Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዛሬም አክራሪነትን ቸል አንበለው!

0 265

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዛሬም አክራሪነትን ቸል አንበለው!

ዳዊት ምትኩ

የአክራሪነት ተግባር ዘርን፣ ቀለምን፣ ፆታን፣ ዕድሜን፣ ሃይማኖትን…ወዘተረፈ ሳይለይ ሁሉንም ሰላማዊ የሰው ዘር ያለ ሐጢያቱ ይቀጥፋል። የተግባሩ መገለጫ ምንም ይሁን ምን፣ ድርጊቱ አንድ የገዘፈ ዕውነታን በውስጡ ይዟል። እርሱም ተግባሩ የራስን እምነትና ፍላጎት በሌላው ላይ በኃይል ለመጫን ንፁሃን ዜጎችን በዘግናኝ ሁኔታ ያለ አንዳች ርህራሄ እስከመግደል ድረስ የሚያደርስ መሆኑ ነው። የአክራሪነቱ መነሻ ያሻውን ቢሆንም፣ ተግባሩ ሁሉም ዜጎች በጋራ የሚቋደሷቸውን እንደ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ዓይነት ዓለም አቀፍ መብቶችን በጠራራ ፀሐይ የሚቀማ ነው።  

ታዲያ እዚህ ላይ ‘አክራሪነትን’ እና ‘አጥባቂነትን’ ለይተን መመልከት ያለብን ይመስለኛል። ለምን ከተባለ፤ ለማያውቃቸው ሰው ሁለቱም በአንድ እሳቤ ሊመሰሉ ስለሚችሉ ነው። እርግጥ አክራሪነትና አጥባቂነት አንድ ናቸው ብሎ መደምደም አይቻልም። ምክንያቱን በምሳሌ ብናስደግፈው፤ አንድ ግለሰብ “ሃይማኖቱን አጠበቀ” ያልን እንደሆነ ‘ሃይማኖቱን በጥብቅ አመነበት፣ ሌሎች ሰዎችንም ሃይማኖታዊ ህጉ በፈቀደው መሰረት እንዲከተሉ አደረገ’ የሚል ፍቺ ከመስጠቱም በላይ፤ አጥብቆ ያመነበት ሃይማኖት ተስፋ ካለው ሰማያዊ ህይወቱ ጋር መገናኘቱንም ያሳየናል፡፡

በአንፃሩ ደግሞ የሃይማኖት አክራሪነትን ፍቺ ከተፃፉት ፅሑፎች በላይ በዝሩው ስንመለከተው፤ ከአጥባቂነት ጋር ፍጹም ተቃራኒ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ “ነገርን በምሳሌ…” እንዲሉ አበው፤ አንድ ሰው “አክራሪ ሃይማኖተኛ ነው” ያልን እንደሆነ፣ ‘ሌሎች እምነቶች ሊኖሩ አይገባም’ ብሎ ያምናል እያልን ነው። ይህ ዕውነታም ‘ሁሉም ሰው የእኔን እምነት ብቻ መከተል ይኖርበታል’ የሚል ጤነኛ ያልሆነ አስተሳሰብን የያዘ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነቱ እሳቤ ግለሰቡ የፈጠረውን አፈንጋጭ እምነት ሌሎች ያልተከለተሉት እንደሆነ ሁከትንና ብጥብጥን ብሎም ግድያን የሙጥኝ በማለት ‘እኔን ብቻ ተከተሉኝ’ የሚል ፍላጎት ያለው መሆኑን ለመገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም።

ታዲያ ይህን ለዓለም ህዝብ የማይበጅ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ድርጊትን ከወዲሁ መቆጣጠር ካልተቻለ፤ የሚያስከትለው አደጋ ምን ያህል የከፋ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት የድርጊቱ ሰለባ ከሆኑ የዓለም ህዝቦች ብሎም ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ለመረዳት የሚከብድ አይመስለኝም።

እርግጥ ይህን አስከፊና ፈታኝ ተግባር የተገነዘበው የዓለም ህዝብ ድርጊቱን “ሳይቃጠል በቅጠል” በማለት ላይ ይገኛል። አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ አፍሪካ፣ ኤስያና ሌሎች ክፍለ-ዓለማት ፈታኙን የአክራሪነት ዕውነታ ተረድተው እየተረባረቡ ነው።

ሃቁን ወደ ሀገራችን ስንመልሰው ደግሞ፤ ተግባሩ ኢትዮጵያ በጀመረችው የፀረ-ድህነት ዘመቻ ላይ ሊሰነቀር የሚችል አሜኬላ እሾህ ሆኖ እናገኘዋለን። አሜኬላ እሾሁ ለመሰንቀር የሚከጅለው ሀገራችን የህልውና ጉዳይ አድርጋ በያዘችው ድህነት ላይ በመሆኑም የተግባሩን አስከፊነትና የግዝፈቱን ልኬት የሚያመላክት ይመስለኛል። ምክንያቱም የህልውና ጉዳይን የሚፈታተን ማንኛውም ክስተት ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት የዚያኑ ያህል የገዘፈ መሆኑ አስረጅ የሚያስፈልገው ጉዳይ ስላልሆነ ነው።

እርግጥ ተደጋግሞ እንደሚነገረው ለአክራሪነት አመለካከት ተጋላጭ ከሚያደርጉን ጉዳዮች ዋነኛዎቹ ጉዳዩች ድህነት እና ኋላቀርነት ናቸው፡፡ ይሁንና ላለፉት 26 ዓመታት የሀገራችን ህዝብ ከድህነት እና ከኋላቀርነት ለመላቀቅ ነባር የመከባበርና የመቻቻል እሴቶቹን ጠብቆ መንገዱን ይዟል።

እንደሚታወቀው የሀገራችን ህዝብ የሚያኮራ እና ለሌሎች ሀገሮችም ጭምር ምርጥ ተምሳሌት ሊሆን የሚችልባቸው አስደሳች እሴቶች አሉት፡፡ ከእነዚህ መካከል በውስጡ ያቀፋቸው የበርካታ ሃይማኖቶች በመከባበር እና በመቻቻል እንዲሁም ለረጅም ዘመናት አብሮ የዘለቀ ሠላም ወዳድ ህዝብ መሆኑ ነው፡፡

ሁኔታውን ከሌሎች ሀገራት አንፃር ስናየው፤ ሀገራቱ እንደ እኛ ብዙ ሃይማኖት ሳይኖራቸው በጣት የሚቆጠሩ እምነቶች እያላቸው መከባበር እና መቻቻል አቅቷቸው ለሁከት እና ለብጥብጥ ሲዳረጉ እናስተውላለን፡፡ ይህ አንፃራዊ ንፅፅር የብዙ እምነቶችና ሃይማኖቶች ባለቤት የሆነው የሀገራችን ህዝብ ምን ያህል ተከባብሮና ተቻችሎ እንደሚኖር ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል።

ለነገሩ አክራሪዎች የሚፈሉጉትን የፖለቲካ አጀንዳቸው ለማራመድ ዋነኛ አማራጫቸው ሃይማኖትን እንደ ሽፋን በመጠቀም ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ማሳካት ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ሃይማኖተኛ መሰል ፖለቲከኞች ለዚሁ እኩይ ተግባር የሚጠቀሙባቸውን ተላላኪ ግለሰቦች በጥቅም በመደለል አሊያም ራሳቸው ፊት ለፊት በመሰለፍ ‘የግድ የእኔን እምነት ብቻ ተከተል’ የሚል ፍላጎታቸውን ገቢራዊ ለማድረግ እስከ ግድያ የሚደርስ ዘግናኝ ተግባር መፈፀማቸው አይቀርም፡፡ በሶማሊያ የሚገኘውን የአል-ሸባብን እንዲሁም የምዕራብ አፍሪካውያኑን ቦኮ ሃራምንና አንሳር ዲንን ብሎም የሰሜን አፍሪካው እስላማዊ መግሪብን መነሻቸው አክራሪነት የሆኑ የሽብር ተግባሮች ለዚህ አባባሌ ሁነኛ አስረጂዎች ይመስሉኛል።

እርግጥ ትናንትን ከዛሬ ጋር እያስተያየን ወደ ፈታኙ እውነታ መዝለቁ ተገቢ ይመስለኛል። እጅግ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው፣ ነገር ግን ራሳቸውን እንደ ትክክለኛ አማኝ በመቁጠር በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ “በሃሰተኛ መልዕክተኝነት” የሚንቀሳቀሱት አክራሪ ወገኖች፤ ስለምን ሰላማዊ በሆነው ሃይማኖት ውስጥ ያለውን ቀኖናዊ መከባበርና መፈቃቀድ ለመበረዝ እንደሚሯሯጡ ከማንም የሚሰወር ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ይኸውም የሃይማኖት ጉዳይ የሰዎችን ስሜት በቀላሉ የሚኮረኩር በመሆኑ፤ የክርስትናንም ይሁን የእስልምና ተከታይ ምዕመናንን በቀላሉ ወደ ማይፈለግ የጥላቻና የአመፅ አቅጣጫ በቀላሉ በመምራት የፖለቲካዊ ስልጣን ግብን ማሳካት ይቻላል ብለው ስለሚያስቡ ነው።

ዳሩ ግን የኢትዮጵያ ህዝቦች ከብዙዎቹ የዓለማችን ህዝቦች የክርስትናንም ይሁን የእስልምና እምነቶችን አስቀድመው የተቀበሉ ብቻ ሳይሆኑ፤ የተለያዩ ሁለገባዊ አስተሳሰቦችን ፈጥረው የመቻቻልና የመከባበር ባህልን ያዳበሩ በመሆናቸው ፍላጎታቸው ረጅም ርቀት ይጓዛል ብሎ ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም፡፡

እርግጥ ባለፉት ሥርዓቶች በየጊዜው የተነሱት ነገስታትና ሱልጣኖች አንዳቸው በሌላኛው ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት አልፎ አልፎ በሃይማኖት ጦርነት መልክ ፖለቲካዊ ፍልሚያዎች አካሂደዋል። በርካታ ዜጎችም በሃይማኖታቸው ምክንያት እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረዋል። ይህ ዘመን የማይሽረው ሃቅ የትናንት ታሪካችን፣ የዛሬና የነገ ደግሞ የማንነታችን መገለጫ ነው፡፡

ያም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ህዝቦች የሃይማኖት እኩልነትና የእምነት ነጻነት ፈጽመው በማይታወቁባቸው በእነዚያ ዘመናት ተከባብረው በአንድነት ዘልቀው ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡ ላለፉት 26 ዓመታት ደግሞ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ህገ- መንግስቱ በሰጣቸው ዋስትና መሰረት የአንደኛው ሃይማኖት ከሌላኛው ሳይበላለጥ እንዲሁም ያሻቸውን ዓይነት እምነት በማምለክ ላይ ይገኛሉ፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ባለፉት ሥርዓቶች ሃይማኖታዊ ነጻነታቸውን የተገፈፉት የኢትዮጵያ ህዝቦች ተከባብረው ከኖሩ፤ ዛሬ ላይ በእኩልነትና በነጻነት እምነታቸውን እያመለኩ የቀድሞ መቻቻላቸውንና መከባበራቸውን የሚተውበት አንዳችም ምክንያት ሊኖር የሚችል አይመስለኝም፡፡ እናም ይህ ነባራዊ ዕውነታቸው በአክራሪነት ጎራ ተሰልፈው ክርስቲያኑንና ሙስሊሙን ማህብረሰብ ለመበጥበጥ ቀን ከለሊት ለሚቧችሩ ወገኖች ቦታ የሚሰጥ አይመስለኝም፡፡

እርግጥ የቁጥራቸው ብዛትና የዓይነታቸው ሁኔታ ይለያይ እንጂ፣ በየትኛውም ሀገር ውስጥ በአክራሪነት ጎራ የተሰለፉ ወገኖች መኖራቸው አይቀርም። በእኛ ሀገር ውስጥ ቢኖሩም ሊደንቀን አይገባም። ሆኖም አክራሪዎቹ ያሉንን የድህነትና የኋላ ቀርነት ተጋላጭነታችንን ተጠቅመው የተጀመረውን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ብሩህ ጎዳና ለማጨንገፍ አደናቃፊ ድንጋይ ሆነው ከተደረደሩ የችግሩ መነሻ መሆናቸው አይቀሬ ነው።

እናም በእኔ እምነት እነዚህን ወገኖች ትርጉም ወደማይሰጡበት ደረጃ ማድረስ የሚቻለው የተጀመሩት ሁለንተናዊ ሀገርን የማሳደግና ህዝብን ከተመፅዋችነት የማውጣት ጥረት ለሚቀጥሉት ጊዜያትም ተጠናክረው ሲቀጥሉ ብቻ ነው። ሰላሙ አስተማማኝ የሆነ፣ በልማት በልፅጎ ሌሎች ከደረሱበት የዕድገት ማማ ላይ መውጣት የቻለ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን በአግባቡ በመጠቀም የሌሎችን መብቶች ማክበር የቻለ ህዝብ ለአክራሪነት ዝንባሌ ሊጋለጥ አይችልም። በመሆኑም ሁለም በየእምነቱ አክራሪነትን ሊዋጋው ይገባል።    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy