NEWS

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አራት ምክትል ፕሬዚዳንቶቹን ከሀላፊነት አነሳ

By Admin

May 02, 2017

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አራት ምክትል ፕሬዚዳንቶቹን ዛሬ ከሀላፊነት አንስቷል።

የባንኩ የኮርፖሬት ማስተዋወቅና ግንኙነት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ሀይሉ ምስጋናው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ የሊዝ ፋይናንስ እና ቅርንጫፎች ስራ ምክትል ፕሬዚዳንት ከሆኑት አቶ ተሾመ ዓለማየሁ በስተቀር ሌሎቹ አራት የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ከሀላፊነታቸው ተነስተዋል።

ከሀላፊነታቸው በተነሱት አራት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ምትክም የባንኩ ፕሬዚዳንት ጌታሁን ናና አዳዲስ ምክትል ፕሬዚዳንቶችን ሾመዋል።

በዚህ መሰረት አቶ ጌታቸው ዋቄ የፕሮጀክት ፋይናንስ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አቶ ሃይለእየሱስ በቀለ የብድር አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አቶ ሃዱሽ ገብረእግዚአብሄር የኮርፖሬት አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት እና አቶ እንዳልካቸው ምህረቱ የፋይናንስና ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ተሾመዋል።

በቅርቡ ለባንኩ አዲስ ፕሬዚዳንት መሾሙን ተከትሎ የተዘጋጀ አዲስ መዋቅርን መሰረት በማድረግ ምክትል ፕሬዚዳንቶቹ ተነስተዋል ነው የተባለው።

ተቋሙ በለውጥ ሂደት ውስጥ በመሆኑና ለዚህ አዲስ አደረጃጀት እየሰራ መሆኑም ለምክትል ፕሬዚዳንቶቹ መነሳት ምክንያት ነው ተብሏል።

እንደ አቶ ሃይሉ ገለጻ ባንኩ አደረጃጀቱን በአዲስ የሰው ሃይል ማሟላት በማስፈለጉ ምክትል ፕሬዚዳንቶቹ ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል።

ለተሰናባቾቹ ምክትል ፕሬዚዳንቶች የደረሰው ደብዳቤም ለአገልግሎታቸው ምስጋናን ያካተተ መሆኑ ተመልክቷል።