NEWS

የአውሮፓ ህብረት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ልማት የሚውል 59 ሚሊየን ዩሮ አጸደቀ

By Admin

May 03, 2017

የአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ለማጠናከር ፣ህገወጥ ስደትን ለመግታት እና መፈናቀልን ለመቀነስ የሚያግዘው 59 ሚሊየን ዮሮ መመደቡን አስታውቋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት በላከው መግለጫ ፥ ህብረቱ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የመደበው ገንዘብ ለሁሉም የቀጠናው ሀገራት ሰላም እና ልማት ፕሮጅክቶች የሚውል እንደሆነ ገልጿል፡፡

የገንዘብ ድጋፉ በቀጠናው የሰላም ግንባታ፣የጸጥታና የመረጋጋት ስራዎችን ማጠናከር ብሎም ኢኮኖሚያዊ ትስስር እና ልማትን ማሻሻልን ያለመ ነው፡፡

ከተጠቀሰው ገንዘብ ውስጥ 40 ሚሊየን  ዩሮ ለምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ እና ለቀጠናው ሀገራት ሰላምን ለማስፈን ለሚረዱ ቁልፍ ተግባራት የሚውል መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የኬኒያ ብሄራዊ ጸረ- ሽብር እንቅስቃሴ ስትራቴጂ ለመደገፍ በህብረቱ እና የኬኒያ ትብብር ማዕቀፍ 5 ሚሊየን ዩሮ ይውላል ተብሏል፡፡

ለሰሜናዊ ደርፉር 10 ሚሊየን ዩሮ የተመደበ ሲሆን ፥በዚህ ገንዘብ 80ሺህ አነስተኛ አምራቾች በቀጥታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ እና ወደ 700 ሺህ ሰዎች በተዘዋዋሪ የሚደግፍ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እና ልማት በመፍጠር የሰዎች ስደትን ለመከላከል ብርቱ እገዛ እንደሚኖረው ተዘግቧል፡፡

አብዛኛው ገንዘብ የሚውለው ለስራ ፈጠራ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት በተለይ ወጣቶችን እና ሴቶችን የሙያ ስልጠናዎች በመስጠት የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲጠናከሩ ይሆናል፡፡

ምንጭ፦አውሮፓ ህብረት