CURRENT

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በኢትዮጵያ እየተከበረ ነው

By Admin

May 03, 2017

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በኢትዮጵያ በመከበር ላይ ይገኛል።

ቀኑ የተለያዩ የመንግስት እና የግል ሚዲያ ተቋማት ባለሙያዎች እና ተወካዮች በተገኙበት ነው በአዲስ አበባ ከተማ በመከበር ላይ የሚገኘው።

በዝግጅቱ ላይም የፕሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ፣ የመገናኛ ብዙሃን ችግሮች እና አማራጮች የሚል ፅሁፍ ቀርቦም ውይይት እየተደረገበት ነው።

በውይይቱ ላይም የመገናኛ ብዙሃን ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ መረጃን በማድረስ መልኩም ችግሮች እንደሚስተዋሉባቸው ተነስቷል።

ለግሉ መገናኛ ብዙሃን ከመንግስት የሚደረግላቸው ድጋፍ አነስተኛ መሆኑ እና የግል የመገናኛ ብዙሃን ቁጥር አነስተኛ መሆን ላይ ውይይት እየተደረገባቸው ነው።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፥ በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፤ ሆኖም ግን በህገ መንግስቱ ከከላ አግኝቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ሁለት አስርት ዓመታትን ብቻ ማስቆጠሩን አንስተዋል።

ዘርፉ አሁንም ቢሆን ከእውቀት እና ከክህሎት ጋር ተያይዞ ክፍተቶች ስለሚስተዋልበት የሚፈለገው ደረጃ ላይ ማድረስ አልተቻለም ሲሉም ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙሃን የተሟላ ሙያዊ ስነ ምግባር እንዲሁም ሙያዊ እውቀት እና ክህሎት እንዲኖራቸው በስፋት መሰራት እንዳለበትም ገልጸዋልል።

የግልም ሆነ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በተጨባጭ መረጃ ላይ በመመስረት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማጋለጥ በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።