Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የምጣኔ ሀብቱን መዋቅራዊ ለውጥ የመደገፉ ጥረት ይጠናከር

0 270

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የምጣኔ ሀብቱን መዋቅራዊ ለውጥ የመደገፉ ጥረት ይጠናከር

አባ መላኩ

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ዘመን አጠቃላይ ምጣኔ ሀብቱ 10 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል። ይህ የአገራችን ዕድገት በየዘርፉ በመሆኑ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ አድርጓል።

በ1983 ዓ.ም በአገሪቱ በከፋ ድህነት ውስጥ ይኖር የነበረው ህዝብ 48 በመቶው በላይ ነበር፤ይህ አኃዝ ባለፉት 26 ዓመታት በተደረገ ጥረት ከግማሽ በላይ መቀነስ ተችሏል። ከድህነት ወለል በታች ይኖር የነበረውን ዜጎች በመቀነስ ረገድ በዕትዕ አንድ ትግበራ ወቅት ከስድስት በመቶ በላይ ወገኖችን ወደተሻለ ህይወት ማሸጋገገር ተችሏል። በ2003 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ይህ አኃዝ 29 በመቶ በላይ የነበረው በዕቅድ ዘመኑ ማብቂያ ላይ ወደ 23 ነጥብ ሦስት በመቶ ማድረስ ተችሏል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው።

የዕትዕ አንድ ትግበራ ዘመን ግብርናው እንዲያስመዘግብ በዕቅድ የተያዘው 8 ነጥብ 6 በመቶ ነበር። ይሁንና ዘርፉ በአማካይ 6 ነጥብ ስድስት በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል። በመጀመሪያው የዕትዕ ዘመን መጀመሪያ ላይ ይህ ዘርፍ ለአገሪቱ ጂዲፒ 41 ነጥብ 5 በመቶ አስተዋፅኦ ነበረው፤ በዕቅድ ዘመኑ ማብቂያ ላይ ይህ አኃዝ ወደ 38 በመቶ ወርዷል።

በዕቅድ ዘመኑ ማብቂያ የኢንዱስትሪና የአገልግሎቱ ዘርፎች ዕድገት በማሳየታቸው የግብርናው ዘርፍ በአንፃራዊ እየቀነሰ የመጣበትን ሁኔታ መመልከት ይቻላል። ይህ የሚያመላክተው የአገሪቱ ኢኮኖሚ የተፈለገውን ያህል ፈጣን ባይሆንም መዋቅራዊ ለውጥ ማድረግ መጀመሩን ነው።  

የአገራችን ዕድገት ሁሉንም ዘርፍ የነካካ በመሆኑ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በህዝቦች መካከል እንዲኖር የራሱን አስተዋጽዖ አበርክቷል። የዕትዕ አንድ የተመዘገበው ዕድገት ዋና ዋናዎቹ በዝርዝር ሲታይ ግብርና 6 ነጥብ 6 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ 20 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፍ 10 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት  አሳይቷል። የነፍስ ወከፍ ገቢም በ2003 ዓ.ም ከነበረበት 377 የአሜሪካ ዶላር በ2007 ዓ.ም ወደ 691 ዶላር ማሳደግ ተችሏል።

ግብርና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚው መሠረት ነው። ግብርና ከአገሪቱ ህዝቦች ከ80 በመቶ አካባቢ የኅብረተሰብ ክፍልን የሚይዝ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ላይ የሚኖር ለውጥ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍልን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ለዚህ ነው መንግሥት በዚህ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ የነበረው። ለዚህም ነው በአምስት ዓመታት ውስጥ ስድስት በመቶ በላይ የኅብረተሰብ ክፍልን ከድህነት ማውጣት የተቻለው።

ይሁንና  አሁንም ወደ አንድ አራተኛው የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍላችን ከድህነት ጠለል በታች የሚገኝ በመሆኑ  በቀጣይም በርካታ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ መንግሥት በመረዳቱ አሁንም ጥረቱ የቀጠለው።

እንዲህ ያለ ፈጣን ዕድገት ቢመዘገብም ምጣኔ ሀብታዊ የመዋቅር ለውጥ የማድረግ ሂደቱ የተጠበቀውን ያህል አይደለም። ይህን ለውጥ ያመጣል ተብሎ የተገመተው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለውጥ እያሳየ ቢሆንም ዘርፉ ሰፊ መሠረት የሌለው በመሆኑ ለአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ አይደለም። በ2007 ዓ.ም ላይ ግብርናው ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) 38 ነጥብ ስድስት በመቶ፣ ኢንዱስትሪው 15 ነጥብ አንድ እንዲሁም አገልግሎቱ 46 ነጥብ ሦስት ነው።

በመጀመሪያው ዕትዕ የመንግሥት የአገር ውስጥ ገቢም ሆነ ወጪ ከሦስት እጥፍ በላይ አድጓል። የመንግሥት የግብር አሰባሰብ ሂደት በዓመት በአማካይ 31 በመቶ ዕድገት ቢያሳይም አሁንም የተፈለገውን ያህል አላደገም። ይሁንና አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂ.ዲ.ፒ)ን 13 ነጥብ 3 በመቶ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

ይህ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች ማለትም 15 በመቶ የመሰብሰብ አቅም ካላቸው አገሮች ጋር እንኳን ሲነጻፀር ዝቅተኛ የሚባል ነው። ይሁንና የግብር አሰባሰቡ ሂደት ቀድሞ ከነበረበት መሻሻል ታይቶበታል። በምክንያትነት የሚጠቀሰውም የተሻለ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት መዘርጋት በመቻሉና በግብር ከፋዮች ዘንድ የተሻለ ግንዛቤ በመፈጠሩ ነው። አሁንም በዚህ ረገድ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ረጅም መንገድ መጓዝ የግድ ይላል።  

በዕቅድ ዘመኑ ስለ ቁጠባ ጠቀሜታ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመከናወናቸውና መንግሥት ለሜጋ ኘሮጀክቶች ቦንድ በመሸጡ ምክንያት እንዲሁም በቤቶች ግንባታ መጀመር ሣቢያ የአገር ውስጥ የቁጠባ ባህል በሁለት እጥፍ ማደግ ችሏል። የቁጠባ ባህሉ መሻሻል ቢያሳይም አሁንም የቁጠባ መጠኑና ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልገው የገንዘብ ፍላጐት መካከል ሰፊ ልዩነት ይስተዋላል።

በመሆኑም አሁንም ዘርፉን ለማጠናከር የመንግሥት ድጋፍን በማጎልበት የቁጠባ መጠንን ማሳደግ አስፈላጊ ነው። የቁጠባ ገንዘብን በማሳደግ ተቋማት ለኢንቨስትመንት መስፋፋት የሚውል መዋዕለ ንዋይ በማሰባሰብ ረገድ አቅማቸውን ማሳደግ ይኖርባቸዋል።

ምጣኔ ሀብታዊ መዋቅራዊ ለውጥ ሲከሰት የሀብትና የፖሊሲ ለውጦች ማድረግን፣ ከተለምዶ ወደ አዲስና ዘመናዊ አሠራር መሸጋገርን የሚጠይቅ እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ  ነው። በመጀመሪያ የዕትዕ ዘመን ምጣኔ ሀብቱ አዝጋሚና የተጠበቀውን ያህል ባይሆንም ከግብርናው ወደ አገልግሎት እንዲሁም ወደ ኢንዱስትሪ የማደግ ሂደት አሳይቷል።

አገራችን ወደ ኢንዱስትሪ ልማት ምጣኔ ሀብት የምታደርገው ጉዞ መልካም ጅማሮ ላይ ቢገኝም አሁንም የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ ውስንነቶች ታይቶበታል። ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተካሄዱ ኢንቨስትመንቶች እሴት በማይጨምሩ ዘርፎች ላይ የተካሄዱ እንደሆኑ በዕትዕ አንድ አፈጻጸም ላይ ታይቷል።

በሁለተኛው የዕትዕ ዘመን መንግሥት እሴት ለሚጨምሩ ባለሀብቶች ልዩ ትኩረት ማለትም የገንዘብ፣ የቴክኒክና ሌሎች ድጋፎችን በመስጠት የምጣኔ ሀብቱን መዋቅራዊ ለውጥ ለመደገፍ ጥረት መደረግ ይኖርበታል።

በመጀመሪያው የዕትዕ ዘመን ዋነኛ ትኩረት መስክ የነበረው የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ነበር። ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ይህን ዓላማ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። የግብርና ግብዓቶችን በማሳደግ፣ የግብርና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን ቁጥር በመጨመር ውጤታማ ሥራ ማከናወን ተችሏል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy