Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት

0 978

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት

ስሜነህ

ለሃገራችን  ኢኮኖሚ  የመዋቅር ሽግግር  ወሳኝ ድርሻ ካላቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት መሆኑ ታምኖበትና ስትራቴጂ ተነድፎለት እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ከሚረጋገጥበት ማሳያዎች አንዱ ለዜጎች በሚፈጥሩ የሥራ ዕድል  ሲሆን የውጪ ምርቶችን በዓይነትና ብዛት የሚያሳድጉ መሆኑም ሌላኛው የፓርኮቹ ወሳኝነት መገለጫ ነው።

ስለሆነም ሃገራችን በርካታ  የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማልማት ላይ ትገኛለች፡፡ የሃገራችን ኢኮኖሚ ከግብርና  ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር  የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ለዚህም  መንግስት  ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ በሁሉም  የአገሪቱ አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት የአገሪቱን እድገት ለማስቀጠል በመስራት ላይ  ይገኛል። የነዚህን ፓርኮች ፋይዳ በሚገባ ለማጤን ማሳያዎች መመልከት ተገቢ ይሆናል።

በ250 ሚሊዮን ዶላር በቻይናው ተቋራጭ (ሲሲኢሲሲ) ኩባንያ የተገነባው እና በሃዋሳ የሚገኘው የኢንዱስትሪ መንደር ለ60 ሚሊዮን ዜጎቻችን የስራ እድልን ያስገኛል።ይህ መንደር አለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟላና ይልቁንም ሃገራችን በአለም አቀፍ መድረኮች  የምትሞግትለትን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂንም የተከተለ ነው።

በበርካታ የምጣኔ ሃብታዊ ምሁራን አስተያየት መሰረት ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ ውድድር ላይ የመግዛት እንጂ የመሸጥ ተሳትፎዋ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ያመለክታል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ሚና አነስተኛ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይጠቅሳል ። ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠይቅ ፣ የቴክኖሎጂ አቅም ስለሚሻ እና ጠንካራ የማኔጅመንት ክህሎትንም ስለሚጠይቅ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አልሚ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዳይሳተፉ ካደረጓቸው ምክንያቶች በቀዳሚነት የሚጠቀሱቱ ናቸው።

ኢንቨስተሮች ከሚገጥሟቸው ችግሮች መካከል በዋናነት የመሬት እና የባንክ ብድር ሲሆኑ ሌላው እና ግዙፉ ፈተና ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የነበረ መሆኑ ይታወቃል ። በተለይ መሬት ለማግኘት በኪራይ ሰብሳቢነት ምክንያት ያለው ውጣ ውረድ አሰልቺ መሆኑ የአደባባይ ሃቅ ነው ። ከዚህ ዓይነቱ ውስብስብና ድካም በኋላ መሬቱ ሲገኝም ህንጻውን ለመገንባትና ከፋይናንስ ጋር ተያያዥ የሆነው ፈተናም ባለሃብቱን የሚያሸሽ መሆኑም ይታወቃል። እኒህን በመሰሉ በርካታ ችግሮች የተተበተበው ይህ ዘርፍ የቢሮክራሲው ሂደት ሲታከልበት በእርግጥም አልሚውን ወደ ኋላ የሚጎትት መሆኑ አያጠያይቅም ።አሁን ግን ለኢንዱስትሪ ፓርኮች በወጣው ፖሊሲ የተመራው መንግስት ይህን ቁስል የሚያሽር መፍትሄ  በነዚሁ ፓርኮች  አዘጋጅቷል፡፡

እንደማሳያነት የወሰድነው የሃዋሳ የኢንዱስትሪ መንደር ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን ያሟላና ከብክለት ነፃ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ሲሆን፣ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ መሆኑ የመጀመሪያው  ማሳያ ነው። የፓርኩ አሠራር ውስብስብ፤ ከፍተኛ የማስተዳደር ክህሎት የሚጠይቅና በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ለማስተዳደር የሚያስቸግር በመሆኑ፣ በውጭ ኩባንያዎች ለሦስት ዓመታት እንዲተዳደር በመንግሥት መወሰኑ አሉታዊ ትርጓሜ ያለው ቢያስመስለውም ከሶስት አመት በኋላ ወይም በሁለተኛው ዙር የእቅዱ የማጠናቀቂያ ዘመን የሚገነባውን የሃገር ውስጥ አቅም ማስላት ያስፈልጋል።

ይህ ፓርክ ከብክለት ነፃ እንዲሆን ፍሳሽ አልባ ቴክኖሎጂ (Zero Liquid Discharge) የተከለው የህንዱ አርቪን ኩባንያ ይህንን ኃላፊነት መውሰዱን ወደፊት ሊገነቡ ከታሰቡት ፓርኮች አንጻር ከወዲሁ እየተገነባ የሚዘጋጀውን አቅም ስናሰላ የፓርኮቹ ፋይዳ ግልጽ ይሆናል፡፡ የሃዋሳ ኢንዱስትሪ መንደር ሃያ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት አምራች ፋብሪካዎችን የያዘ ሲሆን 1.3 ሚሊዮን ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ እና በውስጡ ያሉት የፋብሪካዎቹ መጠለያ ብቻ በ300 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ላይ የተገነቡና ግዙፍ ፓርክ ነው፡፡ ይህ መንደር በጠቅላላ 18 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገዶች ሲኖሩት፣ 21.5 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመር፣ 16 ኪሎ ሜትር የስልክ መስመሮችና 23 ኪሎ ሜትር የንፁህ ውኃ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች ተዘርግተውለታል፡፡ በተጨማሪም በፓርኩ ውስጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ሱቆችና የተለያዩ አገልግሎቶች ለሚሰጡ ተቋማት የሚውሉ ቢሮዎችም ተገንብተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ለአምራቾች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ የታሰቡ የአንድ መስኮት አገልግሎቶች የተሟሉለት ሲሆን፣ ዋና ዋናዎቹም የኤሌክትሪክ፣ የውኃ፣ የስልክ፣ የሎጂስቲክስ፣ የጉምሩክ፣ እንዲሁም የቪዛ አገልግሎትን ያካተተ በጥቅሉ ውጣውረድ ያልበዛበትና የኪራይ ሰብሳቢ ቢሮክራቶችን ቀዳዳዎች ሁሉ የሚደፍን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው፡፡

በዚህ መንደር በዘርፉ ዓለም አቀፍ ዝና ያላቸው 14 የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ምርታቸውን ማምረት ጀምረዋል ፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የ130 ዓመታት ልምድ እንዳለው የሚነገርለት የአሜሪካው ፒቪኤች ይገኝበታልና የሚገነባውን ትልቅ ሃገራዊ አቅም መገመት አይከብድም ፡፡ ከልምዶቹ  ባሻገር ፒቪኤች ካልቪን ክሌይ፣ ቶሚ ሂል ፊገርና በመሳሰሉት አልባሳት መለያዎች (ብራንዶች) መታወቁም  የፓርኩን የላቀ ፋይዳ ያመላክታል ፡፡ እንዲሁም የቻይናው ውሺ ጂንማኦ፣ የህንዱ አርቪንድ የመሳሰሉትን ጨምሮ የሆንግ ኮንግ፣ የቤልጂየም፣ የሲሪላንካና የአሜሪካ ኩባንያዎች ስንቅና ትጥቃቸውን አሟልተው በመንደሩ ተገኝተዋል ፡፡

 

የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ስድስት ሲሆኑ፣ አቅማቸውንና ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ ከመንግሥት ልዩ ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑም ስለአቅም ግንባታና አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ፖሊሲው የሰጠውን ትኩረት የሚያመላክት ነው  ፡፡ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ገብተው ለሚሳተፉ ባለሀብቶች መንግሥት እስከ 85 በመቶ የሚደርስ የባንክ ብድር ያመቻቸ መሆኑም ስለእቅዱ መሳካት  ማረጋገጫ ነው ።

 

የሃገሪቱ የጨረቃ ጨርቅና አልበሳት ኢንዱስትሪ በጠቅላላው እስካሁን ማመንጨት የቻለው የውጭ ምንዛሪ 110 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው። የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻውን አሥር እጥፍ ኤክስፖርት ለማድረግ ይቻለዋል፡፡ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች የሚያገኙት የአቅም ግንባታ ተደማምረው ለአገሪቱ ኢንዱስትሪ አዲስ አብዮት ለመፈንጠቅ ያስችላል ።  

ሌሎቹንም እንመልከት። ሦስት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በአዲስ አበባና ጂማ ከተሞች በ10.5 ቢሊዮን ብር የመገንባት ሂደት እንደተጀመረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የመጀመሪያው ኢንዱስትሪ ፓርክ በቦሌ ለሚ በ3.5 ቢሊዮን ብር የሚገነባ ሲሆን፣ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ሁለተኛ ምዕራፍ ነው፡፡ የቦሌ ለሚ ሁለት ኢንዱስትሪ ፓርክ ለጨርቃ ጨርቅና ለአልባሳት ኢንዱስትሪዎች ልማት የተመደበ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኩን ግንባታ የሚያከናውነው ‹‹ሲጂሲኦሲ›› የተሰኘ የቻይና ኮንትራክተር ሲሆን የፕሮጀክቱ አማካሪ ዶዋ የተባለ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ መረጃው ይጠቅሳል፡፡

ሁለተኛው የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እየተካሄደ ያለው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቂሊንጦ አካባቢ ነው፡፡ የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ የሚለማበት ሲሆን፣ የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች የሚፈበረኩበት ይሆናል፡፡ በ5.5 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚካሄደው የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ12 ወራት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ተነግሯል፡፡ግንባታውን የሚያካሂደው ‹‹ሲቲሲኢ›› የተባለው የቻይና ኮንትራክተር ሲሆን፣ ዶዋ የተባለው የኮሪያ ኩባንያ ፕሮጀክቱን እንዲቆጣጠር ተመርጧል፡፡

ሦስተኛው የኢንዱስትሪ ፓርክ እየተገነባ ያለው በጅማ ከተማ በ1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ ሲሆን፣ በዘጠኝ ወራት ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ የጂማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪዎች ልማት ላይ የተኮረ ነው፡፡ ግንባታውን የሚያከናውነው በኢትዮጵያ ትልልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶችን የሚያካሂደው ‹‹ሲሲሲሲ›› የተሰኘው የቻይና ኮንትራክተር ነው፡፡ ‹‹ኤምኤች›› ኢንጂነሪንግ የተባለው አገር በቀል አማካሪ ኩባንያ የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ እንዲሆን ተመርጧል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የተቋቋመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦሌ ለሚ አንድና የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በከፍተኛ ፍጥነት አጠናቆ ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመቐለ፣ የኮምቦልቻ፣ የአዳማና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማልማት ላይ ነው፡፡ የአዳማና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ደግሞ በቅርቡ ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀመሩም ተነግሯል።  

በሌላ በኩል በአራት ክልሎች የተቀናጁ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በ1.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሊጀመር እንደሆነም ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶችን የሚያቀነባብሩ ፋብሪካዎች የሚገነቡባቸው ሲሆን፣ ፓርኮቹ የሚገነቡት በአማራ ክልል ቡሬ፣ በምዕራብ ትግራይ ባከር፣ በኦሮሚያ ዝዋይ አካባቢ ቡልቡላ፣ በደቡብ ክልል ይርጋለም ከተማ ነው፡፡

የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እያንዳንዳቸው በ250 ሔክታር ቦታ ላይ በፓይለት ፕሮጀክት ደረጃ ተጀምሮ ወደ 1,000 ሔክታር እንደሚሰፉ የሚያመለክቱት መረጃዎች ፤ፓርኮቹን በባለቤትነት የሚገነቡት በየክልሉ የተቋቋሙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽኖች ናቸው፡፡  

በፓርኮቹ የሚቋቋሙት መሠረተ ልማቶች የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዝርጋታዎች፣ የፈሳሽና የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ መስመሮች፣ ሞዴል የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያና ማምረቻ ሕንፃዎች፣ የማቀነባበሪያና ማምረቻ ድጋፍ ሰጪ መሣሪያዎችና መገልገያዎች መትከያ ሕንፃዎች፣ የጥሬ ዕቃዎችና የምርት መጋዘኖች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ፣ የአስተዳደር ቢሮ ሕንፃዎች፣ የባንክ፣ ኢንሹራንስ፣ የማሪታይም፣ የትራንዚት አገልግሎት ቢሮዎች፣ የሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች መኖሪያ ቤቶች ሕንፃዎች፣ የሠራተኞች ማሠልጠኛ ማዕከል፣ የመዋዕለ ሕፃናትና ትምህርት ቤት፣ አረንጓዴ ቦታዎችንም ያጠቃልላሉ።  

ለእያንዳንዱ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ 50 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክና 6,000 ሜትር ኩብ ውኃ እንደሚያስፈልግ ተገምቷል፡፡ የፓርኮቹ ግንባታ ተጠናቆ በሙሉ አቅማቸው ሲሠሩ ከቡሬ ፓርክ በዓመት 558,000 ቶን መጠን ያላቸው የተለያዩ ምርቶች እንደሚመረቱና 14 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚገኝ፣ ከባከር ፓርክ 700,000 ቶን መጠን ያላቸው የተለያዩ ምርቶች እንደሚመረቱና 18 ቢሊዮን ብር ሽያጭ እንደሚገኝ፣ ከቡልቡላ ፓርክ 591,000 ቶን ምርትና 14 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚገኝ፣ ከይርጋለም ፓርክ 233,000 ቶን ምርትና ስድስት ቢሊዮን ብር ሽያጭ እንደሚገኝ በመረጃዎቹ የተመለከተ ሲሆን፤ እያንዳንዱ ፓርክ 419,000 ቀጥተኛ የሥራ ዕድል፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ ለ210,000 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡

የፓርኮች ልማት  በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲሆን ታስቦ እየተገነቡ በመሆናቸው ተመጣጣኝ እድገት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲኖር  ያስችላሉ፡፡  እንዲሁም ለዜጎች ከፍተኛ የስራ ዕድል ከመፍጠራቸው ባሻገር የወጪ ምርቶች ላይ እሴት የሚጨምሩ በመሆናቸው የውጭ ምንዛሬንም  ያሳድጋሉ። መንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በራሱ ወጪ የሚገነባው የአገር ውስጥንም ሆነ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ሲል ነው። እነዚህ በመንግስት ከፍተኛ ወጪ እየለሙ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አስፈላጊው መሰረተ ልማት ሁሉ የተሟላላቸው ስለሆኑ ባለሃብቶች በቀላል ወጪና በአጭር ጊዜ ወደ ምርት የሚያሸጋግሯቸው በመሆኑ  ባለሃብቶችን ትርፋማ ያደርጋሉ።  እየለሙ ያሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘመኑ የደረሰባቸው የግንባታ ሂደትን የተከተሉ በመሆናቸው ከአካባቢ ብክለት የፅዱ ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር ተረፈ ምርታቸውን እንደገና መጠቀም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙላቸው  በመሆናቸው  የሃብት ብክለትን ይቀንሳሉ፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy