Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የችጋርን ዘመን ተሻግረናል

0 437

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የችጋርን ዘመን ተሻግረናል

ኢብሳ ነመራ

በያዘነው ዓመት ክረምት ዓለም አቀፍ የኤል ኒኖ ክስተት ሊያጋጥም እንደሚችል ተገምቷል። በተለይ የአሜሪካ ብሄራዊ የውቅያኖስና ከባቢአየር አስተዳደር የአየር ንብረት ትንበያ ማዕከል ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ከአንድ ወር በኋላ በሚገባው ክረምት ወይም ከዚያ ወዲህ የኤል ኒኖ ክስተት ሊያጋጥም እንደሚችል በምድር ወገብ የፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ ያለ የላይኛው የውቅያኖስ ውሃ ሙቀት እንደሚያመለክት አስታውቋል። ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶች በምስራቃዊ የምድር ወገብ የፓስፊክ ውቅያኖስ አካባቢ ከአማካይ በላይ የሆነ ሙቀት ቢኖርም፣ የውቅያኖስ ውሃ ሙቀት የቅርብ ግዜ ምርመራ ውጤት፣ አሁን የሚገኝበት ሁኔታና ትንበያ ኤል ኒኖ የሚከሰት መሆኑን አያመለክትም የሚል ግምት አስቀምጠዋል። ያም ሆነ ይህ የዘንድሮ የኤል ኒኖ የመከሰት እድል 50 በመቶ መሆኑ ላይ ስምምነት ያለ ይመስላል።

ኤል ኒኖ በምድር ወገብ ምስራቃዊ የፓስፊክ ውቅያኖስ ወለል (እስከ 200 ሜትር ጥልቀት) ላይ በሚፈጠር ከአማካይ በላይ የሆነ መሞቅ የሚከሰት የአየር ንብረት መዛባት ነው። ይህ የውቅያኖስ ውሃ ሙቀት መጨመር የተለመደውን የአየር ግፊት ሁኔታ በማዛባት የንፋስ አቅጣጫን ያዘበራርቃል። የተወሰኑ አካባቢዎች በወቅቱ መደበኛ ዝናብ ሳያገኙ ይቀሩና በድርቅ የመታሉ፤ መደበኛ ባልሆነ ወቅት ደግሞ ከፍተኛ ዝናብ ያገኛሉ። ሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ከመጠን ባለፈ ዝናብ፣ ከውቅያኖስ በሚነሳ አውሎ ንፋስ፣ ከመጠን ያለፈ ቅዝቃዜ…ወዘተ ይመታሉ። ኤል ኒኖ የሚያስከትለው የአየር መዛባት በአጭሩ ይህን ይመስላል።

የኤልኒኖ ክስተት ምክንያት እስካሁን ይህ ነው ተብሎ በውል አይታወቅም። የኤል ኒኖ ክስተት ተፈጥሯዊ ነው። ኤል ኒኖ የሚከሰትበትን ድግግሞሽ በተመለከተ ያሉ መረጃዎች የተለያዩ ናቸው። ከሶስት እስከ አምስት አመት ባለው ልዩነት ይከሰታል የሚለው ግን በአመዛኙ ተቀባይነት ያገኘ ይመስላኛል። ከሁለት እስከ ሰባት ዓመት ባለው ጊዜ የከሰታል የሚል መረጃም አለ። ያም ሆነ ይህ ኤል ኒኖ ሲያጋጥም የኖረ ለወደፊትም የሚያጋጥም የአየር ንብረት መዛባት የሚያስከትል ክስተት ነው። አንዳንድ መረጃዎች በሰው ሰራሽ ምክንያት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ ሙቀት አማቂ ጋሶች (greenhouse gases) ምክንያት የአየር ሙቀት መጨመር የኤ ኒኖን ክስተት ድግገሞሽ እንደጨመረውና ሊጨምረው እንደሚችል ያመለክታሉ። ከዚህ አኳያ ሲታይ የኤል ኒኖን ድግግሞሽና የአስከፊነት ደረጃ ለመቀነስ  ሰው ሰራሽ የሙቀት አማቂ ጋስ ልቀትን መቆጣጠር አስፈላጊ ይሆናል። እናም መንግስታት የደረሱበትን የአየር ንብረት ስምምነት ተግባራዊ  ማድረግ አስፈላጊ ነው። ይህን ስምምነት ችላ ማለት ኤል ኒኖን በየዓመቱ ወደ ሚያጋጥም የተለመደ ክስተትነት የሚለወጥበትን ሁኔታ እንዳያስከትል ያሰጋል። ይህ ሁኔታ በተለይ የክስተቱ አሉታዊ ተጽእኖዎች ተጋላጭ ለሆኑ በማደግ ላይ ለሚገኙ ሃገራት ትልቅ ስጋት ነው። ኢትዮጵያ በኤል ኒኖ የድርቅ ተጽእኖ የምትጠቃ ሃገር በመሆኗ በተለይ  ክስተቱን በሚያፋጥኑ ሰው ሰራሽ ሁኔታዎች ስጋት ላይ ከሚወድቁ ሃገራት ቀዳሚዋ ናት።

ኢትዮጵያ ኤል ኒኖ በሚስከትለው የአየር መዛባት ተጽእኖ በድርቅ ስትመታ የኖረች ሃገር ነች። ከሰላሳ ዓመታት ቀደም ሲል ያጋጠሙት አብዛኞቹ ድርቆች በየአስር ዓመት ልዩነት ያጋጠሙ ቢሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ድግግሞሹ ከዚያም በታሽ ወደ ሆኑ ዓመታት የተቀየረበት ሁኔታ ይታያል። ባለፉ ሃያ አምስት አመታት የነበረውን ሁኔታ እንኳን ስንመለከት በ1985/86፣ 1993/94፣ 2002/2003፣ 2007/2008 እና ዘንድሮ 2009 ዓ/ም ኤል ኒኖ የፈጠራቸው የድርቅ ተጽእኖዎች አጋጥመዋል።

እስካሁን ባለው ሁኔታ መንስኤው ይህ ነው ተብሎ በውል ያልተለየውና ማስቀረትም ያልተቻለው ኤል ኒኖ ኢትዮጵያ ላይ ያስከተላቸው ድርቆች በተለይ ከ30 ዓመታት በፊት የአስከፊ ችጋር ወይም ቸነፈር (famine) መንስኤዎች ሆነው ቆይተዋል። ድርቅ በምግ እጦት ለህይወት መጥፋት፣ ለወረረሽኝ፣ ለስደት ወዘተ መክንያት ሲሆን ይህ ሁኔታ ችጋር ወይም ቸነፈር (famine) ይባላል። ታዲያ ኢትዮጵያ በችጋር ስትመታ ነው የኖረችው። በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ያጋጠመን ዓለም የሚያውቀውን በ1965/66 እና 1976/77 ዓ/ም የተከሰተውን ችጋር ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። የ1965/66 ድርቅ ተጽእኖ ዜና ጎልቶ የወጣው በተለይ በሰሜን አትዮጵያ ወሎ፣ ትግራይ እና በምስራቅ ኢትዮጵያ ኦጋዴን አካባቢ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ የሃገሪቱ ቆላማ የጠረፍ አካባቢዎች በድርቁ ተጽእኖ ስር ወድቀው ነበር። የዚህ ድርቅ ዜና በተወራባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ብቻ ባስከተለው ችጋር ከ3 መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል። በተቀረው አካባቢ ያለቀውን ሃገሬው ብቻ ነው የሚያውቀው።

ይህ ድርቅ ለሰዎች ህይወት መጥፋት፣ ወረርሽኝ መከሰትና ስደት ምክንያት ወደሆነ ችጋርነት የተቀየረው በወቅቱ የነበረው ዘውዳዊ መንግስት ለችግሩ ትኩረት በመንፈጉና እንዲያውም ለመደበቅ በመሞከሩ ነው። በወቅቱ አዲስ አበባ ጎተራ በሚገኘው የሃገር ውስጥ መጠባበቂያ የእህል ክምችት ያለውን ያህል ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ቀርቦ ቢሆን ኖሮ፣ እንዲሁም ችግሩ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለጋሾች ይፋ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ችጋሩን ተከላክሎ የሰውን ህይወት ማትረፍ ይቻል ነበር።

ከዚህ በኋላ በተመሳሳይ የኤል ኒኖ ክስተት ሳቢያ በ1976/77 በኢትዮጵያ ድርቅ ተከስቷል። ይህም ድርቅ ልክ እንደ 1965/66 ሁሉ ችጋር አስከትሏል። የ1976/77 ድርቅና ያስከተለው ችጋር መጠን ከ1965/66 የከፋ ነበር። በዚህ የድርቅ ችጋር ከ1 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን አጥተዋል።

የ1976/77 ድርቅ ወደ ችጋርነት የተለወጠው በተመሳሳይ የመንግስት ችልተኝነት ነበር። በወቀቱ ሃገሪቱን ሲያስተዳደር የነበረው ወታደራዊ መንግስት ለድርቁና ላስከተለው የምግብ እጥረት ተጽእኖ ትኩረት ነፍጓል። በወቅቱ ስርአቱ የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመትና የስርአቱ ገዢዎች ወታደራዊ መለዮአቸውን አውልቀው ወደሰራተኛ መደብነት ተቀይረው የስርአቱ ብቸኛ ገዢ የሆነውን የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) በመመስረት ስራ ተጠምደው ስለነበረ ድርቁንና ያስከተለውን ተጽእኖ ከቁብ አልቆጠሩትም። ታዲያ ወታደራዊ ገዢዎቹ ብዙ ሚሊየን ዶላር አፍስሰው የኢሠፓ ምስረታ ይፋ የተደረገበትንና 10ኛ ዓመት የድል በአላቸውን አክብረው ከጨረሱ በኋላ ነበር ፊታቸውን ወደድርቁ የመለሱት። ያኔ ግን ድርቁ ያስከተለው ችጋር የሚሊየኖችን ህይወት ቀጥፎ ነበር።

እነዚህ ሁኔታዎች በኤል ኒኖ ሳቢያ የሚያጋጥመውን ድርቅ መከላከል ባይቻልም፣ ሊያስከትል የሚችለውን ችጋር ግን ትኩረት ከተሰጠው  መከላከል እንደሚቻል ያሳያሉ።

ድርቅ ከዚያም በኋላ ኢትዮጵያን አልለቀቃትም። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ በወታደራዊው ደርግ ሥርአት ውድቀት ማግስት በ1985/86፣ በ1992/93፣ በ2002/03፣ በ2007/8፣ በ2009 ተከስቷል። ከሃያ አምስት ዓመታት ወዲህ የተከሰቱትን ድርቆች ልዩ የሚያደርጋቸው ያስከተሉት የምግብ እጥረት ተጽእኖ ወደችጋርነት ሳይለወጥ መከላከል በመቻሉ ነው።  ከሃያ አምስት ዓመታት ወዲህ የተከሰቱት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ድርቆች (1985/86 እና 1992/93) ሲያጋጥሙ ሃገሪቱ በፍጥነት የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ማቅረብ የሚያስችል በቂ የመጠባበቂያ የእህል ክምችት ባይኖራትም፣ ድርቁ ያስከተለው የምግብ እጥረት ሳይበረታ የውጭ እርዳታ እንዲደርስ በማድረግ ተጽእኖውን መከላከል ተችሏል። በተለይ በ1992/93 የተከሰተው ድርቅ ወደ 14 ሚሊየን ህዝብ ነበር ለምግብ እጥረት የተጋለጠው።

ከ2002/3 በኋላ ያጋጠሙ ድርቆች ግን የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በተለይ የግብርናው ዘርፍ በፍጥነት እያደገ በነበረበት ወቅት የተከሰቱ በመሆናቸው፣ የምግብ እጥረት ተጽእኖ ማስከተላቸው እንደታወቀ ሁኔታውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቁ ስራ እንደተጠበቀ ሆኑ፣ የውጭ እርዳታ ሳይጠበቅ ከመጠባበቂያ የእህል ክምችት እርዳታ ማቅረብ የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በአጠቃላይ 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎችን ለምግብ እጥረት ተፅዕኖ ያጋለጠው የ2007/8 ድርቅ በተከሰተበት ወቅት መንግስት 450 ሺህ ሜትሪክ ቶን የመጠባበቂያ የእህል ክምችት ነበረው።

ከዚያም በኋላ መንግስት 16 ቢሊየን ብር መድቦ የምግብ ሰብል ከውጭ በመግዛት በራስ አቅም የርዳታ ማቅረብ ተግባር አከናወኗል። ይህን የድርቅ ተጽእኖ በመቋቋም ረገድ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ጊዜዎች መንግስት የአንበሳውን ድርሻ መያዙ ይታወቃል። በዚህ ሁኔታ ድርቁ ለአንድም ሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ሳይሆን፣ ሰዎች ከቂዬአቸው ሳይፈናቀሉ፣ ልጆች ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ መቋቋም ተችሏል።

የ2007/8 ድርቅ ወደ 2009ም ተሻግሯል። የ2009 ዓ/ም ድርቅ በተለይ በደቡብና ደቡብ ምስራቅ ቆላማ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተ ነው። በደቡብና ምስራቅ የኦሮሚያ አካባቢዎች፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በደቡብ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ደቡባዊ ቆላማ አካባቢ በአርብቶ አደርነት የሚኖሩ ዜጎች ናቸው በድርቁ የተጠቁት። በዚህ የድርቅ ተጽእኖ ስር የወደቁት ዜጎች ቁጥር 5 ነጥብ 6 ሚሊየን የነበረ ሲሆን አሁን ወደ 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ጨምሯል። የ2009ን የድርቅ ተጽእኖ ልዩ የሚያደርገው በተጽእኖ ሥር የወደቁት የሃገሪቱ አካባቢዎች የአርብቶ አደሮች መኖሪያ  በመሆናቸው ነው። ይህ ሁኔታ የአርብቶ አደሩ የኑሮ መሰረት የሆኑ እንስሳትም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እድርሷል። በዚህ ምክንያት የእርዳታ አሰጣጡ የእንስሳትን ህይወት ማትረፍንም የሚመለከት እንዲሆን አደርጓል። ይህ ድግሞ የእርዳታ አሰጣጡን አወሳስቦታል።

የድርቁን ተጽእኖ ለመከላከል መንግስት የ1 ቢሊየን ብር ባጀት መድቦ እርዳታ ያቀረበ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ የክልል መንግስታት፣ ባለሃብቶችና ዜጎችም የእርዳታ አቅርቦቱን እየደገፉ ይገኛሉ። በዚህ ሳቢያ እስካሁን ድርቁ ወደችጋርነት አልተለወጠም። አሁን ያለው አጠቃላይ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ድርቁ ቀጣይነት ቢኖረውንም ወደችጋርነት ሊለወጥ የሚችልበት እድል እንደማይኖር ያመለክታል።

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሰሞኑን እንዳስታወቀው በሀገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የዕለት ደራሽ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተረጅዎች የሚውል በቂ የእርዳታ እህል ክምችት አለ። ኮሚሽኑ እስከ ሰኔ ወር ድረስ ለተረጅዎች የሚውል 432 ሺህ 515 ሜትሪክ ቶን እህል ዝግጁ መሆኑን አሰታውቋል። አሁን በየወሩ በቤተሰብ አባላት ቁጥር  ልክ እየቀረበ ያለው የድጋፍ መጠንም ሳይቆራረጥ መቀጠሉን አስታውቋል።

በ2007 እና 2008 የተረጅዎች ቁጥር ሲጨምር ለህጻናትና ለእናቶች የሚቀርበው የአልሚ ምግብ እጥረት አጋጥሞ እንደነበረ ያስታወሰው ኮሚሽኑ፣ ዘንድሮ የዓልሚ ምግብ ተረጅዎች በሚፈልጉት ልክ እየቀረበ መሆኑን አስታውቋል። በአርብቶ አደር አካባቢዎች አርብቶ አደሩ ጥሪቱን እንዳያጣ የእንስሳትን ዝርያ የማቆየት ስራም እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።

ቀደም ሲል እንደተገለጸው የዘንድሮው ድርቅ በአርብቶ አደር አካባቢ  እንስሳ ላይ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ልዩ ያደርገዋል። አርብቶ አደሩ ላሉት ሁሉም ከብቶች የሚበቃ መኖ ማቅረብ አይቻልም። በሃገሪቱ የእንስሳ መኖ ራሱን ችሎ የማይመረት መሆኑና የመጠባበቂያ የመኖ ከምችትም የማይያዝ መሆኑ ከፍተኛ የመኖ እጥረት ፈጥራል። ከዚህ በተጨማሪ ከየአካባቢው የተቃረመውንም ቢሆን  በሺህ ኪሎ ሜተሮች አጓጉዞ ማቅረብ እጅግ ውድ ነው። በዚህ ምክንያት በርካታ እንስሳት ሞተዋል። ምናልባት አሁን እየጣለ ያለው ዝናብ የተረፉት ከብቶች እንዲያገግሙ ማገዝ እንደሚችል ቢገመትም፣ በእንስሳ ላይ የደረሰው ጉዳት ግን ከፍተኛ ነው። መንግስት ይህን ሁኔታ ችላ ብሎታል ማለት እንዳልሆነ ግን መታወቅ አለበት። የእንስሳቱ መሞት በአርብቶ አደሩ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ለተወሰኑ የዘር ከብቶች መኖ የማቅረቡ ስራ እንደተጠበቀ ሆኑ መንግስት እንስሳቱን በመግዛት ስጋውን በቋንጣ መልክ በማዘጋጀት በእርዳታ መልክ መልሶ ለአርብቶ አደሩ እያቀረበ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ ከድርቁ በኋላ ለመልሶ ማቋቋም የሚውል እንዲሁም የእንስሳ ዝርያን ለመጠበቅ ዓላማ የሚውል በርካታ እንስሳት በማቆያ እንዲያዙ ተደርጓል።

እንስሳ የኢኮኖሚ እሴት ያለው ሃብት ነው። በመሆኑም ለእንስሳ የሚደረግ እርዳታ ከኢኮኖሚ ዋጋው የሚበልጥ ሊሆን አይችልም። የአንድን ላም ህይወት ለማትረፍ የመቶ ሺህ ብር ወጪ አይደረግም። የእንስሳትን ህይወት የማዳን ወጪ ኢኮኖሚያዊ ዋጋውን ታሳቢ ያደረገ ነው። በመሆኑም አርብቶ አደሩ እንዳይጎዳ ለእንስሳ የሚደረገው እርዳታ ያለገደብ እንዲቀጥል ማድረግ አይቻልም።

በዚህ ምክንያት የድርቁ ጊዜ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ መልሶ ለእርዳታ ለማዋል ወዘተ ተሽጠው አርሶ አደሩ በእንስሳው ፋንታ ገንዘብ ይዞ እንዲቆይ ከማድረግ ያለፈ አዋጭ ተግባር ማከናወን አዳጋች ነው። ለዘር እንዲተርፉ በአርብቶ አደሩ እጅ ለሚገኙ ጥቂት እንስሳትና በማቆያ ከተያዙ እንስሳት ያለፈ ለሁሉም እንስሳ መኖ ማቀረብ አይቻልም፤ መኖው ኖሮ ቢቻል እንኳን አዋጭ አይደለም። በዚሀ ምክንያት የሚሞቱን እንስሳ ቁጥር በርካታ ሊሆንና የድርቁ ተጽእኖ እስካለ ድረስ ሊቀጥል ይችላል። ከዚህ ባለፈ የሰውን ህይወት የማተረፉ ጉዳይ ግን በማንኛውም ሁኔታ ተጠናክሮ የሚቀጥል የሆናል። የዘንድሮው ድርቅ በዚህ ማእቀፍ ውስጥ መታየት አለበት።

እንግዲህ ድርቅን ማስቀረት አልተቻለም። በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው ዘንድሮም ኤል ኒኖ ድርቅ ይዞ ሊመጣ ይችላል። ይህ ሁኔታ ለወደፊትም ይቀጥላል። በመሆኑም ድርቅ ሲከሰት ተጽእኖውን ለመከላከል ከሚደረገው የዘመቻ ርብርብ ውጭ ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል። ዘላቂ መፍትሄው በቅድሚያ ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ግብርና እንዲኖር ማድረግ ነው። ይህም የመስኖ ግብርናን ማስፋፋት ይጠይቃል። ከዚህ ባሻገር በአጠቃላይ ኢኮኖሚውን ከግብርና ጥገኝነት ማላቀቅ የሚያስችል መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣትን የሚመለከት ነው። እነዚህ ጉዳዮች ራሳቸውን የቻሉ ሰፊ አጀንዳዎች በመሆናቸው እንደአመቺነቱ በሌላ ጽሁፍ እመለስባቸዋለሁ። እስካሁን ያለው የድርቅን ተጽእኖ ለመከላከል የተወሰዱና በመወሰድ ላይ ያሉ እርምጃዎች ግን ድርቅ ችጋር የሚያስከትልበትን ዘመን የተሻገርን መሆኑን ያመለክታሉ።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy