Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቀሩትን የሳዑዲ የምህረት አዋጅ ትግበራ ቀናት ኢትዮጵያውያኑ እንዲጠቀሙ መንግስት ጠየቀ

0 480

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሳዑዲ አረቢያ መንግስት የመኖሪያ እና የስራ ፍቃድ የሌላቸውን የውጭ ሀገራት ዜጎች በ90 ቀናት ውስጥ እንዲወጡ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ቢጋመስም ወደ ሃገራቸው የሚመለሱ ዜጎች ቁጥር አሁንም አናሳ ነው።

ዛሬን ጨምሮ 43 ቀናት ብቻ በቀሩት ቀነ ገደብ ተጠቅመው የሚወጡ ዜጎች ያለምንም እንግልት ወደ ሃገራቸው መመለስ የሚችሉበት እድል መመቻቸቱን ነው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚገልፀው።

የሳዑዲ መንግስት አዋጁን ጥሰው ለሚከርሙ የውጭ ሀገራት ዜጎች ደግሞ እስራት እና ከ15 እስከ 50 ሺህ የሳዑዲ ሪያል እንደሚቀጡ ገልጿል።

በሳዑዲ አረቢያ መንግስት የተሰጠው የምህረት አዋጅ እና ቀነ ገደብ ግን በዚያች ሃገር በሚገኙ እና ወደ ሃገራቸው በተመለሱ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የተደበላለቀ ስሜትን ፈጥሯል።

ከአመታት ቆይታ በኋላ በአዋጁ ምክንያት ወደ ሃገሯ የተመለሰችው ወጣት መስተዋት እርሷ ሃገሯ ብትገባም የሌሎችን መመለስ ግን የምትደግፍ አትመስልም ።

እንደ እርሷ ገለጻ ዓረብ ሃገር ፈተናው የበዛ ቢሆንም ሄዶ ስራ መስራት ያስፈልጋልና ዛሬ ብትመለስም ወደዛው ስለመመለስ እንደምታስብ ትናገራለች።

ከመስታወት ጋር ወደ ሃገሯ የተመለሰችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ደግሞ ከጓደኛዋ በተቃራኒው በዚያች ሃገር መቆየት ካለው ፈተና አንጻር የማይመከር ነው ትላለች።

ከአራት ዓመት በፊት በሳዑዲ እስር ቤት ከርሞ ወደ ሀገሩ የተመለሰው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሃብቶም ደግሞ፥ ዓመታት ለፍቶ ያፈራውን ንብረት እዚያው ትቶ ወደ ሃገሩ መግባቱን ያስታውሳል።

ይህ የእርሱ እጣ ፋንታ በሌሎች የሃገሩ ልጆች ላይ እንዳይደርስም አዋጁን ተጠቅመው እንዲወጡ ይመክራል።

ያለ መኖሪያና የስራ ፍቃድ በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 400 ሺህ እንደሚደርስ ይገመታል።

ከዚህ ቁጥር መካከል ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው እና አሁን ላይ የተሰጠውን የምህረት አዋጅ ተጠቅመው ወደ ሃገራቸው የሚመሰሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ግን የታሰበውን ያህል አለመሆኑን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በ90 ቀናት የምህረት አዋጁ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ 23 ሺህ ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሰነድ መውሰዳቸውን የሚኒስቴሩቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ተናግረዋል፡፡

አቶ መለስ ዓለም በተሰጠው ቀነ ገደብ ከሀገሪቱ አለመውጣት ሰፊውን እና የተሻለውን አማራጭ ትቶ ራስን ለእንግልት መዳረግ መሆኑን ተናግረዋል።

የሳዑዲ መንግስት ህጉን ላከበረ ብሎ ከሰጠው እድል ባሻገር መንግስትም ለዜጎቹ ከቀረጥ ነፃ ንብረቶቻቸውን ወደ አገራቸው እንዲያስገቡ እና ሌሎችንም ድጋፎች እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል ቃል አቀባዩ።

ሚኒስቴሩ በሳዑዲ የሚገኙ ኤምባሲ እና ቆንስላ ፅህፈት ቤቶችን በሰው ሃይል እና በገንዘብ ከማጠናከር ባለፈ፥ ለዚህ ስራ ሲባል የተቋቋሙትን ሰባት የመውጫ ሰነድ መስጫ ማዕከላትን እያጠናከረ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻርም ቤተሰብን ጨምሮ ሀገር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አዋጁ የሚመለከታቸው ዜጎች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy