የመልካም አስተዳደር ችግሮች በህብረተሰቡ ባለቤትነት ይፈታሉ!/ዳዊት ምትኩ/
መልካም አስተዳደር የዴሞክራሲ መገለጫ ነው። በማናቸውም አገር ውስጥ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ዴሞክራሲን የማስፋት አንዱ መንገድ ነው። ተግባሩ የህብረተሰቡን ዕለታዊ ክዋኔ የሚመለከት በመሆኑ ከህዝቡ ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ ነው። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ለመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት መጣር የህዝቡን ሁለንተናዊ መብቶች ማረጋገጥም ተደርጎ ይወሰዳል።
ከእኛ ሀገር አኳያ መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ በይፋ የሚታወቁ ተሃድሶዎች ለሁለት ጊዜያት ተካሂደዋል። አንደኛው በ1993 ዓ.ም በድርጅቱ ውስጥ የነበረውን ክፍፍል ለመፍታት የተሄደበት መንገድ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በጥልቅ ተሃድሶነት በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው የሂደት ጉዞ ነው። መልካም አስተዳደርን በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን ማድረግ ስለማይቻል ነው-እነዚህ ሁለት ተሃድሶዎች የተካሄዱት። በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው ጥልቅ ተሃድሶ ዋነኛ ዓላማውም ሀገራችን ውስጥ በህዝቡ ተሳታፊነት የታዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ነው ማለት ይቻላል።
እርግጥም ኢትዮጵያ ውስጥ መልካም አስተዳደርን ማስፈን የህልውና ጉዳይ ተደርጎ ከተያዘ ቆይቷል። የኢፌዴሪ መንግስት ከህዝቡ ጋር በቅርበት በመስራት የነበሩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መለየት እንደቻለው ሁሉ፤ ነገም ይህን ቁልፍ ችግር ከህዝቡ ጋር በመሆን እንደሚፈታው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። መንግስትም ይህን እውን ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባሮችን አከናውኗል።
ሆኖም አሁንም ቢሆን የመልካም አስተዳድር ችግር አልተፈታም። በእርግጥ መልካም አስተዳደርን በአንድ ጀንበር ለማስፈፀም መሞከር ችግሩ እንዳይፈታ የመፈለግ ያህል የሚቆጠር ይመስለኛል። የአንድ ጊዜ ጫጫታ ለዘመናት ስር የሰደደን የመልካም አስተዳድር ችግርን ሊፈታ አይችልም። በመሆኑም ችግሩን በሂደትና በሰከነ መንገድ ተግባሩን ማከናወን ያስፈልጋል። በአንፃሩም ችግሩን ለመፍታት ጊዜ ስለሚወስድ ሰከን ማለት የገባል በሚል አስተሳሰብ እጅና እግርን አጣጥፎ መቀመጥ ተገቢ አይደለም። ይህም ቢሆን ችግሩ እንዳይፈታ ከመፈለግ ያህል የሚቆጠር ነው።
እርግጥ መንግስት ባለፉት 26 የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት ውስጥ መልካም አስተዳደር አስተዳደር የዴሞክራሲ አካልና መሠረት መሆኑን በመገንዘብ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታን በግብነት አስቀምጦ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል። በዚህም ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ሊያሰፍኑ የሚችሉ ተቋማትን ከመመስረት ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚዎችን አቅም በማጎልበት በርካታ ስራዎችን ፈፅሟል።
ይሀን እንጂ እነዚህ ተግባራት የህዝቡን እርካታና አመኔታ ሊያተርፉ ባለመቻላቸው መንግስት በየደረጃው በአስፈፃሚዎቹ ላይ የተለያዩ ርምጃዎችን ከመውሰድ አልቦዘነም። በጥናት ላይ ከተመሰረተና የችግሩ ምንጭ ምን እና የት መሆናቸውን ከማወቅ በተጨማሪ፣ በፌዴራልም ይሁን በክልል ደረጃ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ አስተማሪ ርምጃዎችን ወስዷል። ለመልካም አስተዳደር ተፈፃሚነት ማነቆዎች ናቸው የሚባሉትን ችግሮች ሊቀይሩ የሚችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት ረገድም ብዙ ርቀት መጓዝ ተችሏል። እናም ከትናንት ዛሬ የተሻለ ሁኔታን መፍጠር ተችሏል።
ይሁንና አሁንም ድረስ ቢሆን የህዝቡን እርካታ መፍጠር አልተቻለም። ለዚህ ደግሞ በመንግስት በኩል ሲገለፅ እንደነበረው፣ የመንግስትን ስልጣን ለግል ጥቅም የማዋል ፍላጎት ገዥውን ድርሻ እንደሚወስድ ነው። በዚህም ሳቢያ ተሿሚዎችና በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚዎች ህዝቡን ከማገልገል ይልቅ ራሳቸው በህዝቡ የመገልገል ስሜትን አዳብረው በመልካም አስተዳደር አፈፃፀም ጉዞ ላይ ችግር ሲፈጥሩ ተስተውሏል።
ይህን ጉዳይ በመቅረፍና የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍታት፤ ህዝብ በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ አመኔታ ይዞ የተገልጋይነት ስሜቱ ከፍ እንዲልና ፈፃሚው አካልም የህዝቡ ተቀጣሪና አገልጋይ መሆኑን እንዲያውቅ በማድረግ ረገድ ጉልህ ስራዎች ተሰርተዋል።
እርግጥ በማንኛውም ሀገር ውስጥ መልካም አስተዳደር የሚታሰበው ስርዓቱ ተግባሩን ለማከናወን ካለው መልካም ፍላጎት አኳያ ነው። ምንም እንኳን የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም መልካም አስተዳደርን በሂደት ለመፈፀም ቁርጠኝነት ቢኖረውም፤ ይህ የመንግስት ቁርጠኝነት ወደ አስፈፃሚው አካል በተለይም ወደ ታችኛው የስልጣን እርከን እየወረደ በሄደ ቁጥር የመሸርሸር ሁኔታ ሲያጋጥመው ተስተውሏል። በተለይም በአንዳንድ የታችኛው የስልጣን እርከን ላይ የህዝብ መሆኑ ተዘንግቶ ፈፃሚዎች እንዳሻቸው ህዝቡን ያንገላቱታል። ከአቅም ማነስ በመነጨም ለህዝቡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ አይሰጡም። ለነገሩ ይህ ሁኔታ እንዳይቀጥል መንግስት ከህዝቡ ጋር ባካሄደው የመጀመሪያ ዙር የጥልቅ ተሃድሶ ሂደት ብዙ ለውጦችን ማምጣት ተችሏል። ይህ ለውጥ ነገም ቢሆን ህዝቡን ይዞ በማስቀጠል ችግሩን በተገቢው መንገድ መፍታት ይቻላል።
እዚህ ሀገር ውስጥ ህዝብን ማዕከል ያደረጉ፣ የተሟሉና ሊያስሩ የሚችሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አሉ። ችግሩ እነዚህን የህዝብ ተጠቃሚነት ማዕቀፎች ከመተግበሩ ላይ ነው። አንዳንዱ ችግር ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ባለማስፈፀም ጭምር የሚገለፅ ነው። ቀላል የማይባሉ ተሿሚዎችና አስፈፃሚዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ለህዝቡ በመስጠት ከመስራት ይልቅ፣ በጥልቅ ተሃድሶው የመጀመሪያ ዙር ወቅት በመንግሰትም ጭምር እንደገለፀው በራሳቸው ተጠቃሚነት ዙሪያ ይሯሯጣሉ። ህዝቡ ደግሞ ገዥውን ፓርቲ የመረጠው ፓርቲው ባቀረባቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ አመኔታን ጥሎ ነው።
ዳሩ ግን አስፈፃሚዎቹ ከገዥው ፓርቲና ከመንግስት ፍላጎትና እምነት ውጪ በመሆን ያልተገባ ተግባር ላይ (በሙስና ተግባራት ላይ በመሳተፍ ጭምር) ህዝቡን ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ እያንዳንዱን ጉዳዩች በመመልከት ረገድ ምንም ነገር በማያመልጠው ህዝብ ዕይታ ውስጥ ይገባና የቅሬታ ሁነኛ መነሾ ይሆናል። እናም ይህን መሰሉን ችግሮች ከህብረተሰቡ ጋር ሆኖ መፍታት ይቻላል።
መንግስት ነገም ቢሆን ቁርጠኛ ነው። በጥልቅ ተሃድሶው የመጀመሪያ ዙር ወቅት ከህዝቡ ጋር በመሆን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ አውጥቷል። በሺህዎች የሚቆጠሩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ፈፃሚዎች ላይም እርምጃ መውሰዷል። ይህም መንግስት መልካም አስተዳድርን እዚህ አገር ውስጥ አለማስፈን የሥርዓቱን ህልውናውን እንደሚፈታተነው ያውቃል። እናም ችግሩን ነገም ቢሆን በስር ነቀልነት ከመፍታት ወደ ኋላ አይልም። ይህን የመንግስትን ቁርጠኛ አቋም ህብረተሰቡም ሊገነዘበው ይገባል።
የኢፌዴሪ መንግስት ራሱን በራሱ የሚያርም ብቻ ሳይሆን፣ ከህብረተሰቡ በሚቀርቡት ማናቸውም መረጃዎች ጉዳዩችን እያጣራ እርምጃ እየወሰደ ዛሬ ላይ የደረሰ ነው። ህዝቡም ይህን እውነታ በመገንዘብ ለመልካም አስተዳደር ተግባራዊነት የበኩሉን ሚና ሊጠጣ ይገባል። በእያንዳንዱ የመንግስት አስፈፃሚ ተቋም ውስጥ የሚከናወኑ ስራዎች ከህዝቡ ዓይን የተሰወሩ አይደሉም። እናም ችግሮችን በቅርበት በመከታተል ማስተካከል፣ መደገፍና ከፍ ሲልም እርምጃ እንዲወሰድ ጥቆማ መስጠት የህብረተሰቡ ሃላፊነት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። እናም ነገም ቢሆን ህብረተሰቡ የመፍትሔው አካል እስከሆነ ድረስ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፈታታቸው አይቀርም። አበቃሁ።