CURRENT

የከተሞች የጎንዮሽ መስፋፋት ለአርሶ አደሮች ሥጋት መሆኑ ተገለጸ

By Admin

May 03, 2017

የከተሞች ያልተገደበ የጎንዮሽ ስፋት አርሶ አደሮች ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑ ተገለጸ፡፡ በአገሪቱ ካለው ፈጣን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ጋር በተያያዘ የሚፈጠረውን የሕዝቦች የመሬት ጥያቄ ለመመለስ ከተሞች ወደ ጎን በሚለጠጡበት ወቅት፣ አርሶ አደሮች ይጠቀሙበት የነበረ መሬት መወሰዱ የችግሩ መንስዔ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የአርሶ አደሮች መሬት በሚወሰድበት ወቅት ተገቢውን ካሳ ካለማግኘታቸው በተጨማሪ፣ በሚሠፍሩባቸው አዲስ አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ያልተሟላላቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች የከተሞች የጎንዮሽ መስፋት በአርሶ አደሮች አኗኗር ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ መሆኑ የተገለጸው፣ በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የከተማ ልማት ፖሊሲ ጥናትና ምርምር በተሠራ ጥናት ነው፡፡

ጥናቱ ከሚያዝያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በጎንደር ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የከተሞች ፎረም የቀረበ ሲሆን፣ በከተሞች የጎንዮሽ መስፋፋት ሳቢያ በርካታ አርሶ አደሮች ከመኖሪያቸውና ከእርሻቸው እየተፈናቀሉ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የማዕከሉ ተመራማሪ ዘመንፈስ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ ያለው የከተሞች መስፋፋት መጠን 20 በመቶ ብቻ ቢሆንም፣ የከተሞች የጎንዮሽ መስፋፋትን ተከትለው የሚመጡ ችግሮች እየናኙ መጥተዋል፡፡

በተመራማሪው ገለጻ መሠረት የሕዝብ ቁጥር ዕድገቱና የመሬት ስፋቱ የተመጣጠኑ አይደሉም፡፡ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና መቐለን ጨምሮ በስድስት ከተሞች የተሠራው ጥናት የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ለአዲስ ተስፋፊዎቹ ቦታ ሲሰጥ፣ ነባር ነዋሪዎች ከይዞታቸው ተፈናቅለው ለኑሮ ምቹ ወዳልሆኑ አካባቢዎች እንደሚወሰዱ አመልክቷል፡፡ የከተሞች መስፋፋት አሁን ባለው አካሄድ ከዘለቀም አርሶ አደሮች የበለጠ ሥጋት ውስጥ እንደሚወድቁ ተገልጿል፡፡

ብዙ የሥራ አማራጮች ስላሉ ወደ ከተሞች የሚመጣው ሕዝብ በርካታ በመሆኑ፣ ከተሞቹ የሕዝቡን ፍላጎት ለማስተናገድ ወደ ጎን ቢሰፉ በጥናትና በዕቅድ ካልተመሩ አርሶ አደሩ የማኅበረሰቡ አካል ሁሌም እንደሚጎዳ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ በተያያዥም ከአንድ አካባቢ የሚነሱ አርሶ አደሮች በሚሠፍሩበት ቦታ የሚኖራቸውን ሕይወት ከግምት ያስገባ የካሳ ክፍያ እንደማያገኙ ገልጸዋል፡፡ ከአርሶ አደሮቹ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በበለጠ መሬቱ ለግንባታው ያለው ምቹነት ትኩረት እንደሚቸረውም አስረግጠዋል፡፡

ከተሞች እየተስፋፉ ያሉበት ሒደት የአርሶ አደሮቹን ተጠቃሚነት ከግምት ያላስገባ መሆኑን ተመራማሪው አስረድተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የካሳ ክፍያ ጉዳይ ሲሆን፣ አርሶ አደሮች በቂ የካሳ ክፍያና የመፈናቀያ ድጋፍ እንደማያገኙ ተመልክቷል፡፡ ሆኖም አርሶ አደሮቹ ከአንድ አካባቢ ሲነሱ የሚሰጣቸው ክፍያ ከተፈናቀሉበት መሬት ከሚያገኙት ጥቅም ጋር የሚመጣጠን መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡ ካሳው የአርሶ አደሮቹን ቀጣይ መጪ ዓመታት ከግምት በማስገባት ከፍተኛውን የገበያ ዋጋ ታሳቢ ያደረገ እንጂ፣ ያለፈውን የኑሮ ሁኔታ የተመረኮዘ መሆን የለበትም ይላሉ፡፡

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከተሞች እየተስፋፉ ባሉባቸው አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮች ከመኖሪያቸው እንደሚነሱ የሚገለጽላቸው በተገቢው ሁኔታ አይደለም፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች ከመሬታቸው እንደሚነሱ የሚገለጽላቸው በጠቅላላ ጉባዔ ወይም በስሚ ስሚ በመሆኑ ንብረታቸውን ለመሰብሰብ በቂ ጊዜም አያገኙም፡፡ በጥናቱ መሠረት ከአዲስ አበባ ተነሺዎች 81 በመቶ በጠቅላላ ጉባዔና ሰባት በመቶ በስሚ ስሚ ስለመፈናቀላቸው አውቀዋል፡፡

አርሶ አደሮች የሚሠፍሩባቸው አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ መጓተት ሌላው ችግር ሲሆን፣ በውጣ ውረድ ውስጥ ሆነው የሚለቋቸው መሬቶች ለታቀደላቸው ዓላማ የማይውሉበት ጊዜ መኖሩ ችግሩን እንደሚያባብሰው ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሮች ከመሬታቸው ከተፈናቀሉ በኋላ መሬቱ በታሰበው መንገድ ግልጋሎት የማይሰጥባቸው ጊዜዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ባለፉት 20 ዓመታት በመቐለ ከተማ ለልማት ከተወሰዱ አካባቢዎች የታቀደው ሥራ የተከናወነባቸው 30 በመቶው ብቻ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

ተመራማሪው ዘመንፈስ (ዶ/ር) የከተሞች የጎንዮሽ መስፋፋት የአርሶ አደሩ ሕይወት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡ የአርሶ አደሮቹ አሰፋፈር የተሰማሩበትን የግብርና ዘርፍ ታሳቢ በማድረግ የሥራ ዋስትና የሚፈጥር መሆንም እንዳለበት ተናገረዋል፡፡ ከተለያዩ የክልል ከተሞች የከተማና ቤቶች ልማት ቢሮዎች የተውጣጡ የጉባዔው ታዳሚዎችም ተመሳሳይ አስተያየት አንፀባርቀዋል፡፡

የከተሞች መስፋፋት በአሉታዊ ጎኑ እንዲታይ መደረጉን በተመለከተ፣ ‹‹ከተማ መጣልኝ ሳይሆን መጣብኝ እየተባለ ነው፤›› በማለት ነበር አንድ አስተያየት ሰጪ ሁኔታውን የገለጹት፡፡ የከተሞች መስፋፋት በነዋሪዎችና በባለሙያዎች መናበብ መከናወን እንዳለበት ተመልክቷል፡፡ የክልል ከተሞች የከተማ ፕላን ከዕቅድ ባለፈ መሬት ላይ ወርዶ በተጨባጭ እንዲተረጎም የጠየቁም ነበሩ፡፡ አርሶ አደሮች ቅሬታቸውን የሚያቀርቡበትና መፍትሔ የሚያገኙበት ሁነኛ አካል አስፈላጊ መሆኑም ተገልጿል፡፡