Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን እና ኢትዮጵያ

0 272

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን እና ኢትዮጵያ

ሰለሞን ሽፈራው

አብዛኛው የዓለማችን ማህበረሰብ የአሜሪካ ዴሞክራሲ አባቶች እንደሆኑ አድርጎ በየአጋጣሚው ከሚያወሳቸው የልዕለ-ኃያሏ ሀገር ቀደምት ፖለቲከኞች መካከል፤ ፕሬዚዳንት ቶማስ ጀፈርሰን አንዱ ናቸው፡፡ እናም የፕሬዚዳንት ጃፈርሰንን ዴሞክራት የፖለቲካ ስብዕና ታሪካዊ አውነታ በተወሳ ቁጥር አብሮ መነሳቱ የማይቀር ጉዳይ እንዳለ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ እርሱም ደግሞ፤ ከመጀመሪያዎቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ተርታ የሚመደቡት ቶማስ ጀፈርሰን፤ በዘመነ ስልጣናቸው “መንግስት ኖሮ ጋዜጣ ሳይኖር ከሚቀር ይልቅ፤ ጋዜጣ ኖሮ መንግስት ሳይኖር ቢቀር እመርጣለሁ” ብለው እንደነበር የሚጠቀስላቸው ሃሳብ ነው፡፡

በእርግጥም ደግሞ የህዝብ ወሳኝነት የሚገለፅበት መንግስታዊ የአስተዳር ዘይቤ ስለመሆኑ መላውን የዘመናችን ዓለም ማህበረሰብ እያስማማ የመጣውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባት አስፈላጊነት ሲታሰብ፤ አብረው መታሰብ ከሚኖርባቸው ቁልፍ ነጥቦች ውስጥ ፕሬስ ወይም ሚዲያ ቀዳሚ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡ ምክንያቱም፤ ዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ የመፍጠር ጥረት አልፋና ኦሜጋ ተደርጎ የሚቆጠረውን የሰዎች ሃሳብን እንደልብ የማንሸራሸር (የመግለፅ) ነፃነትን የሚያረጋግጥ ቅድመ ሁኔታ እንደማሟላት ይወሰዳልና ነው፡፡

በየትኛውም ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓተ-መንግስትን ለመገንባት የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ጥረት እየጎለበተ ሔዶ ትርጉም ያለው የአመለካት ለውጥ ወደማምጣትና በአስተሳሰብ የበለፀገ ህብረተሰብ ወደ መፍጠር ደረጃ ሊደርስ የሚችለው፤ ሁሉም ዜጋ የየራሱን ፖለቲካዊ አቋም የሚያንፀባርቅበት ነፃና ገለልተኛ የሃሳብ መግለጫ መንገድ ሲኖር እንደሆነ፤ በርካታ የዓለማችን ምሁራን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚናገሩለት ጉዳይ ነውና መድገም አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ ይልቅስ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ከማረጋገጥ፤ አለማረጋገጥ ጋር ተያይዞ በሚነሳው ዓለም አቀፋዊ እሰጥ-አገባ ዙሪያ አንዳንድ የኛን ሀገር የሚመለከቱ ነጥቦችን መርጠን ለማየት ብንሞክር ጠቃሚ ይሆናልና ነው እኔም ይህን ርዕሰ ጉዳይ አነሳው ዘንድ የወደድኩት፡፡

ስለሆነም፤ በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ “ለጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ነን” ባዮች አንዳንድ ተቋማት እንደሚያስተባብሩት የሚነገርለትና “ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን” በመባል የሚታወቀው ዓመታዊ በዓል የሚወሳበት አጋጣሚ በመጣ ቁጥር፤ የኢትዮጵያ ስም አብሮ ሲነሳ የሚደመጥበት አሉታዊ ቃና ያለው “ሪፖርት” ተብያቸው ዘንድሮም ያው እንደተለመደው ሁሉ የሀገራት “ጭራ” አድርጎ እንዳስቀመጠን የሚያመለክቱ ምንጮች መኖራቸውን ነው እኔ በግሌ ለመረዳት የቻልኩት፡፡ በዚህ መሰረትም የዘንድሮውን ዓለም አቀፋዊ የፕሬስ ነፃነት ቀን ምክንያት በማድረግ ይፋ የሖነ የነ ሲ.ፒ.ጄ እና የነሂውማን ራይትስዎች ዓመታዊ ሪፖርት፤ ኢትዮጵያን ከአንድ መቶ ሰማኒያ ሀገራት ውስጥ አንድ ሃምሳ አምስተኛ ላይ እንዳስቀመጣት ነው ሰሞኑን የወጡ መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

እንግዲያውስ የዛሬው መጣጥፌ ዋነኛ ትኩረት የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀንና ኢትዮጵያ በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የሚያጠነጥን መሰረተ ሃሳብን አንስቶ ማተት እንዲሆን የፈለግኩትም፤ በተለይ አንዳንድ የሀገራችን ነባራዊ እውነታ የሚገለፅባቸው ጥሬ ሀቆች ላይ ልብ ሊባል እየተገባው፤ ግን ደግሞ የተዘነጋ የሚመስል ቁልፍ ነጥብ ስላለ እርሱን አንስቼ ተጨባጩን በጎ ገፅታችንን ሽምጥጥ አርገው ለመካድ የሚቃጣቸው የውጭ ሃይሎች በዓመታዊ ሪፖርት ተብያቸው ምንኛ ፍርደ ገምድል ፍረጃን እንደሚያሳዩ ማመላከት እንደሚጠበቅብን ስለማምን ነው ማለት ይቻላል፡፡

ስለዚህ፤ አሁን በቀጥታ ወደ ዋናው ነጥብ አልፌ፤ እውን የዛሬዋ ፌዴራላዊት፤ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ የምትመራበት ሕገ መንግስታዊ ስርዓት የነሲ.ፒ.ጄ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ የሚቀመጠውን ያህል የፕሬስ ነፃነት ፀር ነውን? ደግሞስ መላው የዚች አገር ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተጎናፀፉትን ራስን በራስ የማስተዳደር ዴሞክራሲያዊ መብት ጨምሮ፤ ከዚሁ መሰረታዊ መብት የሚመነጩ እጅግ ፈርጀ ብዙ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት መገለጫ ሰብዓዊ መብቶችን ማረጋገጥ የተቻለበት አግባብ እንዳለ አያውቁ ይሆን ሪፖርት አቅራቢዎቹ ዓለም አቀፍ ተቋማት? ወዘተ ለሚሉ ጥያቄዎች እኔ የበኩሌን ምላሽ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡

እናም ከላይ በተነሱት ጥያቄዎች ዙሪያ እውቱን መነጋገር ካለብን፤ ምንም እንኳን በድህረ ደርግ ኢትዮጵያ  ውስጥ የተከፈተውን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከትሎ ሀገራችን ይፋ ያደረገችውን የፕሬስ ነፃነት አዋጅ በሚመጥን የኃላፊነት ስሜት የተቀረፀ የፕሬስ ሚዲያ እንዲኖረን ተደርጓል ለማለት የሚያስችል ውጤት ሳናመጣ መቆየታችን ባይካድም፤ እንደነ ሲ.ፒ.ጄ አምኒስቲ ኢንተርናሽናልና ሒውማን ራይት ሰዎች ዓይነቶቹ ኒዮሊበራል የውጭ ኃይሎች አዘውትረው በሚያሰሙት መሰረተ ቢስ ውንጀላ የሚሉትን ያህል የሚያስወቅስና የሚያስከስስ ተጨባጭ ሁኔታ የተስተዋለበት አጋጣሚ እንዳልነበረ ነው የሚታወቀው ጉዳይ፡፡ ይህን ስንልም ደግሞ፤ ከዛሬ 25 ዓመታት በፊት ጀምሮ ይፋ በሆነው ስርነቀል የስርዓት ሂደት ውስጥ ተወልዶ ማደግ የነበረበትን ለሀገራችን ህዝቦች አጠቃላይ እውነታ የሚመጥን ህብረ ብሔራዊ ወርድና ቁመት ያለው ጤናማ የፕሬስ ሚዲያ በመፍጠር ረገድ የተደረገው ጥረት እንብዛም እንዳልሰመረ ባያከራክርም ቅሉ፤ ያለ መሆኑ ዋነኛው ምክንያት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት፤ ሃሳብን በነፃነት ለመግለፅ መብት ተገቢ ክብር ለመስጠት ስላልፈለገ ነው ብሎ መደምደም ግን ትክክለኛ ፍርድ ሊሆን አይችልም ማለታችን ነው፡፡

