NEWS

የአፍረን ቀሎ ማህበረሰብ የገዳ ስርዓት ዳግም ተቋቋመ

By Admin

May 14, 2017

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የአፍረን ቀሎ ማህበረሰብ የገዳ ስርዓት ዳግም ተቋቋመ።

በሐረር ከተማ ትናንት በተከናወነው በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ እንደተገለጸው  የገዳ ስርዓት የዴሞክራሲ  ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

ጥልቅና ሰፊ ሐሳብን ይዞ በኦሮሞ ህዝብ የመነጨው የገዳ ስርዓት ለበርካታ መቶ ዓመታት የማህበረሰቡ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ አቅጣጫ ጠቋሚ ሆኖ አገልግሏል።

ሆኖም በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ በአገሪቱ በተፈጠሩ ወረራዎች የተነሳ ስርዓቱ ከቦረናና ጉጂ በስተቀር ጸንቶ መቆየት አልቻለም ነበር።

ለመቶ ዓመታት ተዘንግቶ በቆየባት ምስራቅ ሐረርጌ ዞን የአፍረን ቀሎ ማህበረሰብ ውስጥ ስርዓቱ ዳግም እንዲቋቋም ተደርጓል።

በኦሮሚያ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳይ ኃላፊ ወይዘሮ አልፍያ ሐጂ ዩስፍ እንዳሉት  የገዳ ስርዓት በሀገሪቱ  በነበረው  የፖለቲካ መዛባት የተነሳ ከቦረናና ጉጂ ጎሳዎች በስተቀር በሌሎች አካባቢ ተዘንግቶ ቆይቷል።

በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ እየታወሰ የሚገኘውን የገዳ ስርዓት ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ለማስፋፋት የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ኦሮሞዎችን የሚወክል አፍረን ቀሎ የሚል መጠሪያ የተሰጠውን የገዳ ስርዓት መቋቋሙን ነው ያስረዱት።

የድሬዳዋ ባህል ቡድን አባል አባ ቦኮ አብዱልአዚዝ ሱፍያን በበኩላቸው  ከዚህ ቀደም ተበታትነው ይኖሩ የነበሩ ጎሳዎች በአንድ ስርዓት ስር መሰባሰባቸው ለአካባቢው ልማትና እድገት የሚያበረክተው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም በአካባቢው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር የአባ ገዳ ስርዓቱ መቋቋም የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የገዳ ስርዓት በዞኑ መመስረት በአካባቢው ላይ የሚታዩ ግጭቶችን በማስወገድ ቀጣይና ዘላቂነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ  እንዳለው የገለጹት ደግሞ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው፡፡

የአካባቢው ነዋሪ  አቶ ናስር መሀመድ በሰጡት አስተያየት ተዘንግቶ  የቆየው የገዳ ባህላዊ ስርዓት ዳግም መቋቋሙ መደሰታቸውን ገልጸው ለዚህም አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በዕለቱም  የአፍረን ቀሎና ሁምበና የአባ ገዳዎች ሰብሳቢ አበገዳ ሙሳ አሊ የተመረጡ ሲሆን የአባ ገዳ ምክር ቤትም ተመስርቷል።

በኦሮሚያ ሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ አባ ገዳዎች በተገኙበት የምረቃ ስነ ስርዓት በቅርቡም እንደሚካሄድም ተመልክቷል።

የአፍረን ቀሎ ማህበረሰብ የገዳ ስርዓት ዳግም በተቋቋመበት ስነስርዓት ላይ  የሀገር ሽማግሌዎች፣  የሐይማኖት አባቶች፣  አባ ቦኩዎችና የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የገዳ ስርዓትበተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት ፣የሳይንስና  የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ  ቅርስነት  በተያዘው ዓመት መመዝገቡ ይታወሳል።