NEWS

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ተግባራት የሚውል የ4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

By Admin

May 18, 2017

ባንክ በአገሪቷ በአጋርነት ለሚያከናውናቸው የተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚውል የ4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለም ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ  ክሪስታሊና ጂኦርጂቫ ጋር ተወያይተዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ   ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከድህነት ለማላቀቅ ከዓለም ባንክ ጋር በቀጣይ ሦስት ዓመታት በአጋርነት ለምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች የሚውል የ4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ድጋፉ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ ለተፋሰስ ልማት፣ ለሴቶች ሥራ ፈጠራና ለሴፍቲኔት ፕሮግራም እንደሚውልም ገልጸዋል።

በድህነት ቅነሳና በሥራ ፈጠራ ላይ የተሰራውን ሥራ አድንቀው በአገሪቷ ያለውን እምቅ የፈጠራ አቅም መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በተለይም በሴፍትኔት ፕሮግራም እየተከናወነ ያለው ተግባር ዜጎች ከድርቅ እንዲወጡ ብቻ ሳይሆን ህይወታቸው በዘላቂነት እንዲቀየርና እንዲሻሻል ማድረግ መቻሉ የሚደነቅ እንደሆነም ነው የገለፁት።

በቀጣይም የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በጋራ ለመከወን ምክክር እየተደረገ መሆኑንና መግባባት ላይ ሲደረስ የድጋፉ መጠን ሊጨምር እንደሚችል አስታውቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው አገሪቷ ድህንትን ለማሸነፍና መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት ከዓለም ባንክ ጋር መስራቷ ለውጥ ማምጣቱንና ድጋፉ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በሴቶች ተጠቃሚነት፣ በስራ ፈጠራ፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲሁም በሴፍትኔት ፕሮግራም የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት።