Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢትዮጵያና የአፍሪካው ተወካይ በመጨረሻዎቹ ሰዓቶች

0 315

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያና የአፍሪካው ተወካይ በመጨረሻዎቹ ሰዓቶች

                                                           ዘአማን በላይ

ዶክተር ቴዎድሮስ ኣድሃኖም ገብረየስ። የቀድሞው የሀገራችን የጤና ጥበቃና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር። ሰዎች እንደ እኔ በአካል አግኝተዋቸው ባያውቁም ለኢትዮጵያ ባበረከቱት በጎ አስተዋፅኦ የሚዘነጓቸው አይመስለኝም። አዎ! እኔም ዶክተሩን ሁሌም ሳስታውሳቸው ለዚህች ሀገር ያከናወኑት ተግባር ይገዝፍብኛል። በኢህአዴግ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት የቀየሳቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በብቃትና በክህሎት በማስፈፀም እንዲሁም እርሳቸው በተመደቡበት አመራር ሀገራችን ተጠቃሚ እንድትሆን የላቀ ሚና የተጫወቱ ምሁር ኢትዮጵያዊ ናቸው።

እኚህ ምሁር ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ጄኔራል ዳይሬክተርነት ተወዳድረው የተለያዩ ምርጫዎችን በማለፍ በአሁኑ ወቅት ለመጨረሻ ውድድር ከቀሩት ሶስት ዕጩዎች ውስጥ አንዱ መሆን ችለዋል። እስካሁን የተገኙት ድጋፎች እንደሚያመለክቱት ከሶስቱ ዕጩዎች ውስጥ የሀገራችንና የአፍሪካ ወኪል የሆኑት ዶክተር ቴዎድሮስ የአሸናፊነት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል። ይህን ፅሑፍ እስካጠናቀርኩበት ድረስ የመጨረሻው የምርጫ ውድድር ሁለት ቀናቶች ብቻ ይቀሩታል። ታዲያ በእነዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ህብረት ተወካይ እንዲሁም የቻይና፣ የብራዚል እና የቬንዙዌላ መንግስታት ድጋፋቸውን እንደሰጡ ተመልክተናል። ቀደም ባሉት ጊዜያትም ሁሉም የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገሮችና እንዲሁም የኢትዮጵያና የአፍሪካ ወዳጆች ለዶክተሩ ድጋፋቸውን ችረዋል።

ርግጥ ዶክተር ቴዎድሮስን ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ ብሎም እስከ ኤሺያና ላቲን አሜሪካ ድረስ ያሉ የተለያዩ ሀገራት የሚደግፏቸው ከምንም ተነስተው አይደለም— ዶክተሩ እዚህ ሀገር ውስጥ የሰሩትን ስኬታማ ተግባሮች ጠንቅቀው ስለሚያውቁ እንጂ። እንደሚታወቀው የማንኛውም ተቋም ስኬትም ይሁን ውድቀት በሰራተኛውና በመሪው ጫንቃ ላይ የወደቀ ነው። ሰራተኛው ምንም ያህል ትጉህ ቢሆን በአግባቡ አስተባብሮ እንዲሁም የራሱን ዕውቀትና ክህሎት አክሎ የሚመራ ከሌለው አውራ እንደሌለው ንብ ይቆጠራል። በአንፃሩም መሪው ምንም ያህል ትጉህና በዕውቀት የካበተ ቢሆን፣ ሰራተኛው ተቋሙን እንደ ራሱ ቤት የማይቆጥር፣ ባለበት ተቋም ውስጥ የመንግስትን ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ለማስፈፀም ፍላጎት ከሌለው የመሪው ጥረት ከንቱ መሆኑ አይቀርም። በአንድ እጅ ማጨብጨብ ዓይነት ይሆናል። እናም “ጠንካራ መሪ ጠንካራ ተመሪን ይፈጥራል” እንደሚባለው፤ የአንድ ተቋም ውጤታማነት በአመዛኙ በመሪው ትከሻ ላይ የወደቀ ነው ማለት ይቻላል።

ከዚህ አኳያ ዶክተር ቴዎድሮስ ይመሩት በነበረው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ስር የነበሩትን ሰራተኞች በማስተባበርና በመምራት ሀገሪቱ የነደፈችውን የጤና ፖሊሲ እንዲሁም የመንግስታቱ ድርጅት በወቅቱ አውጥቶት የነበረውን የሚሊየሙን የልማት ግቦች በማሳካት ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። በተለይም በሀገራችን ውስጥ በገዳይነት የሚታወቀውን ወባን በ70 በመቶ እንዲሁም የእናቶችና ህፃናት ሞት እንዲቀንስና ኤች.አ.ቪ/ኤድስን በመዋጋት ትርጉም ያለው ለውጥ አምጥተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በየአንዳንዱ ቀበሌ ውስጥ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን በማሳለጥ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንዲሁም የጤና ኬላዎች በገጠርና በከተማ እንዲስፋፉ በማድረግና ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ መሪ ናቸው። በእኔ እምነት ለዶክተር ቴዎድሮስ የድጋፍ ድምፃቸውን እየሰጡ ያሉት የተለያዩ ሀገራት ዶክተሩ እነዚህን የኢትዮጵያና የአፍሪካን ችግሮች በጥቂት ዓመታት ውስጥ መፍታት እንደቻሉ ስለሚገነዘቡ ነው። ዶክተሩ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ሀገራት እያገኙ ያሉት ከፍተኛ ድጋፍ፤ ጥሩ ስራ ሁሌም ተመራጭ የሚያደርግ መሆኑን አመላካች ነው። ለዚህም ነው—የኢትዮጵያና የአፍሪካ ወኪል ሆነው በመቀስቀስ ላይ ሳሉ “You Know ‘WHO’ I AM” በማለት አንድም ራሳቸውን በማስተዋወቅ፣ ሁለትም ‘ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት እኔን ያውቀኛል’ በማለት ይገልፁ የነበሩት።

አፍሪካም ይሁን ሌላው ዓለም የዶክተሩን ብቃት የሚመዝኑት በጤናው ዘርፍ ባከናወኑት ተግባር ብቻ አይመስለኝም። እንዲያውም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው ወቅት ያካበቱትን የዲፕሎማሲ ክህሎት ተጠቅመው የዓለም የጤና ድርጅት ከተለያዩ ለጋሽ ተቋማት ጋር በመቀራረብ እንዲሰራ ያደርጋሉ ከሚል እምነት በመነጨ እምነት ጭምር ነው። ርግጥም የጤና ባለሙያነት ከዲፕሎማሲ ክህሎት ጋር ሲደመር (ለዚያውም በግጭት የሚታወቀውን የምስራቅ አፍሪካን ቀጣና የማረጋጋት ስራ ከባድ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ) የዓለም የጤና ድርጅትን ለመምራት ከበቂ በላይ ይመስለኛል። በዚህም ሳቢያ ነው—የተለያዩ ሀገራት ለዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የድጋፍ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እያሰሙ ያሉት።

ይሁንና መላው የአፍሪካ ሀገራትና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የተለያዩ ማጣሪያዎችን በከፍተኛ ነጥብ አልፈው አሁን እስከሚገኙበት የመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ዶክተሩን እየደገፉ ባሉበት ወቅት፤ በባንዳነት የተሰለፉ አንዳንድ የሽብር ቡድን አባላት፣ ጠባቦች፣ ትምክህተኞችና ዘረኞች የሰውዬውን የምረጡኝ ዘመቻ ለማወክ እየጣሩ ነው። የእነዚህ ቡድኖችና ግለሰቦች ፍላጎት ከኢትዮጵያን አልፎ አፍሪካዊያንን ጭምር የሚያስገርም ይመስለኛል። አፍሪካዊያን ምናልባትም እነዚህ የጥፋት ቡድኖችና ግለሰቦች ከየትኛው ፕላኔት እንደመጡም ሊጠይቁ ይችላሉ። በደመ ነፍስ እንደሚንቀሳቀስ “መንጋ” ሊቆጥሯቸውም ይችላሉ። ምክንያቱም አንድም፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሌላ ኢትዮጵያዊ የዓለም አቀፍ ድርጅትን ለመምራት ሲወዳደር እንደ ጦስ ዶሮ ደንቃራ ሆኖ ይቆማል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው። ሁለትም፣ ማንኛውም አፍሪካዊ ጥቁር የዓለም ድርጅትን ቢመራ ደስታ እንጂ ተቃውሞ ስለማይኖረው ነው።

በእኔ እምነት እነዚህ በአሳፋሪ የጥበትና የዘረኝነት ተግባር ውስጥ የሰመጡ ዜጎች ቢያንስ እንደ ዜጋ ዶክተሩን መደገፍ ሲገባቸው፤ በተቃራኒው ከዶክተሩ ጋር በምርጫ ፉክክር ውስጥ ያሉትን እንግሊዛዊ በመደገፍ ብሎም በዶክተሩ ላይ የውሸት ዘገባዎችን በማጠናቀርና ከፍ ሲልም መግለጫ እስከማውጣት በመድረስ ማንነታቸውን ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን አሳይተዋል። እኔ በበኩሌ በእነርሱ ላፍር ተገድጃለሁ። እናንተዬ ምን ዓይነት መቅለል ነው? ምን ዓይነትስ ፈረንጅ አምላኪነት ነው? ምን ዓይነትስ ኢትዮጵያንና አፍሪካን መናቅ ነው?…ወትሮም የጭፍን ፖለቲካ አራማጅነት ከጥበትና ከትምክህት ወጥቶ ኢትዮጵያዊነትንና አፍሪካዊነት እንዲሁም አለም አቀፋዊነትን ሊያስብ አይችልም። ያም ሆነ ይህ ዶክተሩ ከፍተኛ የህዝባቸውና የአፍሪካ ወንድሞቻቸው ከፍተኛ ድጋፍ ስላላቸው ድል ከእርሳቸው ጋር መሆኑ የሚቀር አይመስለኝም።

በእኔ እምነት የዶክተር ቴዎድሮስ ውድድር በአፍሪካዊነቱ ፋይዳ ስንመለከተው፤ አፍሪካዊና ጥቁር ከኋላ ቀርነትና ከድንቁርና መገለጫነት ተላቅቆ ዓለምን የመምራት ብቃትና ክህሎት ማካበቱን ማሳያ ነው። የዓለምን ድርጅቶች መምራት በእነ ኮፊ አናን ጊዜ ብቻ ያበቃ አለመሆኑንና ዛሬም አህጉሪቱ ዓለምን የሚመሩ ተተኪዎችን ማፍራቷን የሚያረጋግጥም ነው። አፍሪካ ከመፍትሔ ተቀባይነት ወደ መፍትሔ ሰጪነት መሸጋገሯንም ይጠቁማል። እናም እንደ ግንቦት ሰባት ዓይነት የሽብር ቡድኖች፣ ጠባቦች፣ ትምክህተኞችና የጭፍን ፖለቲካ አራማጆች እነዚህን ሁሉ አፍሪካዊ ድሎችን ለመመልከት አይፈቅዱም። ባህር ማዶ ሆነው በባንዳነት ሰልፍ በመውጣት ሀገራዊና አፍሪካዊ ትልሞችን ለማጨናገፍ ይጥራሉ። ግና ጥረታቸው አይሳካም። እንደ በጋ ጉም በንኖ የሚጠፋ ነው። እናም ዶክተሩ እንዳሉት “ድሉ የእኛ ነው”። ይሁንና ድሉን  አስተማማኝ ለማድረግ በሀገር ፍቅርና በአፍሪካዊ ወኔ በውድድሩ ቦታ ላይ በመገኘት በሰላማዊ ሰልፍ ማድመቅ ይኖርብናል። አዎ! በዚህ በዶክተሩ የመጨረሻዎቹ የውድድር ሰዓቶች ጠባቦችን፣ ትምክህተኞችንና ዘረኞችን ልናሳፍራቸው ይገባል።       

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy