Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወጣትነት እና የዘመን መንፈስ

0 1,880

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወጣትነት እና የዘመን መንፈስ

በሰው ልጅ የህይወት ዘመን ውስጥ ወርቃማው የዕድሜ ክልል ወጣትነት ነው ቢባል ከእውነት መራቅ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ “በጉብዝና ወራት ፈጣሪህን አስብ” እንዳለው ቅዱስ መፀሐፍ፣ ማናችንም ብንሆን የወጣትነት ዕድሜያችን ላይ ስላሳለፍነው ህይወት መለስ ብለን ለማስታወስ ስንሞክር ያ ዘመን በእርግጥም ወርቃማ ሊባል የሚችል ሆኖ ይሰማኛልና ነው፡፡ ይህን ስል ግን የወጣትነት ዘመናችን ከእግር እስከ ራሱ በመልካም የህይወት ገፅታዎች የተሞላ ብቻ ተደርጎ ይወሰዳል ለማለት እንዳልሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡

ይልቁንስ፤ ማንኛውም ሰው ቢሆን ከአጠቃላይ የህይወት ዘመኑ ይበልጥ ደስተኛና በትኩስ ሃይል የተሞላ ሆኖ የሚታይበት የዕድሜ ክልል ወጣትነት ነው ተብሎ መታመኑ ተገቢነት እንዳለው ለመጠቆም ያህል ነው፡፡ እንጂማ የሰው ልጅ ዘለቄታዊ ዕጣፈንታ የተቃና መሆን ወይም ደግሞ አለመሆን የሚወሰነው የወጣትነት ዕድሜ ክልል ትኩሳት ሊያስከትልብን ከሚችለው ፈርጀ ብዙ ፈተና በተለየ ጥንቃቄ ማለፍ ሲቻል እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ እንግዲያውስ፤ ወጣትነትና የዘመን መንፈስ በሚለው ርዕስ ዙሪያ የሚያጠነጥን መሰረተ ሃሳብ አንስቼ ከላይ በመግቢያዬ ስለተጠቆሙት ነጥቦች የተሻለ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የምሞክርበትን ሃተታ ለማቅረብ ፈልጌያለሁና ነው በዚህ መልኩ መንደርደር የመረጥኩት፡፡

ስለዚህም፤ አሁን በቀጥታ ወደ ዋናው ነጥብ አልፍና ሚያዝያ 27 ቀን 2009 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከበረውን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች በዓል ምክንያት በማድረግ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ጠቃሚ መልዕክት ሲያስተላልፉ የተደመጡበትን ንግግር ለማስታወስ እሞክራለሁ፡፡ ስለሆነም፤ ዘንድሮ እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ በተከበረው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች 76ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት፤ ክቡር የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፤ በተለይም የሀገራችን ወጣቶች ይህንና ሌሎችም የኢትዮጵያውያን ህዝቦችን የነፃነት ተጋድሎ የሚያወሱ አኩሪ የጋራ ታኮቻችንን ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ የራሳቸውን ገንቢ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ያሳሰቡበትን ጠቃሚ ነጥብ ነው በቅድሚያ የማነሳው፡፡

በዚህ መሰረትም ክቡር ፕሬዚዳንቱ የኢፌዴሪ መንግስትን ወክለው ለበዓሉ ታዳሚዎች ካሰሙት ንግግር ላይ “ይህ ዛሬ በዚህ መልኩ የምናከብረው የጀግኖች አርበኞች ቀን እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎችን ተደጋጋሚ ወረራ በፅናት እየመከትን በመመለስ፤ ለሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራትና እንዲሁም ደግሞ ለመላው የዓለማችን ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆንንበትን አኩሪ ታሪክ የሚያስታውስ ነው” ካሉ በኋላ፤ ይልቁንም ወጣቱ የህብረተሰባችን ክፍል እንደ ባለተራ ትውልድ የጀግኖች አባቶቹንና እናቶቹን አደራ ተቀብሎ የማስቀጠል ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዲችል ለማድረግ መሰራት ስለሚኖርበት አንገብጋቢ የቤት ስራ ጉዳይ የገለፁበትን ነጥብ ስለወደድኩት እርሱን የሚያዳብር ተጨማሪ ሃሳብ ልሰነዝር ነው የፈለግኩት፡፡ ማለትም ክቡር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በዚያው ንግግራቸው “ይህ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የፀረ ቅኝ አገዛዝ ክንዳቸውን አስተባብረው በመነሳት በጋራ ጠላታቸው ላይ የተቀዳጁትን አንፀባራቂ የድል አድራጊነት ታሪካችንን በአግባቡ ጠብቀን ማቆየት የምንችለውም ደግሞ የአሁኑ ወጣት ትውልድ ሀገራችንን ከድህነትና ከሁዋላቀርነት የማላቀቅ አርበኝነቱን ይበልጥ አጠናክሮ ሲቀጥል እንደሆነ ይታመናል” ሲሉ ያሰመሩበት ቁልፍ ነጥብ፤ በእርግጥም መዳበር የሚገባው ገዥ ሃሳብ ሆኖ አግኝቸዋለሁ እኔ በግሌ፡፡

ይህን እንድል የሚገፋፋኝ ምክንያቱም ደግሞ፤ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በበዓሉ ላይ “የሀገራችንን ወጣቶች የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ጋር በሚጣጣም መልኩ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሲባል፤ አንድ አገር አቀፋዊ የወጣት ፌዴሬሽን እንዲመሰረት በመንግስት ታምኖበት ውሳኔውን ተግባራዊ የማድረግ ጥረት ተጀምሯል” የሚል መልካም ዜና አስደምጠቅናልና ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ የምንኖርበት የሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) መገለጫ ዓለም አቀፋዊ እውነታ ፈርጀ ብዙ ተፅእኖውን ከሚያሳድርበት የዘመን መንፈስ ጋር በተያያዘ መልኩ ወጣቶቻችን ላይ የተጋረጠባቸውን ፈርጀ ብዙ ችግር ለመቀልበስ የሚረዳንን መፍትሔ በማፈላለግ ረገድ፤ ራሳቸው የመሪ ተዋናይነቱን አዎንታዊ ሚና ለመጫወት እንዲነሳሱ የሚጋብዝ ሀገር አቀፍ አደረጃጀት የመፍጠር ጉዳይ ለነገ የማይባል ስለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

በግልፅ አነጋገር፤ የዛሬውን ኢትዮጵያዊ ወጣት ትውልድ አጠቃላይ ስብዕና በእጅጉ እየፈተነው ያለ አሳሳቢ ችግር፤ የወቅቱ ዓለም አቀፋዊ እውነታ ከሚገለፅበት የዘመነ “ፌስቡክ” መንፈስ የሚመነጭ ስነ ልቦናዊ ቀውስም ጭምር እንደሆነ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለምና መንግስት የጀመረው ጥረት አደጋውን ያገናዘበ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እናም ከዚህ አኳያ ሊደረግ የታሰበው የሀገራችንን ወጣቶች ትውልዳዊ ሚና ትርጉም ባለው መልኩ አደራጅቶ የማስቀጠል ጥረት ሳይውል ሳያድር ተግባር ላይ ውሎ መታየት ይኖርበታል የሚለው ነጥብ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ እኔ ጉዳዩን ደግፌ ተጨማሪ ሃሳብ ላክልበት፡፡

እንግዲህ የሰው ዘር በትውልዶች ተለጣጣቂ ቅጥልጥሎሽ የተቃኘ ህላዌ የዘመኑ መንፈስ በሚቀድለት የህይወት ቦይ ቁልቁል የሚጎርፍ ማህበራዊ ጅረት ተደርጎ ቢወሰድ ስህተት አይሆንም ይባልም የለ? እናም ከዚሁ ዓለም አቀፋዊ ስምምነት የተቸረው መሰረተ ሃሳብ ሳንለቅ ርዕሰ ጉዳዩን ወደራሳችን ሀገር ነባራዊ እውነታ እናምጣውና የአሁኑ ወጣት ትውልድ ከቀደሙት የኢትዮጵያ ትውልዶች የተለየ ሆኖ የሚታይባቸው የዘመን መንፈስ መገለጫ የወል ፀባዮች የትኞቹ ናቸው? በሚል ጥያቄ ዙሪያ ጥቂት ነጥቦችን ማንሳት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡

ይልቁንም ደግሞ፤ ዛሬ ላይ የምንኖርባትን ፌዴራላዊት፤ ዴሞክራሲያዊት ሪፕብሊክ ኢትዮጵያን የመፍጠር ህልም ከማለም ህልሙ እውን ሆኖ ያየንበትን ምስረታዋ በማሳካት ረገድ ቁልፍ ሚና እንደተጫወተ ከሚታመንበት የ1960ዎቹ ትውልድ ጀምሮ ባለው የሀገራች ህብረተሰብ፤ መካከል አንዱ ከሌላኛው የትውልድ ዘመን የተለየ ሆኖ የሚስተዋልበት ተጨባጭ ምክንያት እንዴት ሊገለፅ እንደሚችል ብናይ ብዙ ጠቃሚ ግንዛቤ የሚስጨብጥ ቁም ነገር እንደምናገኝበት ይሰማኛል፡፡ እንዴት ብትሉኝም፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከሌላው ዓለም የዘመናዊ ትምህርት ማዕድ የመቋደስን አስፈላጊነት መረዳት ከጀመረበት የታሪክ አጋጣሚ ጀምሮ፤ በሚታሰብና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣ የውጭ ሀገራት የፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ተፅእኖ ስር የወደቅንበትን የዘመን መንፈስ በመጋራት ረገድ ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጠው የ1960ዎቹ አብዮታዊ ትውልድ እንደሆነ የሚካድ ጉዳይ አይደለምና ነው፡፡

ከዚሁ ግንዛቤ የተነሳም፤ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው ወጣት የህብረተሰብ ክፍል፤ እንደ አንድ ትውልድ የሚገለፅባቸውን የወል ባህሪያት አንስተው ለመንቀፍ፤ ወይም ደግሞ ለማወደስ የሚሞክሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሲናገሩ በሚደመጡበት አጋጣሚ ሁሉ፤ በተለይም የ1960ዎቹ ዓመታት ውስጥ የተስተዋለውን የስር ነቀል ለውጥ ንቅናቄ አቀጣጥሎ የአፄውን ስርዓት ያንኮታኮተ አብዮት እንዲፈነዳ ስላደረገው ታጋይ ትውልድ ብርታትና ድክመትም አብሮ ሲነሳ መስማት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ለአብነት ያህልም፤ በሸገር 102.1 ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያ ላይ አዘውትረው እየቀረቡ ከወይዘሮ መዓዛ ብሩ ጋር በተለያዩ ማህበራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሲወያዩ የምናውቃቸው ዶክተር ምህረት ደበበ የተባሉ የስነ-ልቦናዊ ትምህርት ባለሙያ፤ ይህን የድህረ 1960ዎቹ ትውልዶች ተቃርኖ ስለገለፁበት ትንተና ማስታወስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ምክንያቱም ዶክተሩ ባሳለፍነው 2008 ዓ.ም ከሸገር ሬዲዮ ጋር ቆይታ ባደረጉበት ውይይት ላይ የሀገራችንን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አጠቃላይ ገፅታ የሚወስን አሉታዊ ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩ ቀለም ቀመስ ወጣቶች ሲበራከቱ የሚተዋሉበት አዝማሚያ ከምን እንደሚመነጭ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ጠይቃቸው ሲመልሱ የተደመጡበት አግባብ ያው እንደተለመደው የዛሬውን ኢትዮጵያዊ ትውልድ ከ1960ዎቹ የዘመን መንፈስ መገለጫ እውነታዎች አኳያ እየተመለከቱ ለማነፃፀር የሞከሩበት እንደነበር አስታውሳለሁና ነው፡፡ እናም እንደርሳቸው ማብራሪያ ከሆነ “የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ” በመባል ከሚታወቀው የታሪካችን ክፍል ጀምሮ አሁን ላይ በአፍላ የወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ እስከሚገኘው የዚች አገር ዜጋ ድረስ ሶስት ተከታታይ ትውልዶችን የሚወክል የዘመን መንፈስ የሚገለፅባት የወል ባህሪ መንፀባረቁን ነው መረዳት የቻልኩት፡፡

ይህ ማለትም ደግሞ፤ በተለይ ከ1950ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት አንስቶ እስከ 1960ዎቹ የመጨረሻ ዓመታት ውስጥ የተስተዋለውን ጉልህ የሚባል የስር ነቀል ለውጥ ፍለጋ ፖለቲካዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ፤ በመሪ ተዋናይነት ያስተባበሩት የግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለም አራማጅ ወጣት ምሁራን ዜጎቻችን የተከሰቱበትን የዘመን መንፈስ የሚወክለው አብዮተኛ ትውልድ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል ማለታቸው መሰለኝ ዶክተር ምህረት፡፡ ከዚያም፤ ይሄኛው አንጋፋ ትውልድ የመጨረሻውን የለውጥ ፍለጋ ግብግብ የገጠመበት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው የ“ነጭና ቀይ ሽብር” አሳዛኝ ክስተት በወታደራዊው የደርግ ስርዓት አሸናፊነት መደምደሙ ከተረጋገጠበት የ1970ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ አንስቶ እስከ የደርግ ውድቀት በነበረው የዘመን መንፈስ ውስጥ ተወልደው ያደጉት ኢትዮጵያውያን እንደ ሁለተኛው ትውልድ ሊወሰዱ ይችላ እንደ ማለትም ጭምር ይሆናል፡፡  

እንደኔ እምነት ግን፤ በተለምዶ “የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ” እየተባለ ከሚወሳው የጋራ ታሪካችን ክፍል ጀምሮ የደርግ ኢ.ሰ.ፓ ወታደራዊ አምባገነን የአገዛዝ ስርዓት የገነባው የአፈና መዋቅር፤ በኢህአዴግ መራሹ እጅግ የተራዘመ የትጥቅ ትግል እንዲኮታኮት እስከተደረገበት 1983 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በዘለቀው ዕርስ በርስ የመገዳደል አዙሪት ውስጥ የማለፍ ዕጣ የገጠማቸውን ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚያካትተው የዘመን መንፈስ እንደ የአንድ አሳረኛ ትውልድ ጉዞ መታየት አለበት ባይ ነኝ፡፡ ይህን የምልበት ዋነኛ ምክንያትም በተጠቀሰው የጊዜ ክልል ውስጥ የወጣትነት ዕድሜ ላይ ከነበረው ኢትዮጵያዊ ዜጋ መካከል አብዛኛው በአንድ ወይም ደግሞ በሌላ መልኩ፤ ስርነቀል የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ከመሻት የሚመነጭ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የተሞከረበትን አግባብ ተቀላቅሎ የመከራውን ገፈት ቀምሷል የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ እንደጥሩ ምሳሌ ሊቀርብ የሚችለው ጉዳይም ደግሞ የደርግ ኢ.ሰ.ፓ ወታደራዊ ፈላጭ ቆራጭ ስርዓት ስልጣን ጨብጦ በቆየባቸው የመከራ ዓመታት ውስጥ የተካሔደው የዕርስ በርስ ጦርነት ላይ አባትና ልጅ፤ ወይም ታላቅና ታናሽ ወንድማማቾች ጎራ ለይተው ሲገዳደሉ የተስተዋሉበት መራር እውነታ እንደነበር ማስታወስ ይመስለኛል፡፡

በተለይም፤ የደርግ ኢ.ሰ.ፓ አምባገነናዊ አገዛዝ የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ሲል ያካሂደው በነበረው የብሔራዊ ውትድርና ምልመላ ምክንያት፤ ወንድ ልጅ መውለድ እንደ እርግማን የተቆጠረበት የታሪክ አጋጣሚ የተስተዋለበትና ወጣቶች በአስገዳጅ ሃይል እየታደኑ ወደማያምኑበት የዕርስ በርስ ጦርነት እሳት እንዲማገዱ ይደረጉበት ስለነበረው አሰቃቂ ትዕይንት ማስታወስ የዚያን አሳረኛ ትውልድ፤ ከተራዘመ የሞት መንፈስ ያጠላበት ጨለማ ዘመን ጋር ተጋፍጦ ማለፍ ያመለክታል፡፡ እናም ከዚያ ሁሉ መላውን የዚች አገር ህዝቦች ፈርጀ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ፤ ዕርስ በርስ የመተላለቅ አዙሪት የመውጣታችንን መልካም ዜና ከሰማንበት የ1983ቱ የግንቦት 20 ድል መበሰር በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነው አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት፤ ይልቁንም ለወጣት ዜጎች ምንኛ እፎይታን የፈጠረ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ እንደነበር ነው እኔ በግሌ ምስክርነት የምሰጠው፡፡  

