የኢትዮጵያን ውድቀት ናፋቂዎች ያዋረደ አሸናፊነት
ብ. ነጋሽ
ባሳለፍነው ሳምንት የቀድሞው የኢፌዴሪ የጤና እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆኖ መመረጥ ኢትዮጵያን ትኩረት ውስጥ የከተተ ዜና ሆኖ ሰንብቷል ። ሁኔታው የኢትዮጵያን መልካም ገጽታዎች ቀልብ በሚስብ አኳኋን አጉልቷል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን የሚመለከት ማንኛውንም ጉዳይ፣ ህዝቡን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን (ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ) ጭምር በመቃወም የሚታወቁ ቡድኖች አቅማቸውን አሟጠው የዶ/ር ቴዎድሮስን የመመረጥ እድል ለማክሸፍ ሞክረዋል።
ከሁለት ዓመት የምረጡኝ ቅስቀሳ በኋላ የዶ/ር ቴዎድሮስ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳየሬክተር ሆኖ መመረጥ በአቦሰጥ የተገኘ አይደለም። ዶ/ር ቴዎድሮስ የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ባገለገሉበት ወቅት በጤና ልማት የተመዘገበው ስኬት ያስገኘው ወጤት ነው። የኢትዮጵያ የጤና ልማት ስኬት በአመዛኙ በእርሳቸው የአገልግሎት ዘመን የተገኘ በመሆኑ እውቅና አግኝተዋል። ስኬቱ የአመራር ብቃት ውጤት ስለሆነ እውቅና ማግኘታቸው ተገቢ (earned) ነው። እርግጥ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ዓለም አቀፍ የጤና ማህበራትንም በመምራት ያስመዘገቡት ውጤት እውቅና አስገኝቶላቸዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት በተለይ ዶ/ር ቴዎደሮስ የጤና ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በጤናው ዘርፍ ያስመዘገበችው ሰኬት ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝቷል። ወባ በተለይ ክረምት እንደወጣ ባሉት ተከታታይ ወራት በሃገሪቱ ቆላማና እርጥበታማ አካባቢዎች በወረርሽኝ መልክ እየተከሰተ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ይገድል ነበር። ታዲያ ሲገድል ሰው አይመርጥም ነበር። መሬት ገምሶ የሚያረሰውን ብርቱ አርሶ አደር ጭምር ነበር እንደዋዛ የሚገድለው። ትውልድ ተኪ ተስፋ ህጻናትና ወጣቶች ከርሞን ሳያዩ ያጨልማቸዋል። በወባ ምክንያት እናቶች፣ እንክብካቤያቸውን የሚሹ ህጻናትን ጥለው ላይመለሱ አሸልበዋል። አሁን ይህ ተቀይሯል። ወባ አሁንም ከኢትዮጵያ ባይጠፋም፣ ክተት አውጆ በአንድና ሁለት ወራት ሺሆችን የሚገድልበት አቅሙ ግን ልምሻ ሆኗል፤ ወባ አሁን በኢትዮጵያ ወረርሽኝ መሆኑ አክትሟል።
መውለድ ለሴቶች የተሰጠ ጸጋ ነው፤ በፈጣሪ የተሰጠ ጸጋ። ሴቶች የሰው ዘር በትውልድ በቅብበሎሽ ዘለዓለም እንዲኖር የማድረግ ጸጋን ነው የታደሉት። ታዲያ በዚህ ጸጋ ልጆች ሲወለዱ ትልቅ ደሰታ ይሆናል፤ በተለይ ለባለጸጋዋ እናት። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የዚህን ጸጋ የማጣጣም እድል ያልነበራቸው እናቶች በርካቶች ነበሩ፤ በወሊድ እየሞቱ። ከ1 መቶ ሺህ እናቶች 1 ሺህ 4 መቶ ትውልድን በሚተኩበት ወቅት – ወሊድ ላይ ህይወታቸው ያልፍ ነበር። ባለፉ ዓመታት ይህ አሃዝ በሁለት ሶስተኛ ቀንሶ አራት መቶ ገደማ ደርሷል።
ትውልድን ሊተኩ ወደዚህ መድር ከሚመጡ ህጻናት መሃከል ብዙዎቹ በጨቅላነታቸው ነበር የሚጠልቁት። ከጥቂት ዓመታት በፊት ከ1 ሺህ ህጻናት 182ቱ በጨቅላነታቸው ነበር የሚቀጩት። አሁን በጨቅላነታቸው የሚቀጩ ህጻናት ከ1 ሺህ በሃያዎቹ የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው። የህጻናት ሞት የጨቅላነት ጊዜያቸውን አልፈው ወፌ ቆመች የተባሉትን፣ ድክ ድክ እያሉ አባታቸውን መከተል፣ ቤተሰቡን ማጫወት የጀመሩትን እስከአምስት ዓመት ያሉትንም ያጠቃ ነበር። ከአምስት ዓመት በታች ከሚገኙ 1 ሺህ ህጻናት 160 ያህሉ ይሞቱ ነበር። አሁን ይህን የህጻናት ሞት በሁለት ሶስተኛ ገደማ መቀነስ ተቸሏል።
ታዲያ በእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የሚሌኒየም የልማት ግብ ማሳካት በመቻሏ እውቅና አግኝታለች።
ከላይ የተጠቀሱትን የጤና ልማት ስኬቶች ለማሳያነት ያህል አነሳሁ እንጂ ኢትዮጵያ ባለፉ ሁለት አስርት ዓመታት በጤና ልማት ዘርፍ እመርታዊ ለውጥ ነው ያስመዘገበችው። ይህ በጤናው ዘርፍ የታየ ልማት በአጋጣሚ የመጣ አይደለም። በጥንቃቄ የተዘጋጀ የጤና ልማት እቅድና የእቅድ አፈጻጸምና አመራር ውጤት ነው። እናም ኢትዮጵያ ውስጥ የተመዘገበው የጤና ልማት ጉልህ ለውጥ ያሳየው ዶ/ር ቴዎድሮስ የጤና ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በመሆኑ የአመራር ብቃታቸው እንደ ስኬቱ ሁሉ ዓለም አቀፍ እውቅናን አስገኝቶላቸዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን ወደ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እጩነት ያመጣቸው፣ በመጨረሻም በ133 ሃገራት ድምጽ አሸናፊ እንዲሁኑ ያደረጋቸው ይህ በእርሳቸው አመራር በሃገራቸው ኢትዮጵያ የተገኘ ስኬት ነው። ይህ የኢትዮጵያ የጤና ልማት ስኬት በኢፌዴሪ መንግስት አፈጻጻም ሪፖርት ብቻ የተገለጸ አይደለም። የልማቱ አጋሮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትንና የዓለም ጤና ድርጅት በራሳቸው መንገድ አጣርተው ያረጋገጡት ነው። ዶ/ር ቴዎደሮስን ለመመረጥ ያበቃቸው ይህ ነው፤ ሌላ ምንም የተሰወረ ሚስጢር የለም።
ይሁን እንጂ፣ ይህ የዶ/ር ቴዎደሮስ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆኖ መመረጥ በጽሁፌ መግቢያ ላይ እንዳነሳሁት የኢትዮጵያንም ስኬት በማሳየት ገጽታዋን ስላደመቀው፣ ቀን ከሌት ለኢትዮጵያ ውርደትና ውድቀት የሚሰሩትን ቡድኖችና ግለሰቦች የእስከዛሬ ገጽታ የማበላሸት ጥረታቸውን በዜሮ የሚያባዛ አደጋ ሆኖባቸዋል። እናም የዶ/ር ቴዎድሮስ እጩነት ተገልጾ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲጀመረ፣ እነርሱም ኢትዮጵያዊውን ዶ/ር ቴዎድሮስ እንዳተመርጡ የሚል ዘመቻ ጀመሩ፤ ባጀት መደበው፣ ቀስቃሽ መልምለው፣ ባለሞያ ቀጥረው ወዘተ።
አነዚህ አብዛቹ ከኤርትራ መንግስት በሚሰጣቸው መመሪያ የሚዘወሩ የኢትዮጵያ ውርደትና ውድቀት ናፋቂዎች፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንዳይመረጡ ለማድረግ የእጩ ማጣራት ሲደረግ የድርጅቱ የቦርድ አባላት ለሆኑ 34 ሃገራት ተወካዮች ደብዳቤ አድርሰዋል። ደብዳቤዎቹ ዶ/ር ቴዎድሮስን በእጩነት እንዳይመርጡ የማከላከል ዓላማ ያላቸው የፈጠራ አስረጂዎችን የያዙ ነበሩ። ዶ/ር ቴዎድሮስ ለእጩነት የቀረቡት በዘፈቀደ ናሙና አወሳሰድ ወይም በእጣ ሳይሆን ተጨባጭ ስራዎቻቸው ሚዛን ደፍተው በመሆኑና የድርጅቱ የቦርድ አባላት ይህን በትክክል ስለሚያውቁ ለደብዳቤው ዋጋ ሳይሰጡት ቀርተዋል።
እናም ዶ/ር ቴዎድሮስ እጩ ሆነው ተመልምለው ምርጫዎች ተጀመሩ፣ የመጀመሪያውን ምርጫ በአሸናፊነት ተወጥተው ሶስት ተፎካካሪዎች ሲቀሩ፣ የኢትዮጵያ ውርደትና ውድቀት ናፋቂዎቹም ዘመቻቸውን ገፉበት። ዘመቻቸውን ቢያጠናክሩም ዶ/ር ቴዎድሮስን እንዳይመረጡ ለማድረግ የሚያቀርቧቸው አስረጂዎች ግን የማይጨበጥ ጉም መሆናቸው አልተቀየረም። ዋናው ምርጫ እየተቃረበ ሲመጣ ለ194ቱ የዓለም የጤና ድርጅት አባል ሃገራት፣ እንደተለመደው በማይጨበጥ የፈጠራ መረጃ የታጀሉ ደብዳቤዎችን ጻፉ። ደብዳቤው የደረሳቸው ሃገራት ተጨባጩን እውነታ ስለሚያውቁት ለዚህ ፍሬ ቢስ ደብዳቤ ዋጋ አልሰጡትም። ለዶ/ር ቴዎድሮስ ድምጽ ያልሰጡትም ቢሆኑ ድምጽ እንዳይሰጡ ያደረጋቸው ምክንያት የኢትዮጵያ ውርደትና ውድቀት ናፋቂዎች “የአትምረጡልኝ” ዘመቻ አይደለም። ሌላ የራሳቸው ተጨባጭ ምክንያት ነው። ይህ ለ194 ሃገራት የተላከ “የአትምረጡልኝ” ዘመቻ እንደውም ቡድኖቹን ትዝብት ላይ የጣለ ነበር።
በዚህ ውጤት እንደማያገኙ ያወቁት የኢትዮጵያ ውርደትና ውድቀት ናፋቂዎች በተለይ የዶ/ር ቴዎደሮስ ተፎካካሪ የነበሩት እንግሊዛዊ ዶ/ር ዴቪድ ናባሮ እንዲያሸንፉ ወደመቀስቀስ ተሸጋግረው ነበር። አብረዋቸው ፎቶግራፍ በመነሳት በፌስቡክ የለቋቋቸውን ቡቱቱ ወሬዎች ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። ዶ/ር ናባሮ ጽንፍ ከረገጡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ጋር በመሆን ያካሄዱት ቅስቀሳ ለትዝብት ከመዳረግ ያለፈ ውጤት አላስገኘላቸውም። በዚህ አኳኋን ይህኛውም የኢትዮጵያ ውርደትና ውድቀት ናፋቂዎቹ ዘመቻ ትርፍ ሳያስገኝ ቀረ።
የኢትዮጵያ ውርደትና ውድቀት ናፋቂዎቹ ዘመቻ እስከመጨረሻው የምርጫ ሰአት የዘለቀ ነበር። መጨረሻ ላይ ምርጫው በሚካሄደበት ጄኔቭ “የአትምረጡልኝ” ሰልፍ ከማካሄድ አልፈው፣ ምርጫው የሚካሄድበት አዳራሽ ውስጥ በመግባት እስከመጮህ ደርሰው ነበር። ዘላለም ተሰማ የተባሉ እንግሊዛዊ ለዚሁ ጉዳይ ከለንደን ወደጄኔቭ ተጉዘው የዓለም የጤና ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባኤ የዋና ዳይሬክተሩን ምርጫ በሚያካሂድበት ወቅት አዳራሽ ውስጥ በመግባት “Africa think again; no Dr Tedros for WHO …” እያሉ አንቧርቀው ነበር። እንግሊዛዊው ዘላለም ተሰማ ግን በጸጥታ አስከባሪዎች ተገፍተው ከመውጣት ያለፈ ምንም ያተረፉት ነገር አልነበረም። እናም ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከ194 የዓለም የጤና ድርጅት አባል ሃገራት የ133ቱን ድምጽ በማግኘት አሸንፈው፤ አሸናፊነታቸው ታወጀ።
ይህ የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆኖ መመረጥ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ያጎላዋል። ለዚህ ያበቃቸው ኢትዮጵያ በእርሳቸው አመራር በጤና ልማት ያስመዘገበችው ስኬት በመሆኑ የዶ/ር ቴዎደሮስ መመረጥ ለኢትዮጵያ የጤና ልማት ሰኬት የተሰጠ እውቅና ተደረጎ ሊወሰድ ይችላል። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫው ወቅት የተጨነቀውና እንዲያሸንፉ የጸለየው፤ ማሸነፋቸው ሲታወጀ በደስታ ስሜት የጦዘው ለዚህ ነው። የዶ/ር ቴዎደሮስ የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ሆኖ መመረጥ ለኢትዮጵያውያን ኩራት፣ የኢትዮጵያን ውርደትና ውድቀት ለሚናፍቁ የኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች ደግሞ ልካቸውን ያሳወቀ ውርደት ነው።