NEWS

የሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ቁጥር 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ደርሷል

By Admin

May 25, 2017

) በኢትዮጵያ የአውሮፕላን ማረፊዎች መስፋፋት የአየር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል።

ኢትዮጵያ ከሩብ ምዕተ አመት በፊት የነበራት የሀገር ውስጥ አውሮፕላን ማረፊያዎች ቁጥር አራት ብቻ ነበር።

በወቅቱ የነበሩት አውሮፕላን ማረፊያዎችም የጦር ስንቅ እና ትጥቅ ለማጓጓዝ ይውሉ ስለነበር አገልግሎታቸው በአብዛኛው ወታደራዊ ነው ማለት ይቻላል።

በ1995 ዓ.ም በአመት 569 ሺህ መንገደኞች የአየር ትራንስፖርትን ይጠቀሙ የነበረ ሲሆን፥ በ2008 ይህ አሃዝ ከአራት እጥፍ በላይ አድጎ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የአየር ትራንስፖርት ተጠቃሚ ሆነዋል።

ለመንገደኞች ቁጥር መመንደግ መሰረታዊ ምክንያቱ የሀገር ወስጥ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች መስፋፋት መሆኑ ነው የሚነገረው።

በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ጂማ፣ ጎዴ፣ ጋምቤላ ብቻ ተሰውኖ የነበረው የሀገር ውስጥ በረራ ዛሬ 23 ከተሞችን አዳርሷል።

በአሁኑ ወቅት በሳምንት ከሁለት እና ሶስት ጊዜ ያላነሰ በረራ ወደነዚህ ከተሞች ይካሄዳል።

የመሰረተ ልማቱ መስፋፋት ዜጎች በአቅራቢያቸው የአየር ትራንስፖርት እንዲያገኙ ከተሞቹም ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እንዲጠናከር አግዟል።

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ደርጅት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ወንድም ተክሉ በአብዛኛዎቹ የክልል ከተሞች አውሮፕላን ማረፊያዎች በሳምንት ከሁለት እና ሶስት ጊዜ ያልበለጠ በረራ ይስተናገድ እንደነበር አስታውሰው፥ በአሁኑ ወቅት በየእለቱ በረራ የሚያስተናግዱ አውሮፕላን ማረፊያዎች ተፈጥረዋል ብለዋል።

የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ እድገት መንገደኞችን በማጓጓዝ ላይ ብቻ የተሰወነ አይደለም፤ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ተከተሎ የመጣውን የወጪ ንግድ ለማስተናገድም የተሰናዳ ነው።

ሀገሪቱ አሁን የአራት አለም አቀፍ እና የ19 ሀገር አቀፍ በድምሩ የ23 አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ባለቤት ናት።

ከአምስት አመት በኋላ ሰባት ተጨማሪ አውሮፕላን ማረፊያዎች እንደሚኖራትም ይጠበቃል።