ለአብነት ያህል ማስታወስ የሚገባኝ ሆኖ የሚሰማኝም ደግሞ፤ የደርግ ውድቀት እውን መሆኑን ተከትሎ በነበሩት ዓመታት ውስጥ በተለይም የሀገራችን ኪነጥበብ ላይ ጉልህ የሚባል የመነቃቃት መንፈስ የተስተዋለበት እንቅስቃሴ ተፈጥሮ ማየታችንን ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም፤ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል የሚገኙ የከተማ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እንደ የዝንባሌያቸው እየተሰባሰቡ የሚያቋቁሟቸው የኪነጥበባዊ ሙያ ማህበራትና እንዲሁም ደግሞ ክለባት የተበራከቱበት ተጨባጭ እውነታ መስተዋሉን ማስታወስ ይቻላል፡፡ ያኔ ተግባራዊ መሆን የጀመረውን ሕገ-መንግስታዊ የመደራጀት መብትና ነፃነት ተጠቅመው፤ የቲያትር፤ እንዲሁም የስነ ፅሁፍና የስነ-ጥበብ ማህበራትን፤ አልያም ደግሞ ክለባትን እየመሰረቱ የየራሳቸውን ልዩ ተሰጥኦ ለማወቅ ያለመ ጥረት ሲያደርጉ ከተስተዋሉት የየአካባቢው ወጣት ዜጎቻችን መካከል ጥቂት የማይባሉ መክሊታቸውን ፈልገው እንዳገኙም ጭምር ነው እኔ የማስታውሰው፡፡

“በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ውሃ ይጠጣል?” እንዲሉ ሆኖ ግን፤ በተለይም ምርጫ 97ን ተከትሎ ከተስተዋለው የተቃውሞው ጎራ ፖለቲከኞችና የገዥው ፓርቲ አለመግባባት ጋር በተያያዘ መልኩ ትምክህተኞቹ ተቃዋሚ ሃይሎች እንደፈሊጥ የያዙት፤ የኢትዮጵያን ኪነ-ጥበባዊ የሙያ ዘርፍ ለፀረ-ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ የአመፅ ተግባር ማስፈፀሚያ የማድረግ ሙከራ ምክንያት፤ ከዚያ በፊት በነበሩት ዓመታት ውስጥ ይስተዋል የነበረው የወጣቱ አበረታች ጥረት መልኩን እየቀየረ የመጣበት የዘመን መንፈስ እንደሰፈነ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ በተለይም ደግሞ የኩርፊያ ፖለቲካውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በመሪ ተዋናይነት የሚያስተባብሩት ፅንፈኛ ተቃዋሚ ቡድች፤ ለራሳቸው በበለፀጉት የምዕራቡ ዓለም ሀገራት እየኖሩ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ያለመ የቀለም አብዮት የመቀስቀስ ሙከራ ሲያደርጉ የሚስተዋሉበት የማህበራዊ ሚዲያ ውዥንብር፤ ወጣቱን ትውልድ የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኛ አስተሳሰብ ሰለባ የመሆን ዕጣ እንዲገጥመው ማድረጉን ነው ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ፡፡

ስለዚህ እንደኔ እንደኔ፤ ወጣትነት ለማንኛውም ዓይነት ከየዘመኑ መንፈስ ለሚመነጭ ዓለም አቀፋዊ ተፅእኖ ግንባር ቀደም ተጋላጭ የሚያደርግ የዕድሜ ክልል ነው የሚለውን ቁልፍ ነጥብ አምኖ ለመቀበል፤ ከ1960ዎቹ ትውልድ የአፍቃሪ ኮሚኒዝም ፖለቲካዊ አመለካከት ጀምሮ ሲሆን ያየነው እውነት በቂ ማረጋገጥ ይመስለኛል፡፡ እናም የዛሬውን ኢትዮጲያዊ ወጣት የህብረተሰብ ክፍል ከዘመነ “ፌስቡክ” ውዥንብር የሚታደግ ሀገር አቀፍ መላ ለመምታት በሚያስችለን የመፍትሔ ሃሳብ ዙሪያ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ትኩረት ሰጥቶ መወያየት ይጠበቅብናል የሚለውን መሰረታዊ ጉዳይ ልናሰምርበት ይገባል እያልኩኝ እነሆ ሃተታዬን እንዲህ አጠቃልላለሁ፡፡ መዓሰላማት!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy