Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቱሪዝም ገበያው !!

0 626

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የቱሪዝም ገበያው !!

                                 ይነበብ ይግለጡ

አዲስ አበባ—ላሊበላ ጎንደር–ትግራይ ባሌ ጅማ ሀረር ሰሜን ሸዋ ሌሎችም የሀገራችን ሰፊ ታሪካዊ ኃይማኖታዊ ባሕላዊ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ታሪኮች የሚገኙባቸው  ታሪካዊ ስፍራዎች ናቸው፡፡ከሚታወቁት በላይ ገና ያልተደረሰባቸው መዳረሻዎች እንደሚኖሩ መገመት ይቻላል፡፡ሲኤንኤን ቀደም ባለ ዘገባው ኢትዮጵያ እጅግ በጣም ምርጥ በሆነው የተፈጥሮ ውበትዋ አስደናቂ በሆነው የመሬት ገጽታዋና ጥንታዊ በሆነው ባሕልዋ በአውሮፓ ሕብረት የቱሪዝም መዳረሻነት ተመራጭ ሀገር መሆንዋን ዘግቦ ነበር፡፡

በባሕልና ቱሪዝም መረጃ መሰረት የጎብኝዎች ቁጥር በ10 በመቶ መጨመሩን የ3000 አመታት የአርኪዎሎጂ ታሪክ የ9 በዩኔስኮ የተመዘገቡ የአለም ቀርሶች ባለቤት የሆነች ሀገር ነች ብሎአል፡፡ዛሬ በዩኔስኮ የተመዘገቡት ቅርሶቻችን 11 ደርሰዋል፡፡ገና ማስመዝገቡን እንቀጥላለን፡፡ቱሪዝም ከብሔራዊው  ገቢ 4.5 በመቶ ሲያስገኝ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የስራ እድሎችን የከፈተና ወደ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ የአለም ባንክ ሲኤን ኤን በዘገባው አውስቶአል፡፡ዛሬ ላይ የቱሪዝም ገቢው እጥፍ አድጎአል፡፡

የትራቭል ዊክሊ ድረ ገጽ ዘጋቢ ዶሪን ሬንሽተን እንደዘገበችው የኢትዮጵያ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር በ2020 የውጭ ሀገር ጎብኚ ቱሪስቶችን ቁጥር ወደ 2.5 ሚሊዮን ለማሳደግ ወስኖ እየሰራ መሆኑን ገልጻለች፡፡ግቡ ከአፍሪካ ምርጥ ከተባሉት አምስት መዳረሻዎች ውስጥ ኢትዮጵያን አንድዋ ለማድረግ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የበለጠ የምትታወቀው በኦሞ ሸለቆ አካባቢ መሆኑን የምትገልጸው ሬንሽተን ብዙ ጎሳዎች ይገኙበታል፤ባሕላቸው ዳንሳቸው ዘፈናቸው አሁንም ከብዙ መቶ አመታት በፊት እንደነበረው ያለ ነው ትላለች፡፡በሰሜን ታሪካዊ የሆኑት የጎንደር የአክሱም የላሊበላ ቅርሶች፤በድንጋይ ላይ የታነጸው የትግራይ ቤተክርስትያን በላስታ ወሎ በአለት ላይ ተፈልፍለው በ13ኛው ክፍለዘመን በንጉስ ላሊበላ የታነጹት 11 ቤተክርስትያኖች የቱሪስት መዳረሻዎች መሆናቸውን ገልጻለች፡፡

ኢትዮጵያ የቱሪስት ኃብትዋን በሚገባ ለአለም አላስተዋወቀችም፡፡ገና ብዙ ይቀራታል፡፡ ቀደም ሲል የቱሪስት ገበያን ወደሀገሪቱ ለመሳብ የሚደረጉት የቅስቀሳና የማስተዋወቅ ዘመቻዎች የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲፈጠር ያደረጉ ነበሩ፡፡ከዚህ ጀርባም የተሳሳተ ግንዛቤ ሆን ተብሎ እንዲፈጠር ይሰሩ የነበሩ ሀገሪቱ እንዳታድግ እንዳትለማ ካላቸው የጠላትነት ስሜት በመነሳት ሲሰሩ የነበሩ ወገኖች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ኢትዮጵያ ደረቃማ በረሀማና አስተማማኝ ሰላም የሌላት ሀገር ተደርጋ ነበር የሚገለጸው፡፡

እነዚህ በውጭው አለም ሲሰራጩ የነበሩ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሊመጣ በሚችለው የቱሪስት ጎብኚ ላይ ለተወሰነ ግዜም ቢሆን ከፍተኛ አሉታዊ  ተጽእኖ በማሳደር ገበያውን አዳክመውት ኖረዋል፡፡ሆኖም ይህንኑ የተሳሳተ ወሬ ንቀው ማለፍ የቻሉ  ቱሪስቶች ወደ ሀገርቤት መጥተው ሲያዩዋት ኢትዮጵያ አረንጓዴና ለምለም አስደናቂ የመልክአ ምድር አቀማመጥ ያላት መሆኑን ማረጋገጥና መመስከር ቻሉ፡፡

የቱሪስት ገበያው በሰፊው የተከፈተው ከዚህ በኃላ ነበር፡፡የማስተዋወቁን ስራ በውጭ የሚሰሩት ከእኛ በላይ ያዩ የጎበኙ የተመለከቱ ቱሪስቶች መሆናቸው ራሱን ችሎ ትልቅ ገበያ እንዲከፈት አድርጓል፡፡አሁን የተጠናከረ ስራ እየተሰራ ያለበት ግዜ በመሆኑ ጎብኚዎች መረጃዎችን በስልኮቻቸው ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርግ አዲስ አፕሊኬሽን በስራ ላይ እንዲውል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የሚገልጹ መረጃዎች አሉ፡፡ለሀገራችን የቱሪዝም መስክ ትልቅ እድገትና እርምጃ ነው፡፡

በቱሪዝም መስክ ያለንን ሰፊ ሀብት የማስተዋወቁ ስራ ብዙ ያልተሄደበት ቢሆንም በእርግጠኝነት ተለይተው ከሚታወቁት የቱሪስት መዳረሻዎቻችን ሌላ ገና ያልተደረሰባቸው ያልተገኙ ወደፊት ሊገኙ የሚችሉ ብዙ ሀብቶች እንዳሉን ልንጠራጠር አይገባም፡፡ የሀገሪቱን የቱሪስት ሀብት በመስተዋወቅ ረገድ በጥናት ላይ የተመረኮዙ ሰፊ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውም ይታመናል፡፡

አንዱም የሀገራችንን ልማትና እድገት ማየት የማይፈልጉ ጠላቶች ሲሰሩና ሲያደርጉ የነበረው ወደ ሀገራችን የውጭ ቱሪስቶች እንዳይገቡ የተለያየ አስፈሪ ገጽታዎችን በረሀማ ሀገር ነች ሰላምና ጸጥታ የላትም የሚለውን በስፋት ሲያሰራጩ ኖረዋል፡፡ሆኖም ይህ ድርጊታቸው ባለፉት አመታት በተሰሩት ጠንካራ ስራዎች መልክና ገጽታውን ለውጦአል፡፡የሀገሪቱ የቱሪስት ገበያም እያደገ እየሰፋ ይገኛል፡፡

አምና ተፈጥሮ በነበረው የሰላም እጦት ለመጠቀም በዚህም ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ለማድረግ ብዙ ርቀት ሄደው የሞከሩ ቢሆንም አልተሳካላቸውም፡፡የሀገራችን የቱሪዝም መስክ ገና ያልተነካና ሰፊ የስራ መስኮችን ለዜጎች መፍጠር የሚያስችል ነው፡፡በባሕልና ቱሪዝም መስክ የተሰማሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠርም ላይ ይገኛሉ፡፡

የተገኘው መረጃ በ2003 ዓ.ም.ብቻ ከዛሬ 7 አመት በፊት ወደ 11ሺህ የሚጠጉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተመዘገቡ ሲሆን፣በእነዚህ ተቋማት ይሰራ የነበረው የሰው ኃይል ቁጥር 60ሺህ ገደማ የነበረ ሲሆን  በ2008ዓ.ም ማብቂያ ለ129ሺህ 819 ዜጎች የሥራ እድል የፈጠሩ 30ሺህ 649 ተቋማት መመዝገባቸው ታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም የሆቴሎች ቁጥር በ2003ዓ.ም 712 የነበረ ሲሆን ከአምስት ዓመታት በኋላ ቁጥሩ ወደ 1ሺህ 129 ከፍ ብሎአል፡፡በአምስቱ ዓመታት ውስጥ  የባለኮከብ ሆቴሎች ቁጥር ከ58 ወደ 111 አድጓል፡፡የኮከብ ደረጃ ባላቸው ሆቴሎች የሚሰሩ ባለሙያዎችም ቁጥር በ63 ነጥብ 2 አድጎአል፡፡በመረጃው መሰረት  በፋይናንስ ረገድ የባለኮከብ ሆቴሎች በ2003 ዓ.ም. የነበራቸው ካፒታል ከ80 ቢሊዮን ብር የማይበልጥ የነበረ ሲሆን ዛሬ ካፒታላቸው ወደ 101 ቢሊዮን ብር ማደጉን ያሳያል፡፡

ዘንድሮ መዲናዋን ከጎበኙ 200ሺህ 407 ቱሪስቶች 10 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ማግኘት መቻሉን የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ገልጾአል፡፡ ይህ ቁጥር በእጥፍ እንዲያድግ ገቢውም እንዲጨምር የበለጠ ስራ መስራት ይጠበቃል፡፡የተለያዩ አለምአቀፍና አሕጉር አቀፍ ተቋማት መናሀሪያ የሆነችው አዲስ አበባ የበርካታ ቱሪስቶች መናገሻ ከተማም ለመሆን በቅታለች፡፡ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉን ሰፊ የቱሪስት መስሕቦችና መዳረሻዎች  የመሰረተ ልማት ግንባታና ማስፋፊያን  ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የበለጠ ብሔራዊ ገቢ ለማስገኘት የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር እንችላለን፡፡

ዘርፉ ሰፊ የመሆኑን ያህል ልክ እንደቡና ገበያችን ሁሉ ቀጣዩ ታላቅ የብሔራዊ ገቢያችን ምንጭ መሆን የሚችለው ቱሪዝም ነው፡፡የቱሪስት መዳረሻ በሆኑት ቦታዎች በሌሎችም የተፈጥሮ መስሕብ ቦታዎች የሐይቅ ዳርቻዎች ምንጮችና ፋፋቴዎች ፓርኮች ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ንጽህናቸው የተሟሏ ዘመናዊ ሆቴሎች እንግዳ ማረፊያዎች መዝናኛ ስፋራዎችን በሰፊው መገንባት አዋጪና ከፍተኛ ብሔራዊ ገቢ ሊያስገኝ የሚችል ነው፡፡

ገና ብዙ ያልተደረሰባቸው የቱሪስት መዳረሻዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ገምቶ ጥናት በስፋት ማካሄድም ይገባል፡፡ የባሕልና ቱሪዝሙ ዘርፍ ይበልጥ ሊደገፍ ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡ ለምሳሌም ወንዶ ገነት በሙቅና ፍልውሀው በአካባቢው መንፈስ የሚሰርቅ አየር  መኖሩ በአእዋፋት ዜማው በሰፋ ሁኔታ ቢሰራበት የቱሪስቶች መዳረሻ ሊሆን የሚችል ነው፡፡የአዋሳ ሀይቅ ከውስጥ እስከ ማዶ ያለው ሰፊ እይታ በጀልባዎች እንደልብ መንቀሳቀስ መቻሉ ዙሪያው ለእይታ የሚስብ መሆኑ ሰፊ የቱሪስት ገበያ ሊስብ የሚችል መሆኑ ከብሔራዊ ገቢ እንጻርም ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡

ለቱሪዝም ገበያ የሚሆኑትን ስፍራዎች በግለሰቦች ይዞታ ስር መያዝ ያለበትንና የሌለበትን ለይቶ ማስቀመጥ የመንግስት ኃላፊነት መሆኑም መታወቅ አለበት፡፡ መንግስት በሚያገባው ገቢ ተጠቃሚው ሀገርና ሕዝብ ነው፡፡ግለሰቦች በሚያገኙት ገቢ ሊያስገቡት የሚችሉት የትርፍ ታክስና ግብር ነው መሆን የሚችለው፡፡ ግለሰቦችም ይስሩ ያስፋፉ፡፡ይህ መልካም እድልና አጋጣሚ ነው፡፡ሆኖም ግን በመንግስት ይዞታ ስር ሁነው ለሀገር በሚጠቅሙትና ከፍተኛ ገቢ በሚያስገኙት ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ ነው የሚሆነው፡፡

በትግራይ በጎንደር በወሎ በጅማ በባሌ በሐረር በወለጋ በሰሜን ሸዋ በጎጃም በአፋር  በቤኒሻኒጉል በጋምቤላ  ብዙ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑና ሊሆኑም የሚችሉ ቦታዎች ሀገራችን አላት፡፡በሙያው ዘርፍ የተሰማሩት ሰዎች ሰፊ ጥናት ሊያደርጉበት ይገባል፡፡አይደለም ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻዎች ተብለው የተለዩት ቀርቶ የኢትዮጵያ ንጹሕ አየርም በሌላው አለም የሚገኝ አይነት አይደለም፡፡

ብዝሐነታችን የተለያዩ ባሕሎች የኑሮ ዘይቤዎች እምነቶች ቋንቋዎች መኖራቸው ትልቅ የቱሪስት ገበያን ይፈጥራሉ፡፡ምድረ ቀደምት የሚለው የቱሪዝም መታወቂያችን የመጀመሪው ሰው ዘር መገኛ ሀገር መሆንዋን የሚያረጋግጥ ጥንታዊና ቀደምት መሆንዋን በውስጥዋም በሌላው አለም ውስጥ የሌሉና የማይገኙ አስደናቂ ነገሮችን አቅፋ መያዝዋን የሚያረጋጋጥ ነው፡፡

በተባበሩት መንግስታት የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ ከ11 በላይ የተለዩና የኢትዮጵያ ብቻ የሆኑ ቅርሶች የሚገኙባት ሀገር መሆንዋ ወደፊት አለም አቀፍ የቱሪስት ገበያዋ እንደሚሰፋ የበለጠ እንደሚያድግ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ካለውም በላይ መሰረተ ልማቱን ማስፋፋትና ማሳደግ ይጠይቃል፡፡

በተለይም ባለፉት አስርት ዓመታት ዘርፉ በ10 በመቶ እያደገ ሲሆን እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 የአውሮፓ የቱሪዝምና ንግድ ምክር ቤት ኢትዮጵያን ቁጥር አንድ የቱሪስት መዳረሻ ሀገር አድርጎ እንደመረጣት ይታወቃል፡፡ይሄንኑ እውነት ሲኤንኤን ዘግቦታል፡፡ተተኪው ወጣት ትውልድ የሀገሪቱን የቱሪስት ገበያ በማስፋትና በማሳደግ ረገድ ብዙ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

በደቡብ ክልል የቱሪስት መስሕብ በሆኑ ቦታዎች የቱሪስት ፍሰትና ገቢ ከሚገመተው በላይ እየጨመረ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡ቀደም ሲል የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ይህንኑ እውነት ገልጾአል፡፡ በግማሽ  በጀት ዓመቱ በታሪካዊ በተፈጥሯዊ ፣በሐይማኖታዊና ባሕላዊ መስሕቦች 740ሺ 390 ቱሪስቶች መጎብኘታቸው ያለውን የስኬት እርምጃ ያሳያል፡፡430 ሺህ የአገር ውስጥና 184 ሺህ የውጭ ቱሪስቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡,

ከአምናው ጋር ሲታይ የጎብኚዎች ቁጥር 58 በመቶ አድጎአል፡፡ በገቢ ረገድም ከቱሪስቶች 165 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ 311 ሚሊዮን 572 ሺህ 102 ብር መገኘቱ አበረታች ውጤት ነው፡፡ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ግድ ይላል፡፡በተለይም በጥምቀት ፣በመስቀልና በፍቼ ጨምበላላ በአላት የአገር ውስጥ ቱሪስቶች እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ዜጎች የራሳቸውን ሀገር የቱሪዝም ሀብትና ታሪክ ለማወቅ አዲስ ጉዞ መጀመራቸውን ያሳያል፡፡

የውጭ ሀገርን ከመጎብኘት በላይ የራስን ሀገር መጎብኘት ማወቅ መበረታታት የሚገባው መሆኑን በመግለጽ ሚዲያው ብዙ ሊሰራበት ይገባል፡፡የውጭ አገር ጎብኚዎች በብዛት ለመሳብ እንዲቻል ከባሕልና ቱሪዝም መስሪያቤት በተጨማሪ የግሉም ሆነ የመንግስት ሚዲያው ሰፊ ትኩረት ሰጥተው ሊያጎሉት ይገባል፡፡  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy