ክቡር የኢፌዲሪ ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ የደስታ መግለጫ
ክቡር የኢፌዲሪ ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገለጹ፡፡ ጠ/ሚ ሃይለማርያም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ላሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች በሙሉ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡ ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ የዶ/ር ቴድሮስን መመረጥ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ምርጫው ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ያላትን ተቀባይነት ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም መመረጥ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ ታላቅ ድል ነው ብለዋል፡፡ ውጤቱ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜያት በዲፕሎማሲው መስክ ላስመዘገበችው ስኬት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ይህ ውጤት በ70 ዓመት በአለም አቀፍ የጤና ድርጅት ታሪክ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊም አፍሪካዊም ዳይሬክተር ጄኔራል ያደርጋቸዋል፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ የተመረጡት በድርጅቱ ውስጥ ለውጥ ማምጣት የሚችል ዳ/ጄኔራል ያስፈልጋል የሚል አስተሳሰብ ተቀባይነት እያገኘ በመምጣቱ ሲሆን በጤናው መስክ አገራችን እንድታስመዘግብ ያስቻሉትን ከፍተኛ ውጤት በድርጅቱ ይደግማሉ ተብሎ ይጠበቃል።