Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተለያዩ ማንነቶችን ማስታረቅ የቻለው የፌዴራል ስርዓት!

0 347

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተለያዩ ማንነቶችን ማስታረቅ የቻለው የፌዴራል ስርዓት!

ወንድይራድ ኃብተየስ

በፌዴራል ስርዓታችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ወይም ቡድኖች አካባቢያቸውን ራሳቸው እንዲያስተዳደሩ ዕድል ከመስጠቱም  ባሻገር በመዕከላዊ መንግስትም እያንዳንዱ ቡድን ተገቢው ውክልና እንዲያገኝ  አስችሏል።ከዚህ በፊት በነበሩ የኢትዮጵያ መንግስታት እንኳን በፌዴራል ይቅርና በአካባቢ አስተዳደር ውክልና ያልነበራቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዛሬ በብሔራዊ ደረጃ የፖሊሲ አወጣጥ በአገሪቱ ቁልፍ ጉዳዮች ውሳኔ ማሳለፍ ችለዋል። በመሆኑም አሁን ላይ ህዝቦች በተወካያችን አልተዳደርንም እንዲሁም  በፌዴራል ደረጃ ተገቢው ውክልና አላገኘንም የሚል ቅሬታ ሲነሳ አይደመጥም።  

ይሁንና የትምክህትና የጥበት ሃይሎች በሁለት ተቃራኒ ጽንፍ ቆመው የህዝቦችን አብሮነት የሚሸረሽር የአገራችንን አንድነት የሚያናጋ ድርጊት ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ታይተዋል። እነዚህ ሁለት ሃይሎች ራሳቸውን በየጊዜው እየቀያየሩ፣ ለአገርና ለህዝብ መብት የቆሙ በመምሰል ወጣቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለማምራት ጥረት አድርገዋል። እነዚህ የጥፋት ሃይሎች ነገም ከዚህ ድርጊታቸው ይቆጠባሉ ማለት አይቻልም። በመሆኑም እነዚህን ሃይሎች የመታገል የእያንዳንዱ አገር ወዳድ ዜጋ ግዴታ ነው።

በኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ውስጥ ሁለት ጉልህ ማንነቶች ይስተዋላሉ። እነዚህም የብሄር/የብሄረሰብ ወይም የቡድን ማንነቶችና ኢትዮጵያዊ ማንነት ናቸው። እነዚህ ሁለት ማንነቶች  ሳይዛነፉ እኩል ሊዳብሩና ሊተገበሩ ይገባል። እንደእኔ እይታ እነዚህን ሁለት ማንነቶችን የኢፌዴሪ የፌዴራል ስርዓት ማስታረቅ የሚቻልበትን ሁኔታ ፈጥሯል። አማራ ሆኖ ኢትዮጵያዊ፤ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ፤ ሶማሌ ሆኖ ኢትዮጵያዊ ወዘተ እየተቻለ የትምክህት ሃይሎች በደፈናው የቡድን ማንነትህን ካልተውክ ኢትዮጵያዊ አትባልም ሲሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ  ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል መስማት የሚያማቸው የጥበት ሃይሎች አሉ። እነዚህ የትምክህትና የጥበት ሃይሎች በኢትዮጵያ ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ትናንሽ ነገሮችን በማነፍነፍና በማጎን  በኢትዮጵያዊ ማንነትና በብሔር ማንነት መካከል መጣረስ እንዲፈጠር አበክረው ሲሰሩ ቆይተዋል።

እነዚህ አካሎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አገራችንን ወደ ሁከትና ብጥብጥ ለመክተት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። በቅርቡ እንኳን  በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በህዝቦች መካከል ቅራኔ እንዲፈጠርና የፌዴራል ስርዓቱ ችግር አድርገው ለማረብ ሲሯሯጡ ተስተውለዋል። እነዚህ ሃይሎች በፈጠሩት ሁከት ዜጎች ተገድለዋል፣ ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለዋል፤ ንብረታቸው ተዘርፏል፣ የስነልቦና ጫና እንዲፈጠርባቸው ወዘተ በአጠቃላይ መልካም ያልሆኑ ነገሮች ለዘመናት በኑሩባቸው አካባቢዎች እንዲደርስባቸው ተደርጓል። እነዚህ መጥፎ ነገሮች ዳግም በአገራችን እንዳይከሰቱ ጥገኞችን መዋጋት የሁላችንም ግዴታ ነው።

በቀጣይ የብሄር ማንነቶችንና ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለማጋጨት ጥረት የሚያደርጉ አካላትን ከድርጊታችሁ ታቀቡ ካላልናቸው ችግሮቻችን ሊያወሳሰቡብን ይችላሉ።  እነዚህ ሁለት ማንነቶች አንዱ በአንዱ መስዋዕትነት የሚገኝ ሳይሆን ሁለቱንም ማታረቅ የሚቻልበት ሁኔታ በፌዴራል ስርዓታችን ተመቻችቷል።  ከላይ እንዳነሳሁት መንግስት በዘርፉ  በቂ ልምድና እውቀት ካላቸው ምሁራን ጋር በቅርበት በመስራት ህዝቦች ስለፌዴራል ስርዓታችን በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ማደረግ ይኖርበታል። ከዚህ ባሻገር መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት በመስራረት የጥበትና የትምክህት መፈልፈያ የሆነውን ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት ይኖርባቸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ትናንሽ ለሚባሉ ችግሮች ሳይቀር የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ምላሽ በወቅቱ ሊሰጥ ይገባል። የክልል ወሰን ወይም የማንነት ጥያቄዎች ለአገራችን የሁከት መነሻ ከቶ መሆን የለባቸውም።  ከላይ እንደጠቀስኩት መንግስትና ህብረተሰቡ በቅርበት በመስራት ለትምክህትና ጥበት መሸሸጊያ የሆነውን  የኪራይ ሰብሳቢነት አካሄድ ማጥፋት ይኖርባቸዋል። ኪራይ ሰብሳቢዎች መቼም ቢሆን ለህዝብና አገር የሚጨነቁበት ነገር አይኖርም።  መንግስት የህዝቦች እውነተኛ ጥያቄዎችን በመለየት በወቅቱ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አንዱ የጥገኞችን አካሄድ ማክሸፍ ይኖርበታል።  

እኛ ኢትዮጵያዊያን ሁላችንም ከተለያዩ  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ብንሆንም ሁላችንንም በአንድነት የሚያስተሳስር  የጋራ ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት መኖሩን ማሰብ ተገቢ ነው።  ትናንሽ ግጭቶች ነገም ተነገወዲያም መቼም መከሰታቸው አይቀርም። እንኳን በአገር ደረጃ ይቅርና  ግጭት በቤተሰብ ደረጃም ይከሰታል። ይሁንና ዋናው ነገር ለችግሮች በሰለጠነ መንገድ መፍትሄ መፈለግ ትልቅ ነገር ነው። የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ደግሞ በዚህ ረገድ ራሱን በራሱ ማስተካከል የሚችልበት አሰራር ያለው ነው። በየአካባቢው የተከሰቱ ግጭቶችን ስንመለከታቸው በህዝቦች መካከል ስር የሰደደ ለግጭት የሚዳርግ ቅሬታ የለም።

የብሔር ማንነታችንን በአካባቢያዊ አስተዳደሮች ልንጠቀምባቸው፣ ቡድናዊ ትስስሮቻችንን ልናጎለብትባቸው እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሌሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር የምንተሳሰርበት ሊሆን ይገባል። ኢትዮጵያዊ ማንነት ሌሎች ማንነቶችን ደፍጥጦ እንዲገኝ አለማድረግ በተመሳሳይ የቡድን ወይም የብሔር ማንነትን ከኢትዮጵያዊ ማንነት  በላይ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ የፌዴራሊዝም ስርዓት  እንዲፈጠር ምክንያት ስለሚሆን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ሁሉንም በልክ በልክ የማናስኬደው ከሆነ ዋጋ ያስከፍለናል። ለጥበትና ለትምክህት ሃይሉ በር እንከፍታለን። በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህን በአግባብ ተገንዝቦ ፍላጎቶቹን  ማስታረቅ ይኖርብናል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የፌዴራል ስርዓት ላይ ራስን በራስ በማስተዳደር ፅንሰ ሐሳብ ላይ የተሳሳተ ዕይታዎች ይስተዋላሉ። ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት የራስን ቋንቋና ባህልን መጠቀምና ማዳበር እንጂ  አናሳዎችን ማጥቃት መሆን የለበትም። በቅርቡ በአገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ያስተዋልናቸው አንዳንድ እጥረቶች አሉ። ቡድናዊ ማንነቶች ከኢትዮጵያ ማንነት እኩል ሊጎለብት ሲገባቸው  በአንዳንድ  አካባቢዎች  የቡድነትኘነት ስሜት በተሳሳተ መንገድ ተተርጉሞ አገርን በሚያጠፋ መልኩ ተመልክተናል።  ይህ ስሜት አንድነትን የሚሸረሽሩ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ የአገራችንን ሰላም የሚያውክ ነው። ለዚህ መጥፎ ስሜት ምክንያት የሆኑት ደግሞ የትምክህትና የጥበት አስተሳሰቦች ናቸው።  

የቡድንና ኢትዮጵያዊ  ማንነቶች ማመጋገብ የማይቻል ከሆነ   አደገኛ ነገር ሊፈጠር ይችላል። ለሰላማችን መደፍረስ ለአንድነታችን መላላት መክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  በአንድነት ሊዋጋቸው ይገባል።  እንዲህ ያሉ አካሄዶች በክልል መንግስታትም ይሁን በፌዴራል መንግስቱ በወቅቱ ተገቢው እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። ጥፋተኞች ለህግ ቀርበው እንደየጥፋታቸው ተጠያቂ መሆን መቻል አለባቸው። በቅርቡ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው ጥፋተኞች ላይ ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድ ማመላከቱ በጎ ጅምር ነው።  

የፌዴራል ስርዓታችን የአገሪቱን ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ቀርፏል። የመጀመሪያው ለዘመናት የአገራችን ችግር ሆኖ የኖረውን የፖለቲካ ችግር ማለትም የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የማንነትና የዕኩልነት ጥያቄዎች መመለስ አስችሏል። ሌላው ደግሞ የአገሪቱ የልማት ፍላጎትን መመለስ የሚያስችል አሰራርን ዘርግቷል።  የፌዴራል ስርዓቱ ፍተሃዊ ልማትን በማስፈንና ድኅነትን በመቀነስ ረገድ ጉልህ  ሚና ተጫውቷል። ባለፉት ሥርዓቶች ፍትሃዊ የሆነ የሃብትና የስልጣን ክፍፍል አለመኖር፣ የህዝቦች የማንነት ጥያቄ በሰላማዊ መንግድ ለማስተናገድ አለመፈለግ እንዲሁም የዜጐች መብትና ነፃነት ያለመከበሩ ተደማምሮ በአገራችን ለረጅም ዘመናት ለቆየ አለመረጋጋት፤አለመተማመንና ከዚህም ባለፈ ለአስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ዳርጎን ቆይቷል። ይህን ችግር የቀረፈው የፌዴራል ስርዓታችን ነው። ይህን ስርዓት የመንከባከብ የሁሉም ሰላም ወዳድ ዜጋ ግዴታ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy