NEWS

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሳዑዲ የሚመለሱ ዜጎችን ሁኔታ በስፍራው ተገኝተው እየገመገሙ ነው

By Admin

May 25, 2017

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሳዑዲ ዓረቢያ የሚመለሱ ዜጎችን ሁኔታ በስፍራው ተገኝተው እየገመገሙ ነው።

በእርሳቸው የተመራው የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ሃይል ወደ ሳዑዲ አምርቷል።

ልዑኩ ከሳዑዲ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሰነድ የሚያገኙባቸውን እና የሰነድ አሰጣጥ ሂደቱን እየገመገመ ሲሆን፥ እስካሁንም በሁለት ማዕከላት በመገኘት አጠቃላይ ሂደቱን ገምግሟል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሳዑዲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር እንደተገናኙም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ዶክተር ወርቅነህ ዛሬ ምሽት ከሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡

መንግስት አዋጁ የሚመለከታቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ፥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ሃይል አቋቁሞ እየሰራ ነው።

እስከ ዛሬ በተከናወኑ ስራዎች ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ግን ከሚጠበቀው አኳያ አነስተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ የምህረት አዋጁ ቀነ ገደብ ሳይጠናቀቅ፥ ወደሀገራቸው እንዲመለሱም መንግስት ጥሪ እያደረገ ገኛል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት በሀገሪቱ ያሉ የመኖሪያ እና የስራ ፍቃድ የሌላቸው የውጭ ሀገራት ዜጎች ለቀው እንዲወጡ ካለፈው መጋቢት 21 እስከ መጭው ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ የዘጠና ቀናት የምህረት አዋጅ አውጇል።