CURRENT

የቀድሞ የአርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንትና ዋና ጸሐፊ በእስራት ተቀጡ

By Admin

May 06, 2017

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት ለሆኑና አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለሚኖሩ ቤት ለሌላቸው አርበኞች የሰጣቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶችን፣ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ተብለው የቀድሞ የማኅበሩ ፕሬዚዳንትና ዋና ጸሐፊ በስድስት ወራት ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ተወሰነ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሐሙስ ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ እንዳስታወቀው፣ የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት በነበሩት ሊቀ ትጉኃን አስታጥቄ አባተና የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ በነበሩት አሥር አለቃ ሰጥአርጌ አያሌው፣ ስድስት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማኅበሩ አባላት ሳይሆን ለግል ዘመዶቻቸው መስጠታቸውን ዓቃቤ ሕግ  በሰነድና በሰው ማስረጃ አረጋግጧል፡፡

ሊቀ ትጉኃን አስታጥቄ ለራሳቸው ከመውሰዳቸውም በተጨማሪ ለእህትና ለወንድማቸው መውሰዳቸውን፣ ዋና ጸሐፊውም ለራሳቸውና ለሌላ ሰው ማስተላለፋቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ሁለቱም ተከሳሾች ሚያዝያ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ጥፋተኛ በመባላቸው የቅጣት ማቅለያ አቅርበው፣ እያንዳንዳቸው አምስት አምስት ማቅለያ ተይዞላቸው ነበር፡፡ በዚህም ጥፋተኛ በተባሉበት የቅጣት እርከን እያንዳንዳቸው ስድስት ወራት ጽኑ እስራትና 1,500 ብር እንዲቀጡ ውሳኔ በመሰጠቱ፣ ወደ ማረሚያ ቤት ተልከዋል፡፡