Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዓለም ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ቀጥሏል!

0 546

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዓለም ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ቀጥሏል!

ሰለሞን ሽፈራው

ሀገራችን ኢትዮጵያ በታላላቆቹ ቅዱሳን መፅሐፍት የተነሳችበት አግባብ ስለመኖሩ በየአጋጣሚው የሚወሳ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለአብነት ያህልም በመፅሐፍ ቅዱስ ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› የሚል የብሉይ ኪዳን ጥቅስ እንዳለ ይታወቃል፡፡  ታላቁ የአላህ መልእክተኛ ነብዩ መሐመድ ‹‹ሐበሾችን ካልነቿችሁ በስተቀር እንዳትነኳቸው›› ሲሉ ለመላው የዓለም ሙስሊሞች ያሳሰቡበትን የአደራ ቃል ጨምሮ ሌላም ሌላም ኢትጵያና ኢትዮጵያዊነት በበጎ የሚነሱበት አግባብ መኖሩን ነው የእምነቱ ተከታይ ሊቃውንቶች የሚያስረዱት፡፡

ይሁን እንጂ በተለይም ዘመነ መሳፍንት እየተባለ ከሚጠቀሰው የሀገራችን ታሪክ ጀምሮ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እተባባሰ እንደመጣ በሚነገርለት ድህነትና ሁዋላ ቀርነት ምክንያት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በዓለም አቀፍ ማህበሰብ ዘንድ የሚታወቁበት አሉታዊ ገፅታ ብቻ ጎላ ብሎ ሲንፀባረቅ መቆየቱ የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡ እንደ አንድ ሀገር ህብረተሰበ የድህነት አመጣሽ ረሀብ መገለጫ ተምሳሌት ተደርገን በፈረንጆቹ መዝገበ ቃላት ወይም ደግሞ ዲሽክነሪ ላይ እስከመስፈር የደረስንበት ውድቀት አጋጥሞን እንደነብም ነው ተደጋግሞ ሲወሣ ከሚደመጠው የምሁራን አስተያየት መገንዘብ የሚቻለው፡፡

ደግነቱ ግን ከ1983 ዓ/ም በሁዋላ ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ የተከፈተውን አዲስ የታሪክ ምእራፍ ተከትሎ የተመሰረተው ፌደራላዊ የመንግስት ስርዓት በፈጠረልን ምቹ ሁኔታ ምክንያት ድህነት አመጣሹን ፈርጀ ብዙ አሳፋሪ ገፅታችንን የመቀየር ጥረት  መጀመራችንና ይሄው የፀረ ድህነት ጥረታችን የሚገለፅበት ሀገር አቀፋዊ የፈጣን ልማት ርብርብም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ እንደመጣ ይታመናል፡፡ እናም ሀገራችንን በአንድ ጠማማ የታሪክ አጋጣሚ የገጠማት ውድቀት እየተባባሰ በመምጣት የጨለማ ዘመን ሰሚ ከተመፅዋችነት ጋር ብቻ ተያይዞ ይነሳ ለነበረው ኢትዮጵያ፤ ለረጅም ጊዜ ጀርባውን ሰጥቷት የቆየው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፊቱን ወደ አዲስ አበባ ማዞር ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አሁን አሁን ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ያለመ ዲፕሎማሲያዊ ጥያቄ የሚያቀርብ የሀገር መሪ የለም በሚያሰኝ መልኩ ዓለም ወደ መዲኖችን አዲስ አበባ እየመጣ ያለበት እውነታ ስለመኖሩ ነው ደፍሮ መናገር የሚቻለው፡፡

ስለዚህም፤ ከ2007ዓ/ም ወዲህ ባሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ እንኳን ከኢትዮጵያው ፌደራላዊ መንግስት ጋር የተሻለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኑነት እንዲኖራቸው ፈልገው ወደ አዲስ አበባ የመጡ የበርካታ ባለፀጋ ሀገራት መሪዎች ቁጥር ሲታይ፤ በእርግጥም ዓለም ወደ ኢትዮጵያ ፊቱን እንዳዞረ የሚያመለክት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለአብነት ያህልም ይህን አሁን በመገባደድ ላይ የሚገኘውን የ2009 ዓ/ም ብቻ ወስደን ብንመለከት እንኳን፤ ገና የበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ግድም የኢትዮጵያውያን ህዝቦች ተረኛ እንግዳችን ከነበሩት የጀርመኗ መራሔ መንግስት አንጌላ መርክል ጉብኝት ጀምሮ፤ ሌሎች በርካታ የሀገራት መሪዎች ወደ አዲስ አበባ ያልመጡበት አንድም ወር የለም የሚያሰኝ ጥሬ ሀቅ ነው የሚስተዋለው፡፡

ከዚሁ የተነሳም፤ በተለይ ድንበር ከሚዋሰኑን የምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያው ፌደራላዊ፤ዴሞክራሲያዊ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ፈልጎ አዲስ አበባን ያልጎበኘ መሪ ወይም ፕሬዜዳንት የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ ብቻ ስለመሆናቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በምንጭነት ጠቅሰው የዘገቡ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ያመለክታሉ፡፡ ለዚህ የ 2009ዓ.ም ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶቻችንን ለሚመለከት አስተያየቴ እንደዋነኛ የመረጃ ምንጭ አድርጌ የምወስደው ደግሞ፤በተለይም ፋናብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬትን እንደሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡

ዘንድሮ በፈጣን የምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትና ብልፅግና ጉዞ ላይ ካለችው ኢትዮጵያ ጋር የተሻለ የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚፈጥሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ባለመ ይፋዊ ጉብኝት ወደ አዲስ አበባ ከመጡት በርካታ የሀገራት መሪዎች መካከል፤የወቅቱን ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ትኩረት የሳበ ፓለቲካዊ ተፅእኖ የፈጠሩ ሴት መሪዎች ተደርገው የሚቆጠሩት፤የጀርመኗ አንጌላ ወርክልና እንዲሁም ደግሞ የላይቤሪያዋ  ፕሬዜዳንት ሔለን ጆንሰን ሰርሊፍ የሚገኙበት ስለመሆኑም ይታወሳል፡፡የኳታሩ ንጉስ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስለ ሁለቱ ሀገራት  ዲፕሎማሲያዊ ዝምድና መደልደል ጉዳይ ከኢፌዴሪ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስቴር ከአቶ ሀ/ማርያም ደሳለኝና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር የመከሩበትን ይፋዊ ጉብኝት ጨምሮ፤አሁንም ድረስ እዚሁ መዲናችን ውስጥ በመካሄድ ላይ በሚገኝ አንድ ዓለም አቀፍ የምክክር መድረክ ለመሳተፍ የመጡ በርካታ የሀገራት መሪዎች ስለመኖራቸውም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡

ከሰሞኑ የአውሮፓዊቷ ሀገር የፓላንድ ፕሬዘዳንት አንዲዠይ ሰባስቲያን ዱዳ ኢትዮጵያን በይፋ ለመጎብኘት የመጡ ተረኛ እንግዳችን እንደነበሩም ማስታወስ  ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ ይህ አሁን በመገባደድ ላይ ያለው 2009ዓ.ም ከገባ ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የመጡት የሀገራት መሪዎችን ቁጥር እናስላው ብንል፤ከቀደሙት የበጀት ዓመታትም የላቀ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት የተቀዳጀንበት ሆኖ እናገኘዋለን 2009ን፡፡ በሌላ አነጋገር፤ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ማማለል የያዘውን የዛሬዋ ኢትዮጵያ በጎ ገፅታ ለማበላሸትና እንደ ቅድመ ግንቦት 1983ቱ አሳፋሪ እርስ በእርስ የመናቆር ታሪካችን የጦርነት ዓውድማ ተደርገን እንድንቆጠር የሚሹት የቀለም አብዮት ናፋቂ የፖለቲካ ሃይሎች የደገሱልን የጥፋት ድግስ ጎላ ብሎ የተስተዋለበት የመስከረም 2009ኙ ሙከራ “የውሻው መጮህ እንግዳውን አይመልሰውም” በሚያሰኝ መልኩ ስለመክሸፉ የሚያሳይ እውነታ ነው ያለው ማለት ይቻላል፡፡

ይህን የምልበት ዋነኛው ምክንያትም ደግሞ፤ ከመራሔ መንግስት (ቻንስለር) አንጌላ መርክል እስከ ሰሞነኛው የፓላንድ ፕሬዘዳንት በዘለቀው የበርካታ ሀገራት መሪዎች ወደ ኢትዮጵያችን ለይፋዊ ጉብኝት የመጡበትን ዲፕሎማሲያዊ ስሌት ግምት በማስገባት ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ይልቅስ ከዚሁ የባለፀጋዎቹን ምዕራባውያን ሀገራት ፕሬዘዳንቶችንም ጭምር ካካተተው የመሪዎች ተከታታይ ጉብኝት ጋር በተያያዘ መልኩ፤የዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ይበልጥ እየጎላ የመጣ ሌላም መሰረታዊ የበጎ ገፅታችን መገለጫ እንዳለን ይሰማኛልና ነው እኔ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ጥቂት ነጥቦችን ማንሳት እንደሚኖርብኝ ያመንኩት፡፡

ስለዚህም፤ክብራት እና ክቡራን  የፅሁፌ አንባቢያን በቅጡ ትገነዘቡልኝ ዘንድ የፈለግኩት ሌላው ተያያዥ ቁልፍ ነጥብ፤በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ መዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚካሄዱ ትልልቅ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎችና እንዲሁም ደግሞ የምክክር መድረኮች፤ከመቸውም ጊዜ በላይ እየተበራከቱ የመምጣታቸውን ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም፤አሁን እኔ ይህቺን ማስታወሻየን በምጫጭርበት ወቅትም ጭምር አንድ የአፍሪካ ሀገራትን የተትረፈረፈ የውሃ ሀብት ለኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫነት ስለማዋል አስፈላጊነት የሚመክር ዓለም አቀፋዊ የውይይት መድረክ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በመካሔድ ላይ ይገኛል፡፡ ለዚሁ የምክክር መድረክ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የመጡ በርካታ የዘርፉ ምሁራን ስለመኖራቸውም ነው የኢትዮጵያ ብሮደ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን በብሄራዊ ሬዲዮው ያስደመጠን ዜና የሚያመለክተው፡፡

ለነገሩ እንደዚህ ዓይነት ከአህጉር አቀፍነት አልፎ በዓለም አቀፋዊው ማህበረሰብ ደረጃ ትኩረት የሚስብ ርዕሰ ጉዳይ የሚነሳባቸው ምጣኔ ሀብታዊ የምክክር መድረኮችን ሀገራችን ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅና እንድታስተናግድ ማድረግ ከተጀመረ ሰነባብቷል ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ ከማስታውሳቸው መሰል መድረኮች መካከል እንደምሳሌ መወሳት ያለበት ሆኖ የሚስማማኝም ደግሞ፤ በተለይ 2007ዓ/ም ክረምት ውስጥ (ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የጎበኙን ሰሞን እንደነበር ልብ ይሏል?) አዲስ አበባችን ያስተናገደችውን እጅግ ግዙፍ አለም አቀፋዊ የፋይናንስ ጉባኤ ነው፡፡

ምክንያቱም፤ በዚያ መድረክ ለመሳተፍ ወደ መዲናችን ከመጡት ከአራት ሺህ በላይ እንግዶች መካከል አብዛኛዎች በዓለም አቀፍ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ የሚባል ሚና የሚጫወቱ ስመጥር ልሂቃን ስለመሆናቸው በወቅቱ ተደጋግሞ የተነገረ ጉዳይ  ነበረና ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ሌሎች መሰል ገፅታ ያላቸው አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ የምክክር መድረኮች መዲናችን ውስጥ ሲካሔዱ እንደቆዩም ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ታዲያ ይህ ጥሬ ሀቅ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን እንደቀጠለ አያመለክትምን ወገኖቼ? እንደኔ እንደኔ ግን በደንብ ያመለክታል ባይ ነኝ፡፡ ወደፊትም ይህ ሁኔታ ይበልጥ ተጠናክሮ የማይቀጥልበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ከወዲሁ ለመገመት ነብይነትን አይጠይቅም፡፡ ለማንኛውም ግን ሃሳቤን ለዛሬ እዚህ ላይ መቋጨቴ ነው፡፡         መዓ ሰላማት!     

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy