Artcles

የመልካም አስተዳደሩ ጉዳይ እንዳይዘነጋ!

By Admin

May 16, 2017

የመልካም አስተዳደሩ ጉዳይ እንዳይዘነጋ!

ዳዊት ምትኩ

መንግስትና ገዥው ፓርቲ በተለያዩ ወቅቶች በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት የህዝቡ ምሬትና ብሶት የሆነውን መልካም አስተዳደርን እንዲሁም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትንና ተግባርን ከህዝቡ ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እንደሚታገል በይፋ ገልጿል። እናም ቃሉን ከተግባር ጋር በማዋሃድ፣ በቅድሚያ ህዝቡን የሚያማርሩና ከህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ህይወት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያላቸው መንግስታዊ ዘርፎችን መርጦ ርብርብ እያደረገ ነው። በጥልቅ ተሃድሶው ቀዳሚ ጉዞ ወቅት በዚህ ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝ ተችሏል።

ይህም መንግስት ህዝቡ የሚያቀርባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ለህዝቡ የገባውን ቃል ሳይውል ሳያድር ዕውን ለማድረግ ያለውን ፍላጎት ያረጋገጠም ጭምር ነው ማለት ይቻላል። እርግጥ የሀገራችን ህዝብ ከመንግስት ጋር ባደረገው ውይይትና ብዙ ጠንካራ ጉዳዩችን ተምሯል።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን፣ መነሻዎችንና የአካሄድ ሰንሰለቶቻቸውን አውቋል። ህዝቡ የችግሩ ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ በመሆኑ ችግሩን በመቅረፍ ረገድ ምን ማድረግ እንዳለበት በውል ተገንዝቧል የሚል እምነት አለኝ። በተለይም በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረጉ ቀጣይ ትግሎችና የማስተካከያ እርምጃዎች ላይ የመንግስትንና የራሱን ሚና የለየበት ነው ማለት ይቻላል።

የዚህ ፅሑፍ ዓላማም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በውስን መልኩ በመቃኘት ከመንግስትና ከህዝቡ ምን እንደሚጠበቅ በማመላከት ግንዛቤ ለማስጨበጥ መሞከር ነው። በመሆኑም ‘የመልካም አስተዳደሩ ጉዳይ እንዳይዘነጋ!’ የሚል ጭብጥን በመያዝ፤ ለሚስተዋሉ ችግሮች የመፍትሔ ሐሳቦችን ማመላከት ተገቢ ይመስለኛል። ይህም በቀጣይ የመልካም አስተዳደር ችግር በሚታዩባቸው የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አኳያ ሁሉም ባለድርሻ አካል በተጠያቂነት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት የሚያግዘው ይሆናል። እስቲ ለማንኛውም መልካም አስተዳደርን በተመለከተ ምናልባትም አብዛኛዎቹን ተዋንያን ሊያስማማ ይችላል ተብሎ ከሚታሰብ አንድ ዓለም አቀፋዊ ብያኔ ልነሳ። ብያኔው የዓለም ባንክ ነው። በብያኔው መሰረት “መልካም አስተዳደር ማለት ሊተነበይ የሚችልና በነጠረ ፖሊሲ አወጣጥ የተካነ እንዲሁም በሙያዊ ስነ-ምግባር የሚታገዝና በሚወስዳቸው እርምጃዎች ተጠያቂ ሊሆን የሚችል መንግስትና በመንግስታዊ ጉዳዮችም በንቃት የሚሳተፍ ህብረተሰብ ያለበት ሆኖ፤ ሁሉም አካላት በህግ የበላይነት አምነው የሚንቀሳቀሱበት ስርዓት ነው።

ይህ የባንኩ ትርጓሜ በማናቸውም አገልግሎት ሰጪ ውስጥ ያሉ መንግስታዊ ተቋማት የሚያከናውኑት የመልካም አስተዳደር ስርዓት ያለ ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ዕውን ይሆን ዘንድ፤ ሊተነበይ በሚችልና በነጠረ ፖሊሲ የሚመራ መንግስት፣ በሙያዊ ስነ ምግባሩ የታመነበትና ማናቸውንም መንግስታዊ ተግባራት በተጠያቂነት፣ በግልፅነትና በህግ የበላይነት ብቻ የሚፈፅም ፐብሊክ ሰርቫንት እንዲሁም በሁሉም መንግስታዊ ክንዋኔዎች ውስጥ መብትና ግዴታውን አውቆ የሚንቀሳቀስ ህዝብ ሊኖሩ ይገባል።

ከእኛ ሀገር የሃያ ዓመት ለጋ ዴሞክራሲ አኳያም ብያኔውና በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው ሃቅ ሊጣጣሙ የሚችሉ አይመስለኝም። ምክንያቱም ባለፉት ስርዓቶች ሀገራችን የተጓዘችበት ጎርባጣ መንገዶችና መንገዶቹን ተከትለው ሲንከባለሉ የመጡ ኋላ ቀር አስተሳሰቦች በህብረተሰቡ ውስጥ መኖራቸው እንዲሁም እሳቤዎቹን ለማስወገድ ብሎም የዴሞክራሲ ባህል ግንባታችን ዘለግ ያለ የጊዜ ዑደትን ስለሚጠይቅ ነው።

ሆኖም መንግስትና ኢህአዴግ ቀደም ሲል በጠቀስኩት የዓለም ባንክ ብያኔም ይሁን በሌላ ዘውግ መልካም አስተዳደርን ላለማስፈን እጅና እግራቸውን አጣጥፈው ተቀምጠዋል እያልኩ አይደለም። ላለፉት 26 ዓመታት መልካም አስተዳደር በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ውስጥ ስር እንዲሰድ ዘርፈ ብዙ ጥረት አድርገዋል። አጥጋቢ ውጤቶችም ማግኘት ተችሏል። አብነቶችን ማንሳት ይቻላል።

የሀገራችን ዴሞክራሲ ስር መስደድ ይችል ዘንድ በሁሉም ደረጃዎች የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲቋቋሙና እንዲጠናከሩ፣ የዳበረ የፍትህ ስርዓት እንዲገነባ፣ የህዝቡ ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲጎለብት፣ በየደረጃው ባሉ የመንግስት አካላት ውስጥ የግልፅነት፣ የተጠያቂነትና የህዝብ አገልጋይነት መርህ እንዲሰፍንና የተግባር መመሪያ እንዲሆን ብሎም በሁሉም መስኮች የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ…ወዘተርፈ ጉዳዩች ዙሪያ አቅም በፈቀደ መጠን የተከናወኑ ወሳኝ ጥረቶችንና የተገኙትን አመርቂ ውጤቶችን መካድ አይቻልም። እነዚህ ሃቆችም መንግስት ግብ ባለውና በነጠረ የፖሊሲ ጥርጊያ መንገድ ሲጓዝ እንደነበር የሚያመላክቱ ናቸው።

ይሁን እንጂ ምንም እንኳን በመንግስት በኩል ቀደም ባሉት ጊዜያት እነዚህ ተግባራት ገቢራዊ ቢሆኑም ሙሉ ለሙሉ ዕውን ሆነዋል ማለት አይቻልም። በሌላ አባባል የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ሀገራችን ውስጥ ያለ አንዳች እንከን እየተከናወነ ነው ማለት አይደለም። ቀደም ሲል እንደተገለፀው አንድም ባለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡት ስነ-ልቦናዊ ጫናዎች፣ ሁለትም ዴሞክራሲያችን ገና በጅምር ላይ ያለ በመሆኑ ከጉዳዩ ግንዛቤ አኳያ የዳበረና በተጠያቂነት ብሎም በግልፅነት ሊሰራ የሚችል የመንግስት አስፈፃሚ አካል አለመኖር የፈጠሩት ችግሮች የመልካም አስተዳደር እጦት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ይመስለኛል።

እናም የመልካም አስተዳደር ጉዳይ መንግስትንና ህዝብን በቀጥታ የሚያገናኝ በመሆኑ ሁለቱም አካላት በየፊናቸው የበኩላቸውን መፍትሔዎች በየጊዜው መውሰድ ይኖርባቸዋል። መልካም አስተዳደርን ዕውን ከማድረግ አኳያ በዋነኛነት ሊያጋጥም የሚችለው ችግር የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ነው። ለአብነት እንኳን የመሬት አሰተዳደር ጉዳይን ብንመለከት፤ የተጠያቂነት ስርዓት አለመጠናከር፤ የግል ጥቅምን በማስቀደም የሊዝ አዋጁ ከታለመለት ዓላማ ውጭ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ እንዲሁም በየደረጃው የሚገኝ አመራር የሚታይበት አድርባይነትና የቁርጠኝነት ማነስ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል።

በመንግስት አስፈፃሚው አካል ውስጥ ከብቃትና አቅም ጋር ተያይዞ በራስ መተማመን አለመኖር፤ ጉዳዮቸን ቶሎ ባለመወሰኑና ባለማሳታፉ ስለማይጠየቅ፤ የራስን ጥቅም ማስቀደም ሊታይ ይችላል። እናም መንግስት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከህዝቡ ጋር በመሆን እየወሰደ ያለውን ርምጃ ሊያጠናክር ይገባል።

እንደሚታወቀው ዛሬም የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ድርጊት የለም ማለት አይቻልም። ይህም በሰራተኛውም ሆነ በሌላው ዜጋ ሰርቶ መለወጥን ሳይሆን አላግባብ በአቋራጭ የሚከብሩበትን መንገድ ብቻ የመፈለግ አመለካከት እንዲጨምር ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ይህ አመለካከት ደግሞ ልማታዊ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን በመሸርሸር የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የበላይነት እንዲኖረው አድርጓል። የአስተሳሰቡ የበላይነት በነገሰበት ስርዓት ውስጥ የተወሰኑ ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ፍትሃዊነትና እኩል ተጠቃሚነት እንዳይኖር በማድረግ የተጀመረው ፈጣን ልማት አሜኬላ እሾህ መሆናቸው አይቀሬ ነው። ይህም ታክስ ከፋዩ ህብረተሰብ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣ ማድረጉ አይቀርም። በተጀመረው ሀገራዊ ልማት ላይ ምንም ዓይነት እሴት የማይጨምሩ ደላሎችና ኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶች ብሎም አንዳንድ ተሿሚዎች ባለስልጣኖች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በር በመክፈት ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖር ያደርጋል። ይህም በአጠቃላይ የፖለቲካል-ኢኮኖሚ ስርዓቱ ላይ አደጋ መደቀኑ አይቀርም። በመሆኑም መንግስትና ህዝቡ ራሳቸው የመሰረቱን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመጠበቅና የጀመሩት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት እንዲቀጣጠል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ዛሬም ደጋግሞ መቃኘት ያስፈልጋል። እናም ሁሌም የመልካም አስተዳደሩ ጉዳይ እንዳይዘነጋ በማለት ሁሉም የዜግነት ድርሻውን ሊወጣ ይገባል። አበቃሁ።