Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከ237 ሚሊየን ብር በላይ ጉድለት የተገኘባቸው ተቋማት የጉድለቱን መንስኤ እና ተጠያቂ እስካሁን አላሳወቁም

0 321

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በበጀት አመቱ ግማሽ ወራት ከ237 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብና ንብረት ጉድለት ተገኝቶባቸው ስለጉዳዩ በአንድ ወር ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርጉ በአዲስ አበባ ከንቲባ ከታዘዙት 20 መስሪያ ቤቶች 18ቱ እስከ ዛሬ ትዕዛዙን አልፈፀሙም።

ከሁለት ወር በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ኦዲተር በአዲስ አበባ ምክር ቤት ተገኝቶ በከተማዋ ያሉ የተለያዩ ተቋማትን የኦዲት ሪፖርት ሲያቀርብ የገንዘብ ጉድለት፣ ያለደረሰኝ የደመወዝና የአበል ክፍያ፣ ከደንብና መመሪያ በውጪ የሆኑ ጨረታዎች፣ የንብረት አለማስመለስና የመሳሰሉት ተነስተው ነበር።

የምክር ቤት አባላትም በቀረበው ሪፖርት ላይ ሀሳብና አስተያየት ከመስጠት ባለፈ ተጠያቂው እንዲለይ ጠይቀዋል። ችግሩ በማን እና በምን ምክንያት ተፈጠረ የሚለውን ዝርዝር ምላሽ ይሰጥበት የሚል አቋም ይዘው መለያየታቸውም ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማም ተቋማቱ በራሳቸው በኩል ይህን የመለየት ስራ እንዲሰሩ በዝርዝር የሚከታተልና ሪፖርት የሚያደርግ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሪፖርት እንዲያቀርብ የሚል የአንድ ወር የጊዜ ቀጠሮን አስቀምጠው ነበር።

ይህ ከተባለ ሶስተኛው ወሩን ቢይዝም ከጥቂት ተቋማት በስተቀር አብዛኞቹ ምንም አይነት ሪፖርት አላደረጉም ብለዋል የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ኦዲተር ፅጌወይኒ ካሳ።

በኦዲት ግኝቱ መሰረት ወደ 137 ሚሊየን ብር የሚጠጋውን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በጥሬ ገንዘብና በንብረት ማስመለስ የሚገባውን ሳያስመልስ መቅረት፤ ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ የ12 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግዢ የፈጸሙ 8 ተቋማት ውስጥም የከተማዋ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንና አዲስ ዙ ፓርክ ቀዳሚውን ቦታ የያዙ ናቸው።

ከ87 ሺህ ብር በላይ ህጋዊ ባልሆነ ደረሰኝ ከፍያ የፈጸሙና ከ176 ሺህ ብር በላይ ያለ አግባብ ደመወዝና አበል የከፈሉ ተቋማት ደግሞ የዳግማዊ ሚኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት፣ የራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል፣ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክትና የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ተጠቃሾቹ ናቸው።

በአጠቃላይ በክፍተቱ ከተካተቱ 20 ያህል ተቋማት በተገቢው ደረጃ ሪፖርት ማድረግ ቢኖርባቸውም ሁለት ተቋማት ብቻ ናቸው ይህን ማድረግ የቻሉት።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ክፍተቱን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጣርቶ ለማጠናቀቅ አልተቻለም በሚል ሪፖርት መሰረት ተጨማሪ ጊዜ መሰጠቱን ገልፀዋል።

ከንቲባው ይህን ይበሉ እንጂ ችግሩ ተቋማቱ የክፍተቱን ተጠያቂዎች የመለየትና አሳልፎ የመስጠት ስራ እንዲሰሩ የተባለውም ተግባራዊ አልተደረገም።

ከንቲባ ድሪባ ኩማ ምንም እንኳን ከተባለበት ቢዘገይም የተሰጠው አቅጣጫ ግን ተግባራዊ መሆኑ አይቀርም ብለዋል።

ቀጣዩ የከተማው ምክር ቤት ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት ውጤቱ የሚታወቅ ይሆናልም ነው ያሉት ከንቲባው።

የገንዘብ እና ንብረት ጉድለቱ ሪፖርት ተጣርቶ ይፋ ሲደረግ በማስረጃ ከሚቀርቡ አሰራሮች ውጪ የሆነ አሰራርን ተከትሎ የተገኘ አመራርም ሆነ ፈጻሚ ተጠያቂ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።

ከንቲባ ድሪባ እርምጃው አስተዳደራዊ ብቻ ሳይሆን በህግ መጠየቅንም ያካትታል ነው ያሉት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy