Artcles

የተቋሙን ገለልተኝነት በምን መመዘኛ ማጣጣል ይቻላል?

By Admin

May 01, 2017

የተቋሙን ገለልተኝነት በምን መመዘኛ ማጣጣል ይቻላል?/ወንድይራድ ኃብተየስ/

ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ላይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየገለበተ መጥቷል። እንዲያም ሆኖ ይህንን እውነታ በተገቢው መንገድ የመገንዘብ ችግር አሁን…አሁን ላይ መንፀባረቁ አልቀረም፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ዐቢይ ጉዳይ መልካም አስተዳደር የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካልታከለበት በመንግሥት ጥረት ብቻ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ነው። ማንኛውም ህዝብ ያልተሳተፈበት ጉዳይ ተፈፃሚ ሊሆን አይችልምና።

በመሆኑም በመንግሥት በኩል መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉና በሂደት የሚከናወኑ ቁርጠኛ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው መላው ህዝብም ዛሬም እንደ ትናንቱ ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይኖርበታል።

በተለይም ቁልፍ የዴሞክራሲ ማስፈኛ ተቋማት በሚባሉት እንደ የሰብዓዊ መብት እና የህዝብ እንባ ጠባቂ ያሉ ተቋማትን በአግባቡ በመጠቀምና የሚፈጠሩ ችግሮችን ተከታትሎ በማሳወቅ ለመልካም አስተዳደር እመርታ መትጋት ከማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው።

መንግሥት ምንም እንኳን ይህን የማስፈፀም ግዴታ ቢኖርበትም ህገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት ብሎም ራሱም ለዴሞክራሲ ሥር መስደድ ካለው ቀናዒ ፍላጎት በመነሳት፤ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በተለይም የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የዜጎች አቤቱታ እንዲደመጥና ተገቢው ምላሽ እንዲሰጥ ተከታትሎ የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ የሚያግዝ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን አቋቁሟል።

መንግሥት ለዴሞክራሲው ግንባታ እውን መሆንና ላሳየው የማይናወጥ ቁርጠኝነት ተመስጋኝ ሊሆን ሲገባ፤ ያለ አንዳች በቂ ማስረጃ በመንግሥትና በተቋሙ ላይ በደፈና ጥላቻ እየታገዙ የውርጅብኝ መዓት ማውረድ ተገቢ አይደለም። ክንዋኔዎቹን በአንክሮና በሰከነ አዕምሮ ማየት ተገቢ ይሆናል።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የዜጎች አስተዳደራዊ በደል ተገቢው ምላሽ እንዲያገኝ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ ይታወቃል። በስሜት ብቻ እየተገፋፉ የተቋሙን ስም ለማጥፋት መሯሯጥ እንዲሁም መንግሥት በዘርፉ እያደረገ ያለውን ጥረት በፀረ ዴሞክራሲያዊነት ታውሮ ላለመቀበልና ለማጣጣል መሞከር ተቀባይነት አይኖረውም።

 

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ሕዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች አንዳንድ አካባቢ በተፈጠረ ሁከት በሰዎች ሕይወት ላይ የደረሰውን ጥፋት በተመለከተ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሪፖርቱን በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል።

 

እንዲህ ዓይነቱ በገለልተኝነት መንፈስ የተሰናዳ ሪፖርት የበለጠ ተዓማኒነቱ ወደፊት እየጎለበተ እንዲሄድ ማገዝና እፀጾችም ካሉ እንዲታረሙ መጠቋቆም የአባት ነው። ከዚህ ይልቅ በጭፍን ጥላቻ ሪፖርቱን ለማጠልሸትና የተቋሙን ገለልተኝነት ለማጣጣል የሚደረገው ዘመቻ ከትዝብት በስተቀር የሚያስገኘው የፖለቲካ ትርፍ ባዶ መሆኑ ሊታወቅ በተገባ። ይልቁን ራሱ ተቃዋሚ ነኝ ባዩ አካልም ቢሆን አመለካከቱ ገንቢና ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑ በእንዲህ ዓይነቱ ጭፍን እሳቤ ጉዞው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱ ደንቃራ  መሆኑ አይቀርም።

 

መልካም አስተዳደር የሚታሰበው ሥርዓቱ ተግባሩን ለማከናወን ካለው በጎ ምልከታ አኳያ መሆኑ እርግጥ ነው። ታዲያ የአገራችን ፖለቲካዊ ሥርዓትም መልካም አስተዳደርን በሂደት ለመፈፀም ቁርጠኝነት ያለው ብቻ ሳይሆን፤ መልካምና የተመቻቸ ምህዳር ጭምርም የነገሰበት ነው። ለምን ቢባል ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ሥልጣን የህዝብና የህዝብ ብቻ መሆኑን በግልፅ አስቀምጧልና ነው። ሥልጣን የተገልጋዩ ህዝብ መሆኑ ደግሞ ለመልካም አስተዳደር እመርታ የራሱ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚካድ አይደለም። እዚህ ላይ መልካም አስተዳደር የተግባር እንጂ የንድፈ ሐሳብ ጉዳይ አለመሆኑን ልብ ልንል ይገባል።

 

የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ተግባሩ ከዜጎች የዕለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ፤ በአተገባበሩ ላይ የሥልጣኑ ባለቤት የሆነው ህዝብ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን አለበት። ህዝቡ በህገ መንግሥቱ የተጎናፀፈውን ሥልጣን በአግባቡ እንዲጠቀምበት ዕድል ይፈጥራልና። በመሆኑም የአገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ይህ ሁኔታ እንዲተገበር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ችግሮችን እየተከተታተለ በማረም ለመልካም አስተዳደር ግንባታው የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ከተቋቋሙት ገለልተኛ አካላት ውስጥ ለአብነት ያህል የሚጠቀስ መሆኑን ልብ ይሏል።

ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ይህ አካል እንዲቋቋም በአዋጅ ከማፅደቅ ጀምሮ ተግባራቱንም የመልካም አስተዳደር እመርታን በሚያረጋግጥ አኳኋን እንዲፈፅም እስከ ማድረግ ድረስ አመቺ የሆኑ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። ይህ ገለልተኛ አካል ህዝቡ በህገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡለት መሠረታዊ መብቶቹ ተግባራዊ መሆናቸውን ያረጋግጣል። እስካሁንም ድረስ በርካታ ህዝባዊ ጉዳዮችን በመመልከት የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት እየተወጣ ስለመገኘቱ ምስክር አያሻም።  

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ጉዳይ የመልካም አስተዳደር ሥራ ምሉዕ እንዲሆን በርካታ ዓመታትን የሚጠይቅ ከመሆኑና አገራችን ካለባት የማስፈፀም አቅም ውስንነት አኳያም ተያይዞ የሚታይ ነው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ያለው የመልካም አስተዳደር ትግበራ አፈፃፀም የአቅም ውስንነትን ተሻግሮ መሻሻል እያሳየ መጥቷል።

 

ይህ ማለት ግን በአገሪቱ ፈፅሞ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሉም ማለት አይደለም። ሆኖም በአስቸኳይ መፈታት ያለባቸው ችግሮች በአፋጣኝ መፍትሄ እየተሰጣቸው ነው። ሌሎችም እየታዩ በሂደት ምላሽ ያገኛሉ። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ማንኛውም የመልካም አስተዳደር ችግር በሂደት የሚስተካከልና የሚታረም መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል።   

 

ሆኖም እንደ ተቃዋሚዎቹ ሁሉንም ነገር የመደፍጠጥ አባዜ ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም በተጨባጭ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ህያው አብነቶች ናቸውና። ተቃዋሚ ተብዬዎች በተለያዩ ህጋዊ አግባቦች አለመሟላት ምክንያት ምላሽ ያልተሰጠውን አንድ ነጠላ ጉዳይ በመምዘዝ ለእነ ሂዩማን ራይትስ ዎች በማቀበልና በክቡር የሰው ልጅ ስም በሚነግዱ አክራሪ ኒዩ ሊበራሎች ነጠላ ዜማ እየታጀቡ በመጨፈር የተቋሙን መልካም የሥራ ውጤት ገደል ለመክተት ሲጥሩም ይስተዋላል።

 

ይህ ደግሞ ሀቁን ለተረዳው ህዝብ አሁንም ቢሆን እነዚህ ወገኖች ካለፈው ድርጊታቸው አለመማራቸውን የሚያረጋግጥ ነው። በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉ ተቃዋሚዎች አንዳንዴም እንኳን ቢሆን የተከናወኑ በጎ ተግባራትን ዓይናቸውን ገልጠው ቢመለከቱ መልካም ይሆናል። የተቃዋሚነት ወግና ባህል ይኸው ነውና። በመሆኑም የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ የሆነውና የሥልጣን ባለቤትነቱን ያረጋገጠው ህዝብ፤ ሥልጣኑ በእርሱ እጅ መሆኑን ዛሬም ቢሆን ነገ አምነው መቀበል ይኖርባቸዋል።

 

ከዚህም እልፍ ሲሉ እነዚህ ተቃዋሚ ነን ባዮች የመልካም አስተዳደር አስፈፃሚ የሆኑትን የሲቪል ሰርቪሱን አወቃቀርና አሠራር እንዲሁም የዳኝነት ሥርዓቱን ካለ አንዳች የነጠረ ፖሊሲና ስትራቴጂ ለመኮነን ቀዳሚ አልተገኘላቸውም።

 

በእኛ አገር እውን በሆነው ባልተማከለው ፌዴራላዊ ሥርዓት መሠረት፤ ህዝቡ የፖለቲካ መሪዎቹንና ተወካዮቹን ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ደረጃ ድረስ ይሾማል፤ ይሽራል። ህዝቡ በምርጫ ካርዱ አማካይነት በቀጥታ የሥልጣን ባለቤት የሆነበት ይህ አሠራር በሥርዓቱ ውሰጥ ወሣኝ ሚና ይኖረዋል። በህዝቡ በቀጥታ የማይመረጡና ሊመረጡ የማይችሉ አካላት መኖራቸው ደግሞ አይቀርም።

 

በዚህ የአሠራር ማዕቀፍ ውስጥ የሚጠቀሱት ሥራ አስፈፃሚው፣ ሲቪል ሰርቪሱና የዳኝነት አካላት ናቸው። እነዚህ አካላት ለመልካም አስተዳደር አተገባበር ያላቸው የማይተካ ሚና ስለሚታወቅ እንደ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር በምክር ቤቶች የሚሾሙ ወይም ለምክር ቤቶቹ ተጠሪ ይሆናሉ። ሆኖም ግን የየራሳቸው ነፃነት ያላቸው አካላት መሆናቸውን መዘንጋት አያስፈልግም። በመሆኑም ተቃዋሚዎቹ ሥራ አስፈፃሚውና ሲቪል ሰርቪሱ ማንም እንዳሻው የሚፈነጭባቸው አካላት አለመሆናቸውን ማወቅ ይኖርባቸዋል።

 

ከዚህ ይልቅ ህዝቡና የህዝቡ ተወካዮች በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መክረው ያፀደቋቸውን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ህጎች በተሟላ ሁኔታ የሚያስፈፅሙ እንዲሁም ለሁሉም ዜጋ ያለ አድልኦ ፈጣን አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ተቃዋሚዎቹ እየመረራቸውም ቢሆን መቀበል አለባቸው። ምክንያቱም እነዚህ አካላት ይህን በማድረጋቸው የህዝቡ ሉዓላዊነት መሣሪያዎች፣ አገልጋዮችና የመልካም አስተዳደር ፈፃሚዎች ከሆኑ በርካታ ዓመታትን በማስቆጠራቸው ነው።

የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓቱ የተጠቃሚው መብትና ጥቅም እንዳይሸራረፍ እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። ይህ ተግባርም መንግሥት በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መተኪያ የሌለው ድርጊት መሆኑን እንደሚያምንና በቁርጠኝነት ለመተግበርም በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀሱን የሚያመላክት ነውና።