ምክንያቱም፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዜጎች የመሰላቸውን ሃሳብ ያለ አንዳች ገደብ የሚገልፁበት የመረጃ ፍሰት ሳይኖር ትርጉም ያለው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ሊኖር እንደማይችል አበክራ ከመገንዘቧ የተነሳ፤ በቀደሙት መንግስታት ዘመን ይሰራበት የነበረው ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) መቅረቱን ያረጋገጠችበትን የፕሬስ ነፃነት አዋጅ ይፋ ያደረገችው ገና በሽግግሩ ወቅት እንደነበር ይታወሳልና ነው፡፡

ይሁን እንጂ፤ በዚች አገር ውስጥ ያኔ እውን መሆን የጀመረውን ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ጉዞ በፀረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ፈርጀው የተነሱት የወደቀው ወታደራዊ አገዛዝ ፕሮፖጋንዲስቶች፤ ወደ ስልጣን የመጣውን አዲስ ዓይነት ፖለቲካዊ ሃይል ለመበቀል ያለመ በሚመስል፤ ጭፍን ድፍን ያለ የጥላቻ ስሜታቸው ማጥላላት የያዙበት ሰፊ ዘመቻ እንደነበር ሲታወስ ነገሩን ገና ከመነሻው ያበላሸው ማን እንደሆነ መገመት ይቻላል ባይ ነኝ፡፡ ስለዚህ ተወቃሽም ተከሳሽም በስልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ ብቻ ተደርጎ የሚወሰድበት አግባብ ፍርደ ገምድልነት ነው የሚለው ነጥብ መጤን አለበት እላለሁ፡፡ ምክንያቱም ደግሞ በ1983 ዓ.ም ለመላው የሀገራችን ህዝቦች የተበሰረውን የግንቦት 20 ድል ዜና ተከትሎ፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የተደረገው የፕሬስ ነፃነት አዋጅ፤ ይጠበቅበት የነበረውን ያህል አውንታዊ ተፅእኖ የመፍጠር ሚና ሳይጫወት ለመቅረቱ ዋነኛውን አሉታዊ ድርሻ መውሰድ የሚኖርባቸው ፅንፈኞቹ የተቃውሞው ጎራ ፖለቲከኞች ናቸው የሚል አቋም አለኝና ነው፡፡

ይህን ስል ግን፤ ገዥው ፓርቲና በእርሱ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት፤ የፕሬስ ነፃነት አዋጁ የሚጠበቀውን ያህል በጎ ተፅእኖ እንዲያሳድር በማድረግ ረገድ መጫወት የሚገባቸውን ታሪካዊ ሚና እየተጫወቱ ናቸው ማለቴ አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ኢህአዴግ መራሹን ፌዴራላዊ መንግስትም የሚያስተቸው ድክመት ስለመኖሩ በየወቅቱ ሲነገር የሚደመጥ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የመንግስት ደካማ ጎን በጊዜ ሊታረም ቢችል ችግሮችን መቀነስ አያዳግትም ነበር የሚሉ ወገኖች የሚያሰሙት፤ (በተለይም የፕሬስ ሚዲያውን ኢኮኖሚያዊ አቅም ከማጎልበት ጋር የሚያያዝ ቅሬታ) እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ዘርፉን ከመሰረቱ ፈር ያሳተ ስህተት የፈፀሙት ግን ፅንፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች ናቸው ለማለት ነው እኔ የፈለግኩት፡፡

ስለዚህም፤ የፕሬስ ነፃነት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት መሟላት ካለባቸው ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ቁልፍ ነጥብ ነው በሚለው መሠረተ ሃሳብ ዙሪያ፤ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል ከተባለ፤ ታዲያ ስለምን ትምክህተኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ጉዳዩን ለእነርሱው ጠባብ ፍላጎት ማስፈፀሚያ ብቻ ሊያደርጉት ሲሞክሩ ይስተዋላሉ? ብሎ መጠየቅ ግድ ይላልና ነው እኔም ነገሩን አንስቼ የሚሰማኝን ለመተንፈስ የተገፋፋሁት፡፡ ምክንያቱም ደግሞ፤ እነ ሲ.ፒ.ጄ. ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን በመጣ ቁጥር ኢትዮጵያን ሃሳብን የመግለፅ ፀር ተደርገው ከሚፈረጁትና የለየላቸው አምባ ገነን መንግስታት ከሚመሯቸው ሀገራት አንዷ እንደሆነች አድርገው ለማስቀመጥ ሲሞክሩ የሚስተዋሉበትን “ዓመታዊ ሪፖርት” ተብዬ እያቀነባበሩ የሚያቀርቡላቸውም ጭምር፤ የችግሩ ፈጣሪዎች ተደርገው የሚወሰዱት ፅንፈኛ ተቃዋሚ ዜጎቻችን ናቸው ተብሎ ይታመናልና ነው፡፡

ስለሆነም፤ ይህን ከኛ አገሩ የግል ፕሬስ ሚዲያ ጋዜጠኞች ጋር በተያያዘ መልኩ ተጠቃሾቹ ዓለም አቀፍ የሲቪክ ተቋማት ደጋግመው ሲያነሱት የሚደመጠውን ውንጀላ በተመለከተ፤ ከማንኛውም የውጭ ሃይል ይልቅ፤ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖርን፤ ከትናንት እስከ ዛሬ እየታተሙ በወጡ ጋዜጦችና መፅሔቶች ላይ ተፅፎ ስላነበብነው አስገራሚም፤ አሳሳቢም ድፍረት የሚንፀባረቅበት የተቃውሞ ፖለቲካ መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ መመስከር ብንችል፤ እውነታውን የሚያስረዳ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህም አንዳንድ የራሴን ትዝብት መሰረት ያደረጉ ነጥቦችን በማስታወስ ነው ሃተታዬን የማጠቃልለው፡፡ በዚህ መሰረትም፤ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ጀምሮ፤ የግሉ ፕሬስ ሚዲያ ላይ በጋዜጠኝነት ሙያ ሲሰሩ ከማውቃቸው ጥቂት የማይባሉ ዜጎቻችን መካከል አንዳቸውም ለአንዲት ቀን እንኳን ሳትብሏቸው፤ ስርነቀል የስርዓት ለውጥ ጉዞው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ህዝቦች ስላመጣው መልካም ነገር የሚያመለክት ዜና ለመፃፍ የሞከሩበት አጋጣሚ አለመኖሩን እንደታዘብኩ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡

ምክንያቱም ደግሞ፤ ለእነዚህ ወገኖች የፕሬስ ነፃነት ማለት፤ በህዝብ ተመርጦ የመንግስትነት ስልጣን የጨበጠውን ገዥ የፖለቲካ ፓርቲ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ከወረራት የፋሽስት ጣሊያን ቅኝ ገዥ ሰራዊት ጋር እያመሳሰሉ ከማቅረብ ጀምሮ፤ ሌላ ማንኛውንም አይነት የውግዘት ፕሮፖጋንዳ ተጠቅመው በፀረ የሀገር አንድትነት ለመፈረጅ መሞከርና ከዚያም ህዝቡን አስቆጥቶ እነርሱ ለሚናፍቁት የቀለም አብዮት ተግባር እንዲነሳ ማድረጊያ መንገድ እንጂ፤ ሌላ ፋይዳ እንዲኖረው አይጠበቅምና ነው፡፡ ከዚህ የተንሸዋረረ ግንዛቤያቸው በሚመነጭ የነውጠኝነት አባዜ ምክንያት፤ የግሉን ፕሬስ ሚዲያ ከእግር እስከ ራሱ ተቆጣጥረው እነርሱ “ወያኔ ኢህአዴግን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ አሽቀንጥሮ ለመጣል የሚካሔድ ሰላማዊ ትግል” እንደሆነ አድርገው ለሚቆጥሩት የአመፅ ተግባር መቀስቀሻነት ሊያውሉት ሲሞክሩ ያልታዘብንበት አጋጣሚ የለም ብልም አጋነንህ አያሰኘኝም፡፡

ታዲያ እኛ የዚች አገር ተራ ተርታ ዜጎች ፤ ላለፉት 25 ዓመታት እዚሁ ዓይናችን ስር ተደጋግሞ ሲፈፀም እያየን የቆየነው፤ የኢትዮጵያ “ነፃ” ፕሬስ ሚዲያ አብዛኛው ጋዜጠኛ ከሙያው ስነ-ምግባር በእጅጉ ያፈነገጠ ድርጊት ይህን መሰል አስተዛዛቢ ገፅታ የተላበሰ እንዳልነበር ሁሉ፤ የነሲ.ፒ.ጄ. እና መሰሎቹ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ የተገለፀው ዝርዝር ጉዳይ ለምን የመንግስትን “ሃጢያት” ለማብዛት የተሞከረበት ብቻ እንዲሆን ተፈለገ!? የኋላ ኋላ የለየለትን ፀረ-ሕገ መንግስት የጎዳና ላይ ነውጥ በፊታውራሪነት አቀነባብረው ስርዓቱን ለመደርመስ ያለመተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ስለተደረሰባቸውና ምኞታቸው እንዳልሰመረ ስለተረዱም ጭምር፤ ሸሽተው ከአገር የወጡት የግሉ ፕሬስ አመፅ ናፋቂ ጋዜጠኞች አይደሉ እንዴ ዛሬ በነኢሳትና ኦ.ኤም.ኤን. አማካኝነት ኢትዮጵያን ለማተራመስ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩት?

ስለዚህ እውነቱን መነጋገር ካለብን፤ ሃሳብን ለመግለፅ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር ቆመናል በሚል ሽፋን የሚያምታቱት የሲቪክ ተቋማት ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀንን ምክንያት በማድረግ ያወጡት መግለጫ ላይ ኢትዮጵያን ከመጨረሻዎቹ ሀገራት ተርታ ያስቀመጡበት ፍረጃ፤ ፌዴራላዊ ስርዓታችንን ከቀለም አብዮት ናፋቂዎቹ ፅንፈኛ የፖለቲካ ቡድኖች የቅልበሳ አደጋ መታደግ መቻላችን እንዳስቆጣቸው ያመለክት እንደሁ እንጂ፤ ቅንጣት ያህል ለዚች አገር ህዝቦች ደህንነት የመቆርቆር ፍትሐዊ ገፅታ አይስተዋልበትም ብሎ ማጠቃለል ይቻላል፡፡ ለማንኛውም ግን በጉዳዩ ዙሪያ እኔ ያለኝ አቋም ይህን ይመስላል፡፡ በተረፈ  እውን የነሲ.ፒ.ጄ. ሪፖርት ነባራዊ እውታውን የሚገልፅ ይዘት አለውን? የሚለውን ጥያቄ ለአንባቢያን የህሊና ፍርድ እተወዋለሁ፡፡ መዓሰላማት!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy