Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢትዮጵያን ፕሬስ የማያንጸባርቁ ወሬዎች

0 335

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያን ፕሬስ የማያንጸባርቁ ወሬዎች/ኢብሳ ነመራ/

ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን ሚያዚያ 25 ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሯል። የፕሬስ ቀን መከበር የጀመረው የተባባሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት  እ ኤ አ በ1991 ዓ/ም ባካሄደው 26ኛ አጠቃላይ ስብሰባ ያሳለፈውን ውሳኔ መነሻ በማደረግ ነው። የተባበሩት መንግስታ ድርጅት በ1993 ዓ/ም የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅቱን ሃሳብ ተቀብሎ ሜይ 3 (ሚያዚያ 25) በየአመቱ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን ሆኖ እንዲከበር ውሳኔ አሳለፈ። የፕሬስ ቀን ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሃያ ስድስተኛ ጊዜ ተከብሯል። ኢትዮጵያ ሃሳብን የመግለጽና የፕሬስ ነጻነትን ለመጀመሪያ ጊዜ ያረጋገጠችው የፕሬስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ መከበር በጀመረበት ቀጣይ ዓመት ማለትም በ1992 ዓ/ም ነበር። ከዚያ በፊት በኢትዮጵያ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የፕሬስ ነጻነት የሚባል ነገር አልነበረም። የነጻውን ፕሬስ ዓለም እጅግ ዘግይታ የተቀላቀለችው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀንን ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ በሃገር አቀፍ ደረጃ አክብራለች።

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን  “Critical Minds for Critical Times: Media’s role in advancing peaceful, just and inclusive societies” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከበረው። እለቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያዚያ 23 እስከ 26 በተለያዩ ሁነቶች በኢንዶኔዢያ ጃካርታ ነው የተከበረው።

የፕሬስ ቀን ሃሳብን የመግለጽ መሰረታዊ መብቶች የሚከበሩበት ነው። በዚህ ዕለት በመላው ዓለም የሚገኙ ፕሬሶች የሚገኙበት ደረጃ ይገመገማል። በመገናኛ ብዙሃን ነጻነትና ገለልተኝነት ላይ የሚደረጉ ተጽእኖዎችን የመከላከል ዓላማም አለው። በስራ ላይ እያሉ ህይወታቸውን ያጡ ጋዜጠኞችም በዚህ ዕለት ይዘከራሉ።

የዘንድሮው የፕሬስ ቀን በኢትዮጵያ ሚያዚያ 25፣ 2009 ዓ/ም በሃገር አቀፍ ደረጃ የግልና የህዝብ ሚዲያ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ተከብሮ ውሏል። በዚህ መድረክ ላይ በሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል።

በዚህ መድረክ ላይ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ንግግር አድርገዋል። ዶ/ር ነገሪ በንግግራቸው፤ የአገሪቱ ሚዲያ በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማጋለጥ የህግ የበላይነት እንዲከበር አስተዋጽኦ በማበርከት ረገድ ብዙ ይቀረዋል። ሙያዊ ሥነምግባር በተላበሱ ጋዜጠኞች፣ በእውቀትና በክህሎት የተደራጁ የሚዲያ ተቋማት እንዲፈጠሩ መንግስት የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታልም ብለዋል።የዚህ አይነቱ የሚዲያ ተቋም ለአገሪቱ የእድገት ጉዞ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በበዓሉ ላይ ጥናታዊ ጽሁፉ ያቀረቡት የሪፖርተር ጋዜጣ አሳታሚ የሆነው የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ቼንተር ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አረጋዊ መንግስት የሚዲያውን ዘርፍ ለማሳደግ ልዩ ትኩረት መስጠት አለበት ብለዋል። የግልም ሆኑ የመንግስት ሚዲያ ተቋማት ከራሳቸው የሚመነጩ ድክመቶች እንዳሉባቸው ያመለከቱት አቶ አማረ የመገናኛ ብዙሃን በተለይ በመንግስት በኩል ድጋፍ ስለማይደረግላቸው ጠንካራ መሆን ተስኗቸዋል ብለዋል። በተለይ የግሉ ዘርፍ የሚዲያ ህጎችና የፕሬስ ነጻነትን ተግባራዊ የማድረግ ክፍተቶች አሉበት በማለትም ተችተዋል። መንግስት በህገ መንግስቱ የተቀመጡ ፕሬስን የሚመለከቱ ህጎችን የሚቃረኑ አዋጆችና ደንቦች በማውጣት ለሚዲያው መዳከም የራሱን ሚና ተጫውቷል ሲሉም ነቅፈዋል።

አንድ አማረ አረጋዊ በዚህ መድረክ ላይ ያነሱትን ብዙዎች ያላስተዋሉትን ወይም ማስተዋል ያልፈለጉትን እውነት ማስታወስ እፈልጋለሁ። እርግጥ አቶ አማረ ይህን ሲናገሩ የመጀመሪያቸው አይደለም፤ ከዚህ ቀደምም በተለያየ መድረክ ላይ ተናግረውታል። ይህም እነ ሲፒጄን የመሳሰሉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ነን የሚሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትን የሚመለከት ነው። ይህን አስመልክቶ በሰጡት አስተያያት እነ ሲፒጄ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞችን መበት የሚያስታውሱት ታስረው ቃሊቲ/ቂሊንጦ ሲወርዱ ወይም ሲሰደዱ ብቻ ነው። በስራ ላይ ያሉ ጋዜጠኞችን አያስታውሱም። ያልተጣራ መረጃ በመያዝ ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ ብለዋል።

ይህ አስተያያት በውስጡ ብዙ መልዕክት ይዟል። ሲፒጄና ሌሎች የተወሰኑ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች/የመገናኛ ብዙሃን መብት ተቆርቋሪ ነን፣ የሰብበአዊ መብት ተሟጋች ነን የሚሉ በምዕራባውያን ቱጃሮች የሚደገፉና የሚመሩ ተቋማት ሃሳብን ከመግለጽ ነጻነት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን እጅግ አብዝተው በተደጋጋሚ ሲተቹ መቆየታቸው ይታወቃል። በተለይ ሲፒጄ የፕሬስ ነጻነትን መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ለመስራት የተቋቋመ ነው የሚመስለው። የሲፔጄን ሪፖርቶች ብቻ የሚመለከት ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም ነጻ ፕሬስ፣ አንድም ጋዜጠኛ ያለ አይመስለውም። መንግስት ሁሉንም ነጻ ፕሬሶች የዘጋ፣ ሁሉም ጋዜጠኞች እስር ቤትና በሰደት ያሉ ነው የሚመስለው።

ሲፒጄና ኘሰሎቹ ኢትዮጵያ ላይ ለሚያወጡት ሪፖርት መነሻ የሚያደርጉት አቶ አማረ እንደገለጹት ያልተጣራ መረጃ በመያዝ ነው። ትኩረታቸው አጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በስራ ላይ ያሉ መገናኛ ብዙሃን እንቅስቃሴ ሳይሆን፣ የጋዜጠኞች መከሰስ ወይም መሰደድ ነው። ሲፒጄና መሰሎቹ ጋዜጠኞች ታሰሩ ተሰደዱ ከማለት ውጭ አነድመ ግዜ የታሰሩበትንና ለስደት ያበቃቸውን ምክንያት በወጉ መርምረው ሚዛናዊ ለመሆን ሞክረው አያውቁም። አንድ ጋዜጠኛ ክስ ሲመሰረትበት ይህችን ጫፍ የዘው ኢትዮጵያን ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት፣ የፕሬስ ነዓነት የተደፈጠጠባት ሃገር አድርገው ሪፖርት ያወጣሉ። የታሰሩና የተሰደዱ ጋዜጠኞችን ቁጥር እየጠቀሱ ሃሳብን በመግለጽ ወይም በፕሬስ ነጻነት መከበር የምትገኝበትን ደረጃ ለማራከስ፣ ሃሳብን የመግለጽና የፕሬስ ነጻነት በህግ ካልተረጋገጠባትና በሃገር ውስጥ አንድም ነጻ ፕሬስና ጋዜጠኛ ከሌለባት ኤርትራ ጋር እያነጻጻሩ ለማቀረብ ይሞክራሉ።

እነ ሲፒጄ አቶ አማረ አረጋዊ እንደገለጹት በስራ ላይ የሚገኙትን የግል ፕሬስ ውጤቶችና ጋዜጠኞች ሁኔታ ማንሳት አይፈልጉም። ጋዜጠኞቹን ለክስና ለስደት ያበቃቸውን ምክንያት በጨረፍታም ሳይጠቅሱ መታሰራቸውና መሰደዳቸው ላይ ብቻ የሚያተኩሩት የፕሬስ ነጻነት በይፋ ከተገደበባቸው ኤርትራና ሰሜን ኮሪያ ጋር በማነጻጻር ዋጋ ለማሳጣት ስለሚመቻቸው ነው። የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሃሳብን የመግለጽ/የፕሬስ ነጻነት የሚገኝበትን ሁኔታ ካቀረቡ በጎ ገጽታው ስለሚጎላ ዋጋ ለማሳጣት ያስቸግራቸዋል። ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ 30 ያህል የግል የህትመት ፕሬሶች፣ 20 የግል ሬዴዮ ጣቢያዎች፣ 28 የማህበረሰብ ሬዴዮ ጣቢያዎች ይገኛሉ። በእነዚህ የመገናኛ በዙሃን ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች ይሰራሉ። እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን በተለይ የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን በማጋለጥ ረገድ እየሰሩ ነው ብሎ መውሰድ ባይቻልም፣ መንግስትንና ገዢውን ፓርቲ መተቸት አሉባቸው ብለው ባመኑባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በዘገባዎችባ በነጻ አስተያየቶች እየተቹ ይገኛሉ። እነ ሲፔጂ ከእነዚህ ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች ይልቅ ቀልባቸውን የሚስባቸው እንደማንኛውም የደሃ ሃገር ወጣት ወደአውሮፓና አሜሪካ የመሄድ ፍላጎተ ያላቸው ጋዜጠኞች ወደጎረቤት ሃገር በሰላም ተጉዘው በዚያ ለተባበሩት መንግስታት የሰደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን መንግስት አስፈራራኝ፣ ሊያስረኝ ነው፣ ምንትስ ቅብጥርስ የሚል ኬዝ አቅርበው የተሰደዱ እንዲሁም በይፋ የፍርድ ሂደት ክስ የተመሰረተባቸውና ቅጣት የተላለፈባቸው በጣት የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች ናቸው። ሲፒጄና መሰሎቹ ለሪፖርታቸው ማሟያ ጋዜጠኞች እንዲሰደዱ ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ መሆኑን የሚያመለክቱ ማስረጃዎችም አሉ።

እነ ሲፒጄ ይህን የሚያደርጉት ባለማወቅ አይደለም። ሆን ብለው ነው። ተቋማቱ ቀድሞውኑ የተመሰረቱበት ዋነኛ ዓላማ ሃሳብን የመግለጽ መብት/የፕሬስ ነጻነት የሚስፋፋበትንና የሚጎለብትበትን፣ ጋዜጠኞች የዳበረ ክህሎት ኖሯቸው በነጻነት መስራት የሚችሉበትን የፕሬስ ምህዳር ለመፍጠር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሃሳብን በነጻነት በመግለጽና በጋዜጠኞች መብት ተከራካሪነት ካባ ርዕዮተ ዓለማዊ አጀንዳን ለማራመድ የተመሰረቱ ናቸው። አብዛኞቹ ምዕራባውያን ካፒታሊስት መንግስታት የሚከተሉትን ገበያ አክራሪ ኒዮ ሊበራል ርዕዮተ ዓለም የማስፋፋት ተልዕኮ ያላቸው ናቸው። ዓላማቸው ከሊበራሊዝም ርዕዮተ ዓለም ውጭ የሆኑ ሃገራትን በተለይ  በልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ውጤት እያስመዘገቡና ለሌሎች ሞዴል ሊሆኑ የሚችሉ ሃገራትን በሰብአዊ መብት ጥሰት በማሸማቀቅና ለዓለም አቀፍ ጫና በመዳረግ የሃገር ግንባታ ሂደታቸውን መቀልበስ ነው።

እነሲፒጄ ስለኢትዮጵያ የሚያወሩት በሃገሪቱ ያለውን የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ አያንጸባርቅም ማለት ግን በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ሙሉ በሙሉ ተረጋግጧል ማለት እንዳልሆነ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ። በአስፈጻሚዎች ትዕዛዝ ብቻ የታሰሩ ጋዜጠኞች፣ እንዲዘጉ የተደረጉ ጋዜጦች መኖራቸው ይታወቃል። ይህን በተለይ በግሉ ፕሬስ ውስጥ የሰራን ጋዜጠኞች ሁሉ የምናውቀው እውነት ነው። ጋዜጠኞች በድንገት ያለምንም የፍርድ ቤት ማዘዣ፣ ምን እንዳጠፉ እንኳን ሳይነገራቸው በፖሊስ ከቢሯቸው የሚወሰዱበት ሁኔታ የተለመደ ነበር። በዚህ ሁኔታ ለቀናትና ለወራት በማረፊያ ቤት በእስር ላይ እንዲቆዩ የተደረጉም አሉ። ይህ ሁኔታ አስደንብሯቸው እውነትን ከመዘገብ ይልቅ፣ የማያውቁትን ባላጋራቸውን የማያስኮርፍ ጉዳይ ለመዘገብ ራሳቸውን ሳንሱር ለማድረግ የተገደዱ፤ ጭራሽ የጋዜጠኝነት ስራቸውን እርግፍ አድርገው የተዉ፣ የተሰደዱም መኖራቸው አይካድም። ይህ ግን እነ ሲፒጄ እንደሚያወሩትና እንደሚያስወሩት ሙሉውን የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ገጽታ የሚወክል አይደለም።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ራሳቸው ነጻ ያልነበሩ በርካታ ጋዜጦችና መጽሄቶች ነበሩ። በገለልተኝነት ከመስራት ይልቅ በተለይ ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለመናድ በይፋ አውጀው በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ገንዘብ የተቋቋሙና ህገመንግስታዊ ስርአቱን የመናድ አመለካከት ለማራመድ ዓላማ የተቋቋሙ ጋዜጦችና መጽሄቶች እንደነበሩ ጋዜጠኞችም፣ ህዝቡም ያውቃሉ። ይህን የጋዜጦቹንና መጽሄቶቹን ዓላማ የመደገፍና ያለመደገፍ ልዩነት እንጂ ይህን ዓላማ ይዘው ይሰሩ የነበሩ ጋዜጦችና መጽሄቶች መኖራቸውን የሚክድ የለም።

በኢትዮጵያ ሃሳብን የመግለጽ መብትና ይህ መብት እውን የሚሆንበት የፕሬስ ነጻነት በህገመንግስት ነው የተረጋገጠው። የሁን እንጂ ይህ መብት የሌሎች ዜጎችን መብትና ነጻነት እንዲሁም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ጭምር የተረጋገጠበትን ህገመንግስታዊ ሥርአት ለመጠበቅ ዓላማ ገደቦች ተጥለዋል። ሃሳብን በነጻነት የመያዝና የመግለጽ መብትን ያረጋገጠው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 29 በንኡስ አንቀጽ 6 እና 7 ላይ የሚከተሉትን ገደቦች ደንግጓል።

 

  • እነዚህ መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሃሳብና መረጃ የማግኘት ነጻነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚቸለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመስርተው በሚወጡ ህጎች ይሆናል። የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ሥም ለመጠበቅ ሲባል ህጋዊ ገደቦች በእነዚህ መበቶቸ ላይ ሊደነገጉ ይችላሉ። የጦር ቅስቀሳዎች፣ እንዲሁም ሰብአዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በህግ የሚከለከሉ ይሆናል።
  • ማንኛውም ዜጋ ከላይ በተጠቀሱት መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ህጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ በህግ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል።  

 

እንግዲህ ይህን የህገመንግስት ድንጋጌና ይህን ድንጋጌ መነሻ በማድረግ የወጡ ህጎችን ጥሰዋል ሊያስብል የሚችል ማስረጃ በተገኘባቸው ጋዜጠኞችና ሌሎች ዜጎች ላይ ክስ መመሰረቱ አይካድም። በይፋ የፍርድ ሂደት ጥፋተኝነታቸው የተረጋገጠ ደግሞ ጥጣት ተወስኖባቸዋል። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሃገር የሚደረግ በመሆኑ ህጋዊና ተገቢ ነው።

ሲፒጄና መሰሎቹ ጋዜጠኞች ተከሰሱ፣ ተፈረደባቸው፣ ተሰደዱ . . . የሚለውን ወሬ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት አውድ ውጭ በማራገብ፣ የኢትዮጵያን ገጽታ ለማበላሸት መንገድ አመቻችተው ከሃገር እንዲወጡ ያደረጓቸውንና የሚሸልሟቸውን ጋዜጠኞች እየጠቀሱ የሚያወጧቸው ሪፖርቶች፣ የኢትዮጵያ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የፕሬስ ነጻነት የሚገኝበትን ደረጃ አያንጸባርቅም። ይህ የእነ ሲፒጄ ወሬ የሃገሪቱን ገጽታ በመሰረተ ቢስ ወሬ ከማበላሸት ያለፈ ለሃገሪቱ የፕሬስ እድገት የሚያበረከተው ፋይዳም የለውም።        

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy