Artcles

የክረምቱ ቤት ስራ!!

By Admin

May 23, 2017

   የክረምቱ ቤት ስራ!!

                                                    ይነበብ ይግለጡ

ክረምቱ እያስገመገመ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት በሀገር ደረጃ  የሚሰሩ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አሉ፡፡አንደኛው ያልተጠበቀ ከባድ ዝናብ ሊያስከትላቸው የሚችላቸውን የተለያዩ አደጋዎች አስቀድሞ ለመከላከል በከተሞችና በገጠር የቦይ ስራዎችን በስፋት መስራት ዝቅ አድርጎ መቆፈር ፍሰቱ አደጋ ሳያስከትል ወደወንዞች እንዲቀላቀል የማድረግ ስራዎች ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው፡፡

የክረምቱ ዝናብ ከመደበኛው ግዜ ቀድሞ የመጣ በመሆኑ በቀጣዮቹ ወራት የዝናቡ መጠንና ውሀው ሊቀንስ ስለሚችል በተለይ በገጠሩ አካባቢ ሰፋፊ ጉድጓዶችን በመቆፈር ውኃውን ጠልፎ ማስቀረት ወደመሬት እንዲሰርግ የማድረጉ ስራም ለቀጣዮቹ ግዜያት ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል፡፡

ጭርሱንም ዘንቦ በማያውቅባቸው አካባቢዎች ደግሞ የክረምቱ ዝናብ ሲዘንብ የጎርፍና የወንዞች ፍሰትና ሙላት ከመደበኛው መንገድ ውጭ አልፎ አደጋ እንዳያስከትል ጥንቃቄ የሚደረግበትም ወቅት ነው፡፡በዝናቡ የሚገኘው ውኃ ለአገልግሎት እንዲውል የግብርና ባለሙያዎች በመላው ሀገሪቱ አስቀድመው ሰፊ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡የተለያዩ አይነት አደጋዎች ከከባድ ዝናብ መዝነብና ተከትሎት ከሚመጠው ጎርፍ ጋር ተያይዘው ይከሰታሉ፡፡

የጎርፍ መጥለቅለቅ የወንዞች ሞልቶ ከመደበኛ ፍሰታቸው ውጭ መፍሰስ በማሳና ሰብሎች እንዲሁም በመኖሪያ ቤቶች ሊያደርሰው የሚችለው ጥፋት የመሬት ናዳና የመሳሰሉት የሚጠበቁ ስለሆኑ ከመከሰቱ በፊት ሕብረተሰቡ ሰፊ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በተለይ በእርሻ ቦታዎች የውኃው መጠን ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ በሚነሳው ጎርፍ የእርሻ ቦታዎችን ሊያጥለቀልቅ ከጥቅም ውጭ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡በከተሞች የውሀ መተላለፊያ ቱቦዎችን በመዝጋት አስፋልቶችን ሊያጥለቀልቅ መተላለፊያ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡አሁንም አቅሙ ከፍተኛ ከሆነ መለስተኛ ድልድዮችን የመስበር የመሬት መሰንጠቅ መንሸራተት ያስከትላል፡፡ከፍተኛ አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ ከሆነም የኤሌክትሪክ ፖሎችን በመጣል የአገልግሎቱን ስርጭትን ሊያስተጓጉል ይችላል፡፡

አስቀድሞ ጥንቃቄና ዝግጅት መደረግ ያለበት በብዙ መልኩ ነው፡፡ክረምቱ ለመግባት እያስገመገመ በሚገኝበት በዚህ ሰአት አስቀድመው የሚሰሩ በርካታ የልማት ስራዎች አሉ፡፡ቀድሞ በተያዘው እቅድ መሰረት በየአመቱ እንደሚደረገው ሁሉ በተራቆቱ መሬቶች አካባቢ የችግኝ ተከላና የተተከሉትንም የመንከባከብ ስራ ያለማቋረጥ ይካሄዳል፡፡ዘንድሮ በመላው ሀገሪቱ ደረጃቸውን የጠበቁ 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኞች እያዘጋጀ መሆኑን የአከባቢ ደንና የአየር ለውጥ ሚኒስቴር ከሰሞኑ አስታውቆአል፡፡በመጪው ክረምት በመላ ሀገሪቱ የሚተከሉ ችግኞች ከዘልማድ አተካከል ወጥተው ተከላውን ዘመናዊና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን ቅድመ ዝግጅቱን በማጠናቀቀ ላይ ይገኛል፡፡

በሁሉም ክልሎች በድሬዳዋና በአዲስ አበባ አስተዳደሮች ደረጃቸውን የጠበቁ  4ነጥብ3 ቢሊዮን ችግኞች ለማዘጋጀት ከ4ሺህ 280 ኩንታል የዛፍ ዘር እንዲሰበሰብና እንዲሰራጭ መደረጉ ጥንት የነበረውን የሀገሪቱን ለምለም የተፈጥሮ ገጽታና የአየር ንብረት  ወደ ነበረበት በሂደት ለመመለስ የሚያስችል ጅምር ነው፡፡ በዚህም በረሀማነትን የመሬት መሸርሸርን ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡የካርቦን ጋዝ ልቀትን ለመቆጣጠር ይረዳል፡፡ደኖችን መንጥሮ አዲስ የእርሻ መሬት ከመፍጠር ይልቅ የተራቆቱ አካባቢዎችን በማከም አነስተኛ መካከለኛና ከፍተኛ መስኖዎችን በመጠቀም ተጨማሪ እርሻዎችን ለማስፋፋት የሚያስችለን መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ደኖቻችንን ማልማት ማሳደግ ማስፋፋት መጠበቅ የሚገባን ብዙ አዋጪ ምክንያቶችም ስላሉት ነው፡፡የግጦሽ መሬቶቻችን በሚገባ በሳር ከተሸፈኑ የእንስሳት እርባታችን ራሱን ችሎ ወደላቀ ደረጃ ይሸጋገራል፡፡ይህም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ማደግና መጎልበት የራሱን ትልቅ ድርሻ ይወጣል፡፡እስከአሁን ባለው መረጃ መሰረት በቀንድ ከብት በአፍሪካ የመሪነቱን ቦታ የያዘችው ሀገራችን ነች፡፡ይሄንንም ዘመናዊ እውቀቶችን በመጠቀም ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር ይጠበቃል፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በቀድሞ አመታት የተተከሉት ችግኞች አድገው የመሬቶቹን ገጽታ ከመለወጣቸውም በላይ የተዛባውን የተፈጥሮ አየር ሚዛን ለማስተካከል የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡በረሀማነትን መቀነስ ተችሎአል፡፡ጠፍተው የነበሩ አእዋፋትና የዱር አራዊቶች ወደቀድሞ ቦታዎች መመለስ ይዘዋል፡፡ይህ ትልቅ ስኬትና ውጤትም ነው፡፡

የተፈጥሮ ጥበቃና የደን ልማት ስራው በሰፊው በመላው ሀገሪቱ ባይሰራ ኖሮ ዛሬ የተደረሰበትን ውጤት ለማግኘት አይቻልም ነበር፡፡በየአመቱ የክረምቱን መግቢያ ወቅት ጠብቆ በመንግስት ደረጃ የሚካሄደው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ከፍተኛ ውጤቶችን ለመስገኘት የቻለ ነው፡፡ባላሰለሰ ሁኔታ እየተሰራበትም ይገኛል፡፡ችግኞቹ እያደጉ ሲሄዱ የመሬት መሸርሸርን ይከላከላሉ፡፡በውስጣቸው በሚያቁሩት ውሀም ምንጮችን ማመንጨት ይችላሉ፡፡አካባቢው እርጥበት እንዲኖረውም ያረዳሉ፡፡ለእንሰሳት ቀለብ እንደልብ ለማስገኘትም ይጠቅማል፡፡

በዘንድሮው አመት  የተለያየ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች ለማፍላት ከታቀደው ውስጥ እስከ አሁን ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ጥራት ባለው መንገድ ማብቀላቸውን (መፍላታቸውን )የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡

ችግኞቹ በቀላሉ እንዳይበላሹ በሚል ቁመታቸው 40 ሴንቲ ሜትር ስራቸውም 40 ሴንቲ ሜትር ሆነው እንዲፈሉ መደረጋቸው በዚሁ አመት ለሰው ሰራሽ ደን ልማት የሚውል ግማሽ ሚሊዮን  ሔክታር የደን መሬት ተለይቶ መከለሉ፤የዛፍ ዝርያ ጥምርታ ፍኖተ ካርታ የተዘጋጀ መሆኑን የደን ሚኒስቴር መረጃ ያስረዳል፡፡በተደረገው ክትትልና ድጋፍ እስከአሁን ከ388 ሔክታር መሬት በላይ የመለየት ስራ መከናወኑ ታውቆአል፡፡

የችግኝ አፈላልና የተከላ ስራውን በስርአቱ ለማከናወን እንዲችሉ ለአርሶ አደሮችና ለአርብቶ አደሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱ ሊበረታታና በሰፊው ሊኬድበት የሚገባ ስራ ነው፡፡አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ በቀድሞ ዘመናት ከመሬቱ ጋር በተያያዘ አጠቃቀሙን ባለማወቅ እውቀትና ስልጠና እንዲያገኝ ባለመደረጉ የተለያዩ ችግሮች ውስጥ እየወደቀ ፈተናው በርትቶ ነው  የኖረው፡፡

በተለይ የአርብቶ አደሩ ሕይወት ለምለም መሬቶችንና ለከብቶቹ ውኃ ያለበትን በመከተል ይሄድ የነበረ ከመሆኑ አንጻር ይህን በሚያጣበት ወቅት ለከፍተኛ ችግር ድርቅና ረሀብ ለከብቶችና ለሰው ሕይወት ሕልፈት ችግር እየተዳረገ ነበር የሚኖረው፡፡ችግሩ አሁንም ያለ ሲሆን ለመከላከልና ዘላቂ ውጤት ለማስገኘት ሰፊ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ደኖችን ለቤት መስሪያ ለማገዶ ለእርሻ በሚል መመንጠሩ ሀገሪቱን ለተለያየ ተፈጥሮአዊ ችግሮች ተጋላጭ የሚያደርጋት መሆኑን በማሳወቅ ረገድ አርሶ አደሩንም ሆነ አርብቶ አደሩን በሰፊው ማስተማርና ማሳወቅ ተገቢ ነው፡፡የጋራና ሸንተረሩ መራቆት ያገጠጠ መሬት መሆኑ በረሀማነትን ድርቅን ማስከተሉ በተደጋጋሚ አመታት የተከሰተ እውነት ነው፡፡ከፍተኛ አደጋን የሚጋብዝ ችግር መሆኑን አርሶአደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ በውል አልተረዳውም አያውቀውም ነበር፡፡ግንዛቤ እየፈጠረ የመጣው ከቅርብ አመታት ወዲህ ነው፡፡

የደኑ መመንጠር መመናመን ባዶ መሆን የዱር እንሰሳትና አእዋፋት ጭምር እንዲሰደዱ ያደርጋል፡፡መኖሪያና መጠለያ ስለሚያጡ፡፡ከባድ ዝናብ ሲዘንብ ውኃውን ይዞ ሊያስቀር የሚችል ተክልና ደን ስለሌለ ወደ ውስጥ ከመስረግ ይልቅ ባዶ መሬቱን እየሸረሸረ ለም አፈሩን ጭምር ጠርጎ ይወስደዋል፡፡በባዶው ከፍተኛ መሬት ላይ ከመሬት መሸርሸሩም ሌላ የመሬት ናዳ ይከተላል፡፡በአፈሩ ውስጥ ያሉ ያልተጠቀምንባቸው ልዩ ማእድናት ሁሉ ተሸርሽረው ይወሰዳሉ፡፡መሬቱ ባዶ ሲሆን በተለይ በበጋው ወራት ለቤት እንሰሳት ቀለብ ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ከብቶቹ ይጎዳሉ፡፡በአካባቢው ውኃ ለማግኘት የማይቻልበት ሁኔታም ይፈጠራል፡፡ችግሩ ብዙ ነው፡፡

ደኖች ከሌሉ ወንዞችና ኩሬዎች ቢኖሩም ሊደርቁ ይችላሉ፡፡ይህንን ለመከላከል ነው በተለይ አርብቶ አደሩ ለከብቶቹ ውሀና መኖ ፍለጋ በጥንታዊ ሕይወቱ ከሚንከራተት ይልቅ በአንድ አካባቢ እንዲሰፍር ቤትና መሬት እንዲኖረው ወደ እርሻ ስራ እንዲሰማራ የጤና የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኝ የንጹህ ውሀ ተጠቃሚ እንዲሆን በእቅድ የተሰራው፡፡ውጤታማ መሆን ተችሎአል፡፡

አርሶ አደሩን በተመለከተ ቀድሞ የነበረውን ባሕላዊና በርካታ ትውልዶችን ያሳለፈ ጥንታዊ አስተራረስ እንዲለውጥ ዘመናዊ የግብርና እውቀት እንዲኖረው በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ክልሎች በመንግስት በኩል የተሰራው ስራ ከፍተኛ ለውጦችንና ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሎአል፡፡የመስኖ ውኃን በበጋው ወራት በመጠቀም የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማምረት ከቤተሰቡ ጠቀሜታ አልፎ ለገበያ በማቅረብ በሰፊው ተጠቃሚ ለመሆን ችሎአል፡፡

ድሮ በአቅራቢያው የነበሩ ወንዞችን ጠልፎ በመስኖ በመጠቀም ወይንም የዝናብ ውሀን በተለያየ ዘዴ ወደመሬት አስርጎ እርጥበት መፍጠር ጉድጓዶችን  ቆፍሮ በማጠራቀም ወሀ በሚጠፋበት ግዜ ለመስኖ ስራ የመጠቀም ልምዱም ባሕሉም አልነበረም፡፡ዛሬ ከፍተኛ ለውጦች ተገኝተዋል፡፡የወደሙትን የተፈጥሮ ደኖች ለመተካት የተያዘው ሀገራዊ እቅድ ስኬታማ ቢሆንም አሁንም ብዙ ይቀረናል፡፡ዘንድሮ በቀጣይ አመትም ሆነ ወደፊት በማያባራ ሁኔታ ችግኞችን እያፈሉ በየአመቱ በመላው ሀገሪቱ የመትከሉ ስራ የቀጣዩም ትውልድ ባሕል ሁኖ እንዲቀጥል ምድርን አረንጉዋዴ እናልብሳት በሚል መሪ መፈክር የችግኞችና የደን ቀን በሀገር ደረጃ መከበር ይገባዋል፡፡

በብሔራዊ ደረጃ ስራ ሳይስተጓጎል በተለያዩ ዝግጅቶች ቀኑን መዘከር ይቻላል፡፡የተተከሉ ወይም የሚተከሉ ችግኞች በሂደት አድገው ትልቅ ደን ይሆናሉ፡፡ደኖች ከሌሉ የሰው ልጅ ሕይወት በብዙ መልኩ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ደኖች ብዙ ተፈጥሮአዊ አደጋዎችን ከመከላከላቸውም በላይ ለሰው ልጅና ለቤት እንሰሳት ለአእዋፋት ለዱር አራዊቶችም ሕይወት እጅግ ወሳኝ ናቸው፡፡ደኖቻችንን ከጭፍጨፋና ከምንጠራ መታደግ አለብን፡፡

ደኖች የሀገርና የሕዝብም ሕይወት ናቸው፡፡የችግኝ ተከላና ማፍላቱ ስራ ሰፊው ሕብረተሰብ ውስጥ እውቀቱ እንዲሰርጽ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ እንዲስፋፋ ማድረግ ትልቅ ውጤት ያስገኛል፡፡እንዲያውም የትኛው ቀበሌ ወይም የገበሬ ሰፈር ወይንም የአርብቶ አደሩ አካባቢ የበለጠ በደንና በአዳጊ ችግኞች ተሸፈነ በሚል ወደፊት የበለጠ ለማትጋት አንዱን ከሌላው መንደርና ቀበሌ ጋር በማወዳደር ሽልማቶች መሸለም የበለጠ ተነሳሽነትን ከመፍጠሩም በላይ የደን ምንጠራንም ለመከላከል ይረዳል፡፡

በውጭ ሀገራት አንድ ዛፍ ወይም ያደገ ተክል የቆረጠ አንድ ሰው እንደገደለ ተቆጥሮ በሕግ ይቀጣል፡፡በቆረጡት ምትክም የመትከል ግዴታ አለባቸው፡፡እነዚህን ግንዛቤዎች ለመፍጠር የአካባቢ ደንና አየር ለውጥ ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ እውቀቶችን በሕዝቡ ውስጥ ለማድረስ ሚዲያውን ተጠቅሞ ሰፊ ስራ መስራት ይጠበቅበታል፡፡