Artcles

የሥራና የቁጠባ ባህላችን መለወጥ በመጀመሩ በስኬት ጎዳና መጓዝ ጀምረናል!

By Admin

May 07, 2017

የሥራና የቁጠባ ባህላችን መለወጥ በመጀመሩ በስኬት ጎዳና መጓዝ ጀምረናል!

ወንድይራድ ኃብተየስ

የኢፌዴሪ መንግስት ለወጣቶች የስራ ፈጣራ  መነሻ የሚሆን  10 ቢሊዮን ብር በላይ መድቧል፡፡ በተመሳሳይ  የክልል ማንግስታትና ከተማ አስተዳዳሮች  እንደየአቅማቸው ከበጀቶቻቸው በመቀነስ  ከፍተኛ ገንዘብ ለዚሁ ዓላማ መድበዋል። መንግስት ይህን ገንዘብ  ለወጣቶች የስራ ፈጠራ መነሻ እንዲሆናቸው የመደበው  የተትረፈረፈ  ወይም በቂ  በጀት ኖሮት ሳይሆን፤ መንግስት ለወጣቶች ያለውንው ወገንተኝነትና  ህዝባዊነት ለመግለጽ ነው። ይህ ገነዘብም በቂ ነው ማለት ባይቻልም ለስራ መነሻ መሆን የሚችል ነው።  ከሌላ በጀት ተቀንሶ ለወጣቶች የስራ መነሻ እንዲሆን የተመደበ ገንዘብን ወጣቶች  በአግባብ በመጠቀም ራሳቸውንና አገራቸውን የመለወጥ ሀላፊነት ይኖርባቸዋል። ስራን በማክበርና ቁጠባን በማጠናከር መለወጥ ይቻላል። በዚህ ዙሪያ ዛሬ የአንድ ወጣት ተሞክሮን ላካፍላችሁ። እዮብ ረጋሳ ይባላል። ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ነው።  እዮብ በብረታ ብረት ስራ ከቴክኒክና ሙያ ተቋም ተመርቋል።  

እዮብ እንደሚለው ከቴክኒክና ሙያ  ተቋም ተመርቆ  ለአንድ ዓመት ያህል ስራ አልነበረውም። ሁሉንም ነገር ከቤተሰቦቼ  እጠብቅ ስለነበር፣ የጥገኝነት ስሜት ያድርብኝ ስለነበር ኑሮ በጣም ያስጠላኝ ነበር። በቀጣይ ህይወቴ ምን ይሆን እያልኩ እጨነቅ ነበር። ይሁንና በሚሌኒየሙ ማለትም በ1999 ዓ ም አጋማሽ አካባቢ መንግስት ስራ አጦችን በአነስተኛና ጥቃቅን ሲያደራጅ ስለነበር  እዮብ   አብረውት ከተማሩ ከሶስት ጓደኞቹ ጋር በመደራጀት በብረታ ብረት ስራ የተሰማራ ወጣት ነው።

እዮብ እንደሚለው በወቅቱ መንግስት አጭር ስልጠና፣ ብድር፣ መስሪያ ቦታ እንዲሁም የገበያ ትስስር አመቻችቶላቸዋል። ይሁንና ስራ እንደጀመርን አካባቢ በርካታ ውጣ ውረዶች ገጥመውን ነበር። አዲስ ስለሆን ገበያም አልነበረንም። ይሁንና መንግስት ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጋር  የገበያ ትስስር እንዲፈጠርልን በማድረጉ በስራችን ላይ ለውጥ ማየት ጀመርን። ብዙም ሳንጠናከር አንዱ ጓደኛችን ዲቪ ደረሰውና ወደ ውጭ ሄደ። ሁለታችን ግን አሁንም እየሰራን ነው።

ስራ የጀመርነው አስፈላጊው የስራ መሳሪያዎች ሳይሟሉልን ነበር። በብድር ያገኘነው ገንዘብ ለስራ መነሻ የሚሆኑ መሳሪያዎችን ለማሟላት እንጂ ሁሉንም መሳሪያ ሊያሟላ የሚችል አልነበረም። ወጣቶች አሁንም መረዳት ያለባቸው ነገር አዲስ ስራ ጀማሪ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንደማይሆንላቸው ማሰብ ይኖርባቸዋል።

ዛሬ ላይ የእነእዮብ ድርጅት አጠቃላይ ሃብት ከስምንት መቶ ሺህ ብር በላይ እንደደረሰ እዮብ ራሱ ይናገራል። ድርጅቱ አንድ የስራ ደብል ፒክ አፕ መኪናም  ባለቤት ነው።   የእነእዮብ ድርጅት ሶስት ተጨማሪ ሰራተኞች በመጨመር አምስት ደርሰዋል። እንደእዮብ ገለጻ አሁን ላይ ድርጅታቸው ከየትኛውም ድርጅት ጋር ተወዳድሮ ስራ ማግኘት የሚችልበት ወይም በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል።  በመሆኑም ድርጅቱ ዛሬ ላይ የማንንም ድጋፍ አይፈልግም። ዛሬ እዮብ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኛም ነው። ድርጅቱን በበላይነት የስተዳድራል። እኛ ይላል እዮብ በአነስተኛና ጥቃቅን በመደራጀት በአጭር ጊዜ መለወጥ የቻልነው መንግስት ያደረገልንን ድጋፍ በአግባብ  መጠቀም በመቻላችን ነው።

እዮብ ስለቁጠባ እንዲህ ይላል። ለእኛ ድርጅት መለወጥ ዋንኛው ምክንያት ቁጠባ ነው። የመጀመሪያው የተሰጠንን ብድር በወቅቱ መመለስ በመቻላችን ተጨማሪ ብድሮችን ማግኘት ችለን ነበር። እንደእኔ ይላል እዮብ  ቁጠባ የለውጥ ዋንኛው መሰረት ነው። ስራ የሚጀምር ማንኛውም አካል ይላል እዮብ ቁጠባን መልመድ መቻል አለለበት። አለበለዚያ ይላል እዮብ ካገኟት ትንሽ ገቢ ላይ መቆጠብ ካልተቻለ ወይም ማደግ ወይም መለወጥ አይኖርም። ሌላው ለስኬት የሚያበቃው ነገር ይላል እዮብ  ወጣቶች ስራ ማክበር መቻል አለባቸው። እኛ ስራ ስንጀምር አካባቢ የሁላችንም ቤተሰቦች ደስተኛ አልነበሩም። አንዳቸውም አያበረታቱኝም ነበር።  ቤተሰቦቻችን ስራው ጥሩ አይደለም አትስሩ፣ ይቅርባችሁ  ባይሉንም፤ የአንዳችንም የቤተሰብ አባላት አይዟችሁ ነገ ትለወጣላችሁ በርቱ፣ ከጎናችሁ ነን የሚለን አልነበረም። ይሁንና ዛሬ ከራሳችን አልፈን ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠር ችለናል።  

እዮብ እንደሚለው ስራ በሚጀመርበት ወቅት ሁሉም ነገር የተሟላ እንደማይሆን ወጣቶች ሊገነዘቡ ይገባል። ወጣቶች ሁሉን ነገር መንግስት እንዲያመቻችላቸውም መጠበቅ የለባቸውም፡፡  ወጣቶች ያገኟትን ድጋፍ ተጠቅመው በራሳቸው ጥረት መለወጥ መቻል አለባቸው እንጂ ሁሉም ነገር በአንዴ ሊሟላ አይችልም ሲል ምክሩን ይለግሳል።  

በአሁኑ ሰዓት መንግስት በጀት ከመመደብ ጎን ለጎን ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ስራ አጥ ወጣቶችን የመመዝገብ፣ የመለየት፣ ማደራጀትና የማሰልጠን  ስራዎች  በስፋት እየተከናወነ ነው፡፡ በአንዳንድ ክልሎች ለወጣቶች ስልጠና እየተሰጠ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ከዚያም አልፈው የብድር አገልግሎት በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። ወጣቶችም ስራን በማክበር  ማለትም ያገኙትን ስራ በመስራት ልምድ መቅሰምና ጥሪት መቋጠር የኖርባቸዋል። በተጨማሪም  ወጣቶች የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ ነገ እቀየራለሁ የሚል ስሜት ሊያድርባቸው ይገባል።

እዮብ እንደሚለው አሁን ለወጣቶች የሚሰጣቸው ገንዘብ አነስተኛ ሊሆን ቢችልም  እንኳን አብቅተው  ስራ መጀመር፤  እንዲሁም  የተሰማሩበትን የስራ መስክ በማክበርና በመውደድ ጠንክረው በመስራት ውጤታማ መሆን ይችላሉ።  ከዚህም ባሻገር ከሚያገኙት የዕለት ገቢ ላይ በመቆጠብ  የተበደሩትን ገንዘብ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ በመመለስ ለሌሎች እህትና ወንድሞቻቸውም  እነሱ ያገኙትን የበድር ዕድል  ተጠቃሚ እንዲሆኑ  ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ወጣቶች መንግስት በብድር የሰጣቸውን ገንዘብ በሀላፊነት ስሜት ሊጠቀሙበት ይገባል።

እዮብ እንደሚለው ማንኛውም መለወጥ የሚፈልግ አካል ወጣት ሆነ አዛውንት    በመጀመሪያ የተሰማራበትን የስራ መስክ  መውደድና ማክበር  አለበት። ማንም ሰው ስራ ሳይንቅ  ዝቅ ብሎ የመስራት ልምድን ሊያዳብር ይገባዋል። ለመለወጥ ስራን ከመውደድና ማክበር ባሻገር ይላል እዮብ  ቁጠባን ልምድ ማድረግ ይገባል። ማደግ መለወጥ የሚቻለው ገቢህ ከፍተኛ ስለሆነ ሳይሆን ከምታገኘው ላይ መቆጠብ ሲቻል ብቻ ነው። አንዳንድ ወጣቶች ትምህርት መስመራችንና ስራችን አይጣጣምም ሲሉ ሌሎች ደግሞ ይህን ያህል ዓመት ተምሬ እንዴት ይህን ስራ እሰራለሁ በማለት ስራ ሲያማርጡ፤ አንዳንዶች ደግሞ  ክፍያው ዝቅተኛ ነው በማለት  ያለስራ መቀመጥን ይመርጣሉ። ይህ አግባብ አይደለም። ዝቅ ብሎ መስራትን የማያውቅ መነሻውንም ሆነ ኋላም መድረሻውን ስለማያውቀው ገንዘብ አያያዝ አይሆንለትም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስራ የማማረጥ አባዜ  በወጣቶቻችን አካባቢ ለውጥ የታየበት ሁኔታ አለ። ወላጆችም ከጥቂት ዓመታት በፊት  ልጄ ይህን አይሰራም እንዲህ ያለ ቦታ አይሄድም ወዘተ የሚል ቅሬታ ያቀርቡ ነበር። የሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ አስተሳሰብም ለውጥ እየታየበት ነው።  ይህን የስራ ማክበር ባህል በሁሉም ዘንድ እንዲሰርጽ በማድረግ አገራችንን መቀየር  ይኖርብናል። በተመሳሳይ የቁጠባ ባህላችንም እጅጉን ተለውጧል ማለት ይቻላል። በመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ወቅት አገራዊ ቁጠባን በ2003 ዓ ም ከነበረበት 9 በመቶ አካባቢ  በ2007 ዓ ም ማብቂያ ላይ ወደ 21 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የተቀመጠውን ቁጠባ ግብ ማሳካት ከተቻለ፣ የአገር ውስጥ ቁጠባ ለአገራችን የኢንቨስትመንት መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።   

እዮብ እንደሚለው በቅርብ የሚያውቁኝ ሰዎች የትላንት ምንነቴን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ  የጥንካሬ አብነት አድርገው ያነሱኛል። አዎ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለዚህ መብቃቴ በምሳሌነት ብነሳ  አይበዛብኝም። እንደኔ እደኔ ይላል እዮብ ድህነትን ያላየ ሰው ለመለወጥ በጣም ይከብደዋል። ምክንያቱም መነሻውን አያውቀውም። እዮብ ይህን ሲል አንድ ነገር ታወሰኝ። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ  እንዲህ ይሉ ነበር “የድህነት ታሪካችን ቁጭት ሊፈጥርብን ከቻለ መለወጥ እንችላለን” ያሉት ከእዮብ አባባል ጋር  ተመሳሰለብኝ።

እዮብ እንደሚለው  ሰው ያገኘውን መስራት አለበት። ስራ መምረጥ የሚቻለው ጠንከር ሲሉና ጥሪት ሲያዝ ነው። በባዶ ኪስ ተምሬለሁ እኔ እንዲህ ወይም እንዲያ ነኝ ማለት ምን ጥቅም አለው። ሰው ገንዘብ ማግኘት ያለበት  ወጥቶና ወርዶ መሆን መቻል አለበት።  ምክንያቱም ይላል እዮብ ሰው ለፍቶ ያገኛትን ገንዘብ እንዴት ሆኖ እንዳገኛት ስለሚያውቅ እንደው እንደዋዛ አይበትናትም። ገንዘብ አክባሪዋን ትፈልጋለች ይባላል። እውነት ነው፤ አንድ ብር ሁለት የምትሆነው ሌላ ጓደኛ ሲጨመርባት ነው። ቁጠባ ካልተለመደ ምንም ያህል ገቢ ቢያድግ ፍላጎትህም አብሮ ያድግና መቆጠብ አቻልም፤ ቁጠባ ከሌለ ደግሞ መለወጥ አይቻልም። እንደኔ ለመለወጥ መሰረቱ ካገኘሃት ገቢ ላይ እንደአቅም መቆጠብ ሲቻል ነው።   

ለማደግ ይላል እዮብ ዋናው ነገር ብዙ ገንዘብ ማግኘት ሳይሆን ከገቢህ ላይ ምን ያህሉን  ቆጠብኩ ነው። ቁጠባ ያለመደ ሰው በፍጹም ሊያድግ አይችልም። ሰው የሰራውን ሁሉ የሚበላው ከሆነ መለወጥ እንደማይችል ሊያውቅ ይገባል። አንድ አባባል አለ “ሆድ እንዳሳዩት ነው” ይባላል። ያገኘነውን ገንዘብ ሁሉ የምንበላውና የምንጠጣው ከሆነ መለወጥ ከቶ አይታሰብም። ስራን መውደድ፣ ማክበር፣ ወጪን መቀነስና ቁጠባን ማሳደግ  ከተቻለ እድገት ይኖራል። ካልሆነ ግን ሰርቶ ለሆድ ነው። ሲል እዮብ ታሪኩን አጫወተኝ።