Artcles

የቻይና አጋርነት ለእድገትና ትራንስፎርሜሽን ስኬት

By Admin

May 23, 2017

የቻይና አጋርነት ለእድገትና ትራንስፎርሜሽን ስኬት

ስሜነህ

 

ሃገራችንን  መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ በመንደፍና በአግባቡ በመተግበር ባለፉት 12 ተከታታይ ዓመታት የሚያበረታታ የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብ መቻሉን መንግስትን ጨምሮ አለም አቀፍ ተቋማት የተለያዩ እና ዘርፈ ብዙ ማሳያዎች ጠቅሰው በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል።

በሁለተኛው ዙር እቅድ በግልጽ እንደተቀመጠው ሃገራችንን ወደዚህ ደረጃ ለማምጣት ልዩ ትኩረት የተሰጠው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው።በእቅዱ መሠረት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ  ከ446 ነጥብ 5 ሚሊዮን እስከ 2 ነጥብ 63 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ  ማግኘት የሚያስችል ፕሮግራም ተነድፏል፤ስትራቴጂም ተዘርግቷል ።በእቅድ  ዘመኑ መጨረሻም  ዘርፉን እስከ 23 እጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።   

 መንግሥት የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች የተቀላጠፈ የፋይናንስ፣ የጉምሩክና የሎጅስቲክ አገልግሎቶች ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ነው ። ከድጋፍና እገዛዎቹ መካከልም እንደ መለዋወጫዎች፣ አክሰሰሪዎችና ኮምፒውተሮች የመሳሰሉ መሣሪያዎች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ የማድረግና ከውጭ በሚመጡት ላይም የጥራት ፍተሻ አገልግሎት በመስጠት ፤  ከዚህም በተጨማሪ  የገበያና የምርት ግብይት ትስስር፣ የገበያ ማፈላለግ ማስተዋወቅና ማስተሳሰር እገዛዎች  ዋነኞቹ ናቸው ። 

መንግሥት ዘርፉን ለማገዝ ቀላል የማይባል እርምጃዎችን በየደረጃው ወስዷል። የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራት በማረጋገጥ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ ያላሳለሰ ጥረት አድርጓል።  በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የተለያዩ ማበረታቻዎችንም ተደርገዋል። የጉምሩክና የቀረጥ ማበረታቻ አዋጅ ወጥቶ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረጉ ስለትጋቶቹ አንደኛው ማሳያ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪነት ደግሞ ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ ኤጀንሲ አቋቁሞ የሥራ አመራር ሥርዓትን ለማስረጽ በመስራት ላይ መገኘቱም በተመሳሳይ ሊሰመርበት የሚገባው ነጥብ ነው።

 ዘርፉን ለማገዝ ከተወሰዱ ሌሎች እርምጃዎች መካከል የኢንዱስትሪ ዞንን የመከለል ተግባር ይገኝበታል። በአገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ዞን በሚመለከት የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ የማልማቱ ተግባር እየተቀላጠፈ ይገኛል። ኢንዱስትሪው በቀጣይ 13 ዓመታት ሊመራበት የሚችል ስትራቴጂ የጥናት ሰነድ በመዘጋጀት ላይ መሆኑም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል። ከሰሞኑ ደግሞ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ያካተተ የልኡካን ቡድን ወደቻይና በመሄድ ዘርፉን በተሻለ ለማሳደግ እና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ስምምነቶችን ለማድረግ መቻሉ በእርግጥም የማኑፋክቸሪንግና ለዚሁ ዘርፍ መደላድል የሚሆነው መሆኑን ማረጋገጫ ነው።

ሰሞነኛው ጉዞ ቻይና የሆነበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። አውሮፓውያንና አሜሪካውያን ከደሃ አገራት በተለይም ከአፍሪካ ጋር ያላቸው ግንኙነት እርዳታ ከመስጠትና ከመቀበል የሚመነጭ መሆኑ የመጀመሪያው ነው። አውሮፓውያንና አሜሪካ ለአስተዳደር ዘይቤያችን ላይመቹን ይችላሉ የሚሏቸውን የአፍሪካ መሪዎች በአመጽና  በመፈንቅለ መንግስት  እንዲወገዱና የራሳቸውን አሻንጉሊት መንግስታት እንደሚያስቀምጡ የሚታወቅ ሲሆን፤ እንዲህ አይነት ተግባር የቻይና አጀንዳ አለመሆናቸውም ሌላኛው ምክንያት ስለመሆኑ የፖለቲካው ዘርፍ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።

አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ከአፍሪካውያን ጋር የነበራቸው ታሪካዊ ግንኙነት የቆሸሸ በመሆኑና አውሮፓውያኑ ያንን ግንኙነት ለማስተካካልና ለማጽዳት የወሰዱዋቸው እርምጃዎች እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑም ሌላኛው ነው። በተለይ አፍሪካ ባላት የተፈጥሮ ሃብት ልማትን እንዳታመጣና የመልካም አስተዳደር ችግሮቿን በራሷ መንገድ እንዳትፈታ የአውሮፓ አገራትና ታላላቅ ኩባንያዎቻቸው ከጀርባ ሆነው የሚሰሯቸው ደባዎችም ሊጠቀስ የሚገባው ምክንያት እንደሆነ ቢያንስ ምርጫ 97ን  እና ወ/ሮ አና ጎሜዝን  የሚያስታውሱ ሁሉ አይረሱትም ።  

አፍሪካና ሌሎች ታዳጊ አገራት ራሳቸውን ለማልማት የሚያቀርቡዋቸውን እቅዶች ውድቅ ለማድረግና ብድርና እርዳታ ለመከልከል አለምዓቀፉ የገንዘብ ድርጅትና የአለም ባንክ የሚያስቀምጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምጣኔ ሃብታዊ ሳይሆኑ ፖለቲካዊና ርእዮተአለማዊ በመሆናቸው አፍሪካውያን አሁን ለደረሱበት መነቃቃት የቻይና ባንኮችና የገንዘብ ተቋማት አማራጭ ለመሆን ችለዋል። ይህንን   አማራጭ በሚገባ እየተጠቀሙ ከሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት መካከል ደግሞ ሃገራችን ቀዳሚ ስትሆን ይህም በመጀመሪያው ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ውጤት የተረጋገጠ ሲሆን ፤የሁለተኛው ዙር ሂደቱም የቀጠለው ይህንኑ ነው። በተለይ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ወሳኝ በሆኑቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ላይ የቻይና ሚና የማይናቅ እና ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን የሰሞንኛው ጉዞ መነሻ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተመራ የልዑካን ቡድን ከግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ የቻይና የተለያዩ ግዛቶችን ሲጎበኝ እንደነበር ይታወቃል።  በዚህ ጉብኝት ላይ ሃገራችን ካተረፈቻቸው የልማት ድጋፎች መካከል በአዳማ ከተማ ለሚገነባው ኢትዮ – ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚውል 260 ሚሊዮን ዶላር ከቻይና ኤግዚም ባንክ በብድር ማግኘቷ  ሊጠቀስ የሚገባው ይሆናል ።

ባንኩ ብድሩን የሰጠው የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ፒንግ በ2006 ዓ.ም ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት በተፈረሙት የሁለትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ መሰረት ነው።   ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በብድር ስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ፓርኩ የከባድ ማሽኖች፣ የኃይል ቁሳቁሶችን የሚያመርትና ለሃገሪቷ ልዩ ሊሆን የሚችል ነው።

በተለይም ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችላት ልዩ ፓርክ ከመሆኑ አንጻር ብድሩ የተለየ ትርጉም ይኖረዋል። በዚሁ ላይ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት፣ የሃይል ማመንጨትና ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ፣ በማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ልማትና የቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግርን ከመፍጠር አኳያ አስደናቂ ስራ እያከናወኑ መሆኑም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የእቅድ ዘመኑ የተሳካ እንደሚሆን ከወዲሁ ለመገመት ያስችላል።

በዚህ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ ከሁናን ግዛት በዘመናዊ ግብርና፣ የኢንዱስትሪ ሽግግር እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ልምድ ትቀስማለች።የቻይናዋ ሁናን ግዛት ‹በቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሺዬቲቭ› አማካኝነት በአለም አቀፍ ቀላልና ዘመናዊ የትራንስፖርት ስርዓት ዘጠኝ ፓርኮችንና 11 ቢሮዎችን ትከፍታለች።

የሁናን ግዛት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የተለያዩ ማበረታቻዎች የቀረቡላቸው ሲሆን፤ እኤአ 2016 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች የ180 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ማካሄዳቸውም ጥያቄውን ተቀብለው እንደሚመጡና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሃገራት ተርታ ለመሰለፍ የሚደረገውን ጉዞ እንደሚያሳልጡ ከወዲሁ ለመገመት የሚያስችል ይሆናል።

ይህን ከመሰለው የቻይና ድጋፍ ባሻገር ሃገራችን የመንግስታቱ ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ዋነኛ መሳሪያዎች አድርጋ መውሰዷም የእቅዱን ስኬት የበለጠ ያፈጥነዋል።የሁለተኛው ዙር እቅድ ድህነትንና ረሃብን ማጥፋት፣ ጤናማ ህብረተሰብ መፍጠር፣ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ማረጋገጥ እንዲሁም የመሰረተ ልማት ግንባታና የውሃ ስነ-ምህዳርን መጠበቅ የሚሉትን የድርጅቱን ግቦች መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ስለሆነ በተለይ የልማት ግቦቹ በመላ አገሪቱ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋትና የክልሎችን የወጪ ንግድ ሚና በማሳደግ ረገድ ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑና ዕቅዱ ወጣቶችን በማብቃት፣ ስራ ፈጠራን በማገዝና ወደ ስራ በማሰማራት ላይ ትኩረት ያደረገም ነው።

በሁለተኛው ዙር እቅድ ዘመን ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከነበረበት የ4 ነጥብ 9 በመቶ ወደ 5 ነጥብ 4 በመቶ እንዲሁም የኮንስትራክሽን ዘርፉም ከ8 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 9 ነጥብ 5 በመቶ ማደጉ ለተመዘገበው ሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የጎላ ድርሻ የሚይዝ ይሆናል ። የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢም ከ691 የአሜሪካን ዶላር ወደ 794 ዶላር ከፍ ማለቱም  ሂደቱ የተሳካ መሆኑን ያሳያል ።በጤናው ዘርፍ የእናቶችን ሞት በመቀነስ፤ በትምህርት ዘርፉም በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ፣ በመሰናዶና  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ተሳትፎ የተከናወኑት ስራዎች ስኬቱን ከወዲሁ የሚያጠይቁ ሲሆን፤በአንፃሩ በኤክስፖርት ሴክተርና ከሀገር ውስጥ ምርት አኳያ የታክስ አሰባሰብ ክንውን ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ አፈጻጸም ታይቷልና ሊታሰብበት ይገባል።