ረገድ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እጅ ለእጅ ተያይዘው በመቆም ዓባይ ወንዝ ላይ እየተሰራ ያለውን ታላቅ ታሪክ ለማስቀጠል መቻላቸው አድናቆት አይበዛበትም፡፡

ይልቁንም ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፤ አሁን ሰሞኑን በኢትዮ ግብፅ መንግስታት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ሲባል ወደ ካይሮ ተጉዘው ከፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በተወያዩበት ወቅት “የእኛና የእናንተ ዕጣ ፈንታ በጥብቅ የተሳሰረ ነው፡፡ ስለሆነም ወይ አብረን እንለማለን፤ ወይም ደግሞ አብረን እንጠፋለን እንጂ አንዱ አገር ጠግቦ እያደረ አንዱ አገር ግን የሚራብበት ሁኔታ ፈፅሞ ሊኖር አይችልም” ሲሉ የተናገሩትን ጠጣር እውነት ከተለመደው የዲፕሎማሲ ቋንቋ ላቅ ያለ ሆኖ እንዳገኘሁት በዚህ አጋጣሚ ልገልፅላቸው እወዳለሁ፡፡   

በእርግጥም ደግሞ ክቡር ዶክተር ወርቅነህ አክለው እንዳሉት፤ እኛ ከአዲስ አበባ እስከ ግብፅ ካይሮ ድረስ የተሰመረ ተፈጥሯዊ የጋራ ዕጣፈንታ በጥብቅ ያስተሳሰረን የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ህዝቦች፤ አብረን ከመስጠም ይልቅ፤ አብረን የምንዋኝበትን የዕድገትና የብልፅግና ጉዞ ማስቀጠል እንደሚጠበቅብን የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ፤ አሁንም ድረስ በ1992 እና እንዲሁም ደግሞ በ1959 ዓ.ም የተፃፉ የዘመነ ቅኝ ግዛት ኢ-ፍትሐዊ ውሎችን እንደ ሕጋዊ የስምምነት ሰነድ ለመቁጠር ሲቃጣቸው ለሚስተዋሉ አንዳንድ የካይሮ ፖለቲከኞች፤ እቅጩን ተናግሮ አደብ የሚስገዛልንን አካል በእጅጉ እንሻለን፡፡   መዓሰላማት!  